ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል በክልሎች መካከል

Views: 367

በኢትዮጵያ አንዳንድ የክልል መንግሥታት ከሌሎቹ በበለጠ የበለፀጉ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በኢኮኖሚ፤ በኢንቬስትመንት፣ በንግድ እንዲሁም በማህበራዊ እና መሰረተ ልማት ወደ ኋላ የቀሩ ናቸዉ። በክልሎች መካከል ያለዉ የሃብት ክፍፍል ፍትሃዊ አይደለም። ምንም እንኳን በክልሎች መካከል ከፍተኛ የዕድገት ያለመመጣጠን ቢኖርም ሰፊውን ክፍተት መፍታት አሁንም ከባድ ነዉ። ከዚህ በፊት ያለመመጣጠኑን ለማስተካከል የተለያዩ ፖሊሲዎች ተሞክረው የነበረ ቢሆንም በዋነኛነት የጉዳዩ የፖለቲካ አጀንዳ መደረግ አንዳቸዉም መፍትሔዎች እንዳይሠሩ አድርጓቸው እንደቆየ አሸናፊ እንዳለ ዳሷል።

የቡና መገኛ የሆነው በደቡብ ክልል የሚገኘዉ ከፋ ዞን መጠነ ሰፊ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ያሉት ሲሆን በክልሎች መካከል ያለውን ያልተመጣጠነ ዕድገት ለማሳያ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላል። ከፋ በማር፤ ቡና ፤ በቆሎ፤ ባቄላ፤ ጣውላ እና የቁም ከብቶች ምርት የተትረፈረፈባት ብትሆንም የተመቻቸ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ወደ ከማዕከላዊ ገበያ ጋር ያላት ቁርኝት በጣም አናሳ ነው። ከቦታው የሚወጡ ምርቶች አላስፈላጊና ረጅም የጉዞ መስመር ተከትለው ከሔዱ በኋላ ነው ማዕካላዊ ገበያ የሚደርሱት። ቀደም ሲል ከፋ ዞን ደመቅ ያለ ስልጣኔ የነበራት ቢሆንም በአሁን ሰዓት ግን ያንን እንደገና እንዲያበብ ማድረግ አልተቻለም። ቢያንስ ላለፉት ዐስር ዓመታት የከፋ ዞን ነጋዴዎች፤ ገበሬዎች እና ነዋሪዎች መንገድ፤ አየር ማረፊያ፤ ንፁህ ዉሃ፤ ሆስፒታሎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንዲገነባላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር።

ይህን በማስከተል በሺዎች የሚቆጠሩ የከፋ ዞን ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመስከረም 2012 ቦንጋን ለመጎብኘት በሔዱበት ጊዜ ከደቡብ ክልል ተለያይተዉ ክልላዊ መንግሥት የመሆን ጥያቄ አቅርበዉላቸው ነበር። በርግጥ በድቡብ ክልል ያሉት ዐስሩም ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን በመንግሥት ተቀባይነት ያገኘው የሲዳማ ዞን ጥያቄ ብቻ ነዉ። ‹‹ክልላዊ መንግሥት መሆን ከልማት ጋር ለተያያዙ ችግር ሁሉ መፍትሄ ሊሆን አይችልም።›› ነበር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ። በኢትዮጵያ ወስጥ የሚነሱት የክልልነት ጥያቄዎች ጀርባ ያለው ጉዳይ የእኩልነት ጥያቄ ነዉ።

ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት በፌዴራል ስርአቱ ስር ያሉ በርካታ አካባቢዎች በልማቱ ተጠቃሚ አልነበሩም። በአብዛኛዉ ጊዜ የልማት ፕሮጀክቶች የክልሎችን የስትራቴጂክ አጋርነት ወይም የመደራደር አቅም ተመርኩዘው በማዕከሉ የሚተገበሩ መዘወርያዎች ነበሩ። ማዕከላዊ አስተዳደር የክልሎችን የልማት ፍላጎት ለማስተናገድ እንዲሁም የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሰራጨት ያለው አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ብቸኛዉ አማራጭ ክልሎች እና የአካባቢ አስተዳደሮች እራሳቸውን እንዲያለሙ እደል መስጠት ነወ። በመሰረታዊ ደረጃ የክልሎች ያልተመጣጠነ ዕድገት ፍትሃዊ ካልሆነ የመሰረተ ልማት ስርጭት ጋር የተያያዘ ነው። ስለሆነም አንዳንድ ክልሎች የተሻለ ኢንቬስትመንት ፍሰት፤ ምርታማነት ፤ የነፍስ ወከፍ ገቢ እና የሥራ ዕድሎች ሲኖሩዋቸው ሌሎች ደግሞ ለተሻለ ዕድሎች ለመሰደድ ምናልባትም የፖለቲካ ትግል ለማካሔድ ይገደዳሉ።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጠናቀረ ሪፖርት በክልሎች መካከል ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት አለመኖሩን ማሳየቱን ተከትሎ ምክር ቤቱ የመሰረት ልማት ፍትሃዊነትን የሚዳስስ ንዑስ ኮሚቴ አቋቁሟል። የሶማሊ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አደም ፋራ ‹‹ፍትሃዊ ባልሆነ የክልሎች የሀብት ክፍፍል ምክንያት ብዙ ተሰቃይተናል።›› ብለዋል። የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት እርስቱ ይርዳዉ በበኩላቸዉ ከፍተኛ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ፀጋ እና ሰፊ መሬት የታደለው ክልላቸው ማዕከላዊ መንግሥት በሳል የፕሮጀክት ስርጭት ዘዴ ቢነድፍ ኖሮ የተሻለ የዕድገት ሁኔታ ይኖረው እንደነበር ይናገራሉ። ‹‹ሩቅ የሆኑ ቦታዎች በጭራሽ ተዘንግተዋል። እንደ መንገድ፤ የኃይል እና የስልክ አውታረ መረብ ያሉ መሰረተ ልማቶች እንደውም የላቸዉም። በተጨማሪም ከጠረፍ ከተሞች ጋር እና ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ጋር እቃዎቻቸውን ለመለዋወጥ ተገቢ ገበያዎች እና የስርጭት መስመሮች የሏቸውም።›› ብለዋል።

