በሦስት ወራት የ 20 ቢሊዮን ብር ነዳጅ ተገዝቷል

Views: 372

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በ2012 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ 20 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 932 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን ገለፀ።

በ 2011 ተመሳሳይ ወቅት ድርጅቱ በጥቅሉ 913 ሺሕ 167 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለገበያ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ በዚህኛው በጀት ዓመት ወደ አገር ውስጥ የገባው የነዳጅ አቅርቦት እስከ 20 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚደርስ ጭማሪ አሳይቷል።

ወደ አገር ውስጥ ከገቡ የነዳጅ ምርቶች ውስጥም ቤንዚን 141 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ፣ ነጭ ናፍጣ 577 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 190 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በመያዝ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የነዳጅ ምርቶቹ ኢትዮጵያ ከኩዌት፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከሱዳን መንግሥታት ጋር ባላት የኹለትዮሽ የኢኮኖሚ ስምምነት መሠረት በጅቡቲ ወደብ በኩል የሚገቡ ናቸው። ከኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፓሬሽን፣ አድኖክ (ADNOC) ከተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያ እና ከሱዳን ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ነዳጅ በቀጥታ ግዥ እየቀረበ እንደሚገኝ ድርጅቱ ገልጿል።

በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው የነዳጅ ፍላጎትን ተመርኩዞ በተለያዩ ክልሎች 13 የመጠባበቂያ ነዳጅ ዴፖዎችን ገንብቶ 360 ሺሕ ሜትሪክ ኩብ ክምችትን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ የነዳጅ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዓለማየሁ ፀጋዬ ገልጸዋል። ዘለቄታዊ ጠቀሜታ እና የኢኮኖሚ ፍሰትን መሰረት ያደረጉ ጥናቶችን በማካሔድ ተጨማሪ ዴፖዎች በመገንባት መጠባበቂያ ነዳጅ ከማቅረብ በተጨማሪ የአቅርቦት መቆራረጥን ለማስቀረት እና በጅቡቲ ሆራይዞን ላይ የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለመቀነስ የሚያስችል የአገር ውስጥ ኦፕሬሽናል ዴፖ እና ተርሚናሎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህም መካከል አዋሽ ኦፕሬሽናል ዴፖ ለኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር በቅርብ ርቀት ላይ ከባቡር እና ከነዳጅ ጫኚ ተሸከርካሪ ለመቀበል የሚያስችል መሠረተ ልማት አካትቶ መገንባቱ የተገለፀ ሲሆን፣ የአዋሽ ኦፕሬሽናል ነዳጅ ዴፖ 33 ሺሕ ሜትሪክ ኩብ የማከማቸት አቅም ያለው እንዲሁም 33 ሺሕ ሜትሪክ ኩብ በድምሩ 66 ሺሕ ሜትሪክ ኩብ ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር በግንባታ ላይ ይገኛል።

እነዚህ ማከማቻዎችም በባቡር ተጓጉዞ የሚመጣውን ነዳጅ በመቀበል በአንድ ጊዜ 16 ቦቴ ተሽከርካሪዎችን ለመጫን እና 8 ቦቴ ነዳጅ ለማራገፍ የሚያስችል ተርሚናል አካትተዋል።

የባቡር መሠረተ ልማቱ ነዳጅ ማቅረብ ሲጀምር ከ70 እስከ 80 ቦቴ መኪኖች የሚጭኑትን የነዳጅ መጠን በአንድ ጊዜ ከማስተናገዱ ባሻገር ለነዳጅ ጫኚ ተሽከርካሪዎች እስከ ኹለት ቀናት የሚጠይቀውን የጉዞ ጊዜ በ10 ሰዓታት ውስጥ ማድረስ ያስችላል ተብሏል።

በተመሳሳይ በዱከም ከተማ 300 ሺሕ ሜትሪክ ኩብ የመጠባበቂያ ነዳጅ ክምችትንና የተርሚናል አገልግሎትን የሚሰጥ ለመገንባት ከሚመለከተው የመስተዳደር አካል የቦታ ርክክብ ተደርጎ የቅየሳ፣ የአፈር ምርመራ እና የዲዛይን ሥራ ተጠናቅቆ የፕሮጀክቱ ቅድመ-ግንባታ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

የነዳጅ ድርጅቱ ላለፉት 52 ዓመታት የተጣሩ የነዳጅ ውጤቶችን በጅቡቲ ወደብ በኩል እና ከሱዳን በማቅረብ ላይ ነው። እነዚህም የነዳጅ ውጤቶች ቤንዚን፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ነጭ ናፍጣ፣ ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ/ፊውል ኦይል/ እና ኬሮሲን ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com