መሰረተ ልማት፡ ሀብት ወይስ የምርት መንስኤ?
ባለፉት ዐስራ አምስት ዓመታት በአገሪቱ ለታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ መሰረታዊ ልማት በተለይም መንገዶች ላይ የተደረገው ኢንቬስትመንት ነው። ለይ የተደረገ ኢንቬስትመንት የኢትዮጵያ ጂዲፒ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት ነዉ። ባለፉት 21 ዓመታት ወስጥ የመንገዶች ሽፋን ከ26,000 ኪ.ሚ ወደ 127,000 ኪ.ሜ አድጓል። ነገር ግን ይህ ከአገሪቱ የመንገድ ፍላጎት 32 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን መሆኑን በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ መረጃ ትንተና እና ጂኤይኤስ ቡድን መሪ ሲክስ አብራር ያስረዳሉ። በዚህ የበጀት ዓመት ብቻ መንግሥት ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከፍተኛው የሆነውን 46 ቢሊዮን ብር በጀት መድቧል። ‹‹መንግሥት መንገዶች ላይ ያተኮረው በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው መንገዶችን በማስፋፋት ምርትን ለማሳደግ እና ገበያና አምራችን ለማቀራረብ ነው። ሁለተኛው መንገዶችን በማሻሻል የሽያጭ ታሪፍን ለመቀነስ ነው። የመንገድ ደረጃ ከጠጠር ወደ አስፋልት ከፍ ሲል የነዳጅ ወጪ እና የመኪኖች የአገልግሎት ዘመን በ45 በመቶ ይሻሻላል።›› ይላሉ ሲክስ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ድጎማ እና የጋራ ገቢዎች ድልድል ቋሚ ኮሚቴ በግንቦት 2011 ባወጣው ሪፖርት መሠረት በፌዴራል መንግሥቱ የተገነቡ መንገዶች በትግራይ ክልል ካሉ ወረዳዎች ውስጥ 95.5 በመቶዎቹን ሲያገናኙ፤ በአማራ ክልል 82 በመቶዎቹን፤ በደቡብ ክልል 81 በመቶዎቹን፣ በኦሮሚያ ክልል 73.6 በመቶዎቹን እና ዝቅተኛ ተብሎ የተያዘውን በሶማሌ ክልል 57 በመቶዎቹን አገናኝተዋል። ትግራይ እና ጋምቤላ ከፌዴራል መንገድ ጋር የማይገናኙ ሁለት ወረዳዎች ብቻ ያሏቸው መሆኑ ዉዝግብ አስነስቶ የነበር ሲሆን የትግራይ ክልል ሪፖርቱ ትክክል ያለመሆኑን ገልጾ የአስተዳደር ለውጡን ግምት ውስጥ ያላስገባ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሷል ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር። በተጨማሪም በትግራይ ክልል ካሉት ወረዳዎች 92 በመቶዎቹ በኮንክሪት አስፋልት የተያያዙ ሲሆን በአማራ ክልል ይህ ቁጥር 51 በመቶ፤ በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልል 46 በመቶ፣ በአፋር 45 በመቶ፤ በጋምቤላ 39 በመቶ፣ በቤንሻንጉል 25 በመቶ እና በሶማሊያ 15 በመቶ ነዉ።

ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያጠናቀረዉ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ መሰረተ ልማት ለማጎልበት ኃላፊነት የተሰጣቸወ ተቋማት ሶስት ዋና ዋና ችግሮች አሉባቸው። የመጀመሪያዉ በክልሎችና በከተሞች የፕሮጀክት ስርጭት ግልፅ እና የተረጋገጠ ቀመር አለመኖር ነዉ። ምንም እንኳን ፌዴራል መንግሥት ፕሮጀክቶች የሚፀድቁት ፍላጎትንና የሚያስገኙትን የጥቅም መጠን መሠረት አድርጎ ነው ቢልም እውነታው ግን ከዚያ የተለየ ነው። ሁለተኛው የአዋጭነት ጥናት በሚያካዱ አማካሪዎች እና ተቆጣጣሪዎች ሆን ተብሎ የሚደረግ የመረጃ ለውጥ ነዉ። ሶስተኛው ፕሮጀክቶች የት፤ ምን እና እንዴት እንደሚገነቡ ጫና ለማሳደር ባለሥልጣናት ጣልቃ መግባታቸው ነው።

በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ መምህር እና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ታደለ ፈረደ (ፕሮፌሰር) ‹‹ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች እንኳን የአዋጪነት ጥናት ሲጀመሩም ሆነ ሲጠናቀቁ ንድፍም የላቸዉም›› ብለዋል። ‹‹ለምሳሌ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ሀዲድ ሲጠናቀቅ በመጫኛ እና ማውረጃ ጣቢያዎች መካከል እና ሀዲዱ በሚያልቅበት ቦታ የጭነት መኪኖች ያስፈልጉታል። የባቡር ሃዲድ ያለ መገጣጠሚያዎች መገንባት ያለማወቅን የሚጠቁም ነዉ።››

በደቡብ ክልል 2531 ቀበሌዎች (በክልሉ ዉስጥ ካሉት አጠቃላይ ቀበሌዎች 66 በመቶዎቹ) በሁሉም ወቅቶች በሚሠሩ መንገዶች የተገናኙ እንደሆኑ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ ያሳያል። በተመሳሳይ ሁኔታ ኦሮሚያ፤ አማራ፤ ትግራይ እና ቤንሻንጉል ክልሎች ከ60 በመቶ በላይ የተገናኙ ሲሆን የተቀሩት ከዚህ በጣም ዝቅ ባለ ደረጃ የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ በሶማሊያ ክልል በሁሉም ወቅቶች ከሚሠሩ መንገዶች ጋር የተያያዙት 30 በመቶ የሚሆኑት ቀበሌዎች ብቻ ናቸው። ከፍተኛ የቆዳ ስፋት በመያዝ አገሪቱ ውስጥ ካሉት ቀበሌዎች 42 በመቶዎቹን የያዘችው ኦሮሚያ ካሏት 6478 ቀበሌዎች ዉስጥ 93 በመቶዎቹን በማገናኘት አገራዊ አማካኝ ከሆነው 76 በመቶ ከፍ ያለ የቀበሌዎች ግንኙነት መጠን አላት። ሆኖም በመላ አገሪቱ መንገድ ግንባታ ላይ ከፈሰሰው መዋዕለ ንዋይ በተቃራኒ ክልሎች ሁልጊዜም ስለ ሃብት ክፍፍል ፍትሃዊነት ቅሬታ ያሰማሉ። ‹‹መንገዶችን የምንገነባው ለአገራዊ ኢኮኖሚ ያላቸውን አስተዋጾኦ መሠረት አድርገን ነው። እናም መንግሥት የጠየቅነዉን ያህል በጀት ስለማይሰጠን ገንዘቡን ቅድሚያ ለሚሰጣቸዉ መንገዶች ብቻ እንጠቀማዋለን›› ሲሉ ሲክስ ያብራራሉ።

በፌዴራል መንግሥት የሚሠሩ ሌሎች ዋና ዋና የሕዝብ ፕሮጀክቶች ዩኒቨርስቲዎችን፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች እና ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ያካትታሉ። ሁሉም ክልሎች ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ግንባታ አስመልክቶ ቅሬታቸውን ገልፀዋል። ለምሳሌ የአገሪቱ ደቡባዊ እና ምዕራባዊ ክፍሎች ምንም የአውሮፕላን ማረፊያ የለቸውም። የንግድ ጉዞዎች እና ከዚህ አካባቢ የሚወጡ ትኩስ ምርቶች በዝግተኛ እንቅስቃሴ ምክንያት ሁልጊዜ አደጋ ላይ ናቸው። ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሊ እና ድቡብ ክልሎች እያንዳንዳቸው አንድ ወይም ሁለት የአውሮፕላን ማረፊያ ሲኖራቸው የትግራይ ክልል 3 የአየር ማረፌያ አለዉ።

በዩኒቨርስቲ አኳያ ደግሞ አብዛኞቹ አካባቢዎች ቃል የተገባላቸውን አግኝተዋል። የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ወደ 45 ያሻቀበ ሲሆን ኦሮሚያ በ12 ሲመራ አማራ እና ደቡብ ክልል እያንዳንዳቸው ዐስር በመያዝ ይከተላሉ። ትግራይ ደግሞ 4 አለው ። ምንም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ከሌላት ሀረሪ በስተቀር የተቀሩት ክልሎች አንድ ወይም ሁለት አሏቸው። ባለሞያዎች በሰዉ ልጆች ላይ እሴት ከመጨመር ይልቅ በብሔሮች መካከል ላለው ውድድር ምላሽ ለመስጠት ነው የተቋቋሙት በሚል በዩኒቨርሲቲዎቹ ስርጭት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። ለምሳሌ ብዙዎች ሀረሪ ታሪካዊ ሥልጣኔዋን እንዲሁም አሁንም ያሉ ማህበራዊ እና ከከተሜነቷ ጋር የተያያዙ ውብ እሴቶቷን የምታጠናበት ልዩ ዩኒቨርሲቲ ያስፈልጋታል ይላሉ። ነገር ግን የክልሉ መንግሥት በፖለቲካ ውስጥ ጫና የማሳደር አቅሙ አናሳ ስለሆነ ይህ ሊሆን አልቻለም።
ሌላዉ አወዛጋቢ ነጥብ የኢንዱስትሪ ግንባታ ነዉ። ምንም እንኳን ወደ ኢንዱስትሪ መርነት የሚደረግ ጉዞ፤ ኤክስፖርት እና የሥራ ፈጠራ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት መንስኤ ቢሆኑም የሚሠሩበት ቦታ በዋነኝነት የሚወሰነዉ ክልሎች በሚያሳድሩት ጫና ነው። ኦሮሚያ እና አማራ እያንዳንዳቸው አምስት ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሲኖራቸዉ ትግራይ እና ደቡብ ደግሞ እያንዳንዳቸው ሁለት አሏቸው። ሌሎቹ ግን ምንም የላቸዉም።

በ3ጂ አውታረ መረብ መሰረተ ልማት አማራ በ71 በመቶ ሲመራ፤ ኦሮሚያ በ66 በመቶ እና ደቡብ ክልል በ64 በመቶ ይከተላሉ። ለሌሎች ክልሎች ግን ሽፋኑ ከ40 በመቶ በታች ነዉ። በኤሌክትሪክ ተደራሽነት ትግራይ በ21 በመቶ ሲመራ በመቀጠል ኦሮሚያ በ15 በመቶ፣ አማራ በ10 በመቶ፣ ድቡብ ክልል ደግሞ 9 በመቶ እና ሶማሊ በ4.5 በመቶ ይከተላሉ።

የእነዚህ መሰረተ ልማቶች በክልሎች ያለውን የኢንቬስትመንት ፍሰት ይወሰናል። ማንነቱ እንዲገለፅ ያልፈለገ ባለሙያ እንደገለፀው በአገሪቱ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ የተሳሳተ በመሆኑ የተነሳ የክልሎች የፕሮጀክት ስርጭት በመሰረቱ የተሳሳተ ነው። ‹‹በጎሳ የታነፀ የፖለቲካ ሳጥን ዉስጥ ልማት ለማየት ይሞክራሉ። በገዢው ፓርቲ ዉስጥ ጠንካራ ድምፅ ያለዉ ክልል ከፍተኛውን ቁራሽ ማግኘቱ የተረጋገጠ ነው።››

እንደ ባለሙያዉ ገለፃ ፕሮጀክቶች በሶስት የተከፈሉ ናቸዉ። አንደኛዉ በፌደራል መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚሠሩ ናቸዉ። ይህ አብዛኛዉን ጊዜ የተሻለ የፖለቲካ ተፅኖ ለሚያሳድሩ የሚሔድ ነው። ሁለተኛዉ በልማት ድርጅቶች እና በውጭ ቀጥተኛ ኢንቬስትመንት የገንዘብ ድጋፍ የሚሠራ ሲሆን ከፓርቲ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው። ሶስተኛዉ በራሳቸው የክልል መስተዳድሮች የሚሠራ ሲሆን ከሌሎች ተግዳሮቶች ጋር በገንዘብ የተገደቡ ናቸዉ።

ባለሞያዉ እንደተናገሩት ‹‹አንድ ባለሥልጣን የራሱን ክልል ለማልማት የሚጥር ከሆነ ማዕከላዊ መንግሥት ከቦታው ያነሳዋል ወይም ወደ ሌላ ቦታ ያዛውረዋል። ሌባ እና ግድ የለሽ ከሆኑ ግን በሥልጣን ላይ ሊቆዩና የፈለጉትን ሊያድርጉ ይችላሉ። በአሁኑ ስርአት ኪስህን ልታደልብ ትችላለህ አንድ ክልልን ግን አትችልም።›› ‹‹ማእከላዊ መንግሥት አንድ ክልል ቢበለፅግ ሌሎቹ ቂም ሊይዙ ይችላሉ ብሎ ይፈራል›› ሲሉ ባለሙያው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በመፍትሔነት የሚያነሱት ሀሳብ ለሁሉም የኢኮኖሚ ነፃነት መስጠትን ነው። ማዕከላዊ መንግሥት ጠንካራ ክልሎች በእራሳቸው እንዲሔዱ በመተዉ ራሱን በቁጥጥር መገደብ ይገባዋል። ከዚያ ማዕከላዊ መንግሥት በቂ ጊዜ እና ሀብት በመቆጠብ ኋላ ቀር እና የተዘነጉ ክልሎችን ሊደግፍ ይችላል ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸዉ ክልሎች በፌዴራሉ መንግሥት ላይ ጥገኛ እንዳይሆኑ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ነፃነት ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ። ‹‹በባለፈው የሕዝብ ቆጠራ ዝቅ ተደርጎ በተቀመጠው የሕዝብ ቁጥር እና የጉዳዮ ፖለቲካዊ መልክን መያዝ ምክንያት ፍትሃዊ ያልሆነው የሃብት ክፍፍል ላይ የእርማት ርምጃዎችን ከመውሰድ በተጨማሪ ፌዴራል መንግሥት የክልሎች ኢኮኖሚያቸውን በብቃት እንዲያስተዳድሩ እና ከጥገኝነት እንዲላቀቁ አቅም ለመገንባት መሥራት አለበት።›› ብለዋል።

ከአቅርቦት ወገን፡ ከትራንስፎርሜሽን ወደ ማሻሻያ
ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ ፕሮጀክቶች ክልሎች ውስጥ የተሰራጩ ባለመሆናቸው የተነሳ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ ኢኮኖሚ ዉስጥ ተካተው ምርታማነትን ከፍ ሊያደርጉ አልቻሉም ነበር። ከፍተኛ እምቅ አቅም ያላቸው ክልሎች የፖለቲካ ጫና የማድረግ አቅም ስለሌላቸው ብቻ በኋላቀርነት እና ድህነት ውስጥ እየማቀቁ ነው። ባለፉት ዐስር ዓመታት የታየው የኢትዮጵያ እድገት በጥቂት ማዕዘኖች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሲሆን ዕድገትን ያልተማከለ ሊያደርጉ የሚችሉ ቦታዎች ደግሞ ይበልጥ ተገለዋል። የፋይናንስ ሚኒስትር የሆኑት እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ መዋቅራዊ ለዉጥ ለምን እንዳልተሳካ መጠየቅ አለብን። በመሠረተ ልማት ላይ በከፍተኛው ኢንቬስት የተደረገ ቢሆንም የአቅርቦት መሻሻል ግን እውን ሊሆን አልቻለም።›› ብለዋል።

በአሁን ጊዜ መንግሥት በባለፉት 15 ዓመታት በመሰረት ልማት ላይ ኢንቬስት በማድረግ የመጣውን የኢኮኖሚ ዕድገት ሚዛን ለመጠበቅ አቅርቦትን ከፍ በማድረግ ላይ ያተኮረ አዲስ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እያካሔደ ይገኛል። ‹‹ይህ ማሻሻያ ከዚህ በፊት ተደጋግመዉ ከተወሰዱት የተበጣጠሱ ማሻሻያዎች በተለየ መልኩ አጠቃላይ እና መሰረታዊ ነዉ። ይህ ማሻሻያ በምንም ዓይነት ርዕዩት ዓለም እና ሞኬል አልታሰረም። ዋነኛ ዓላማው የኢኮኖሚውን ትኩረት ከፍላጎት ወገን ይልት ወደ አቅርቦት በማዞር አቅርቦትን መጨመር ነው።›› ይላሉ እዩብ ተካልን።

የማዕከላዊ ባንክ ገዢ የሆኑት ይናገር ደሴ እንዳሉት ከዚህ በኋላ መንግሥት ትኩረት የሚሰጠዉ እስካሁን በተገነቡት መሰረተ ልማቶች በመጠቀም በአቅርቦት በኩል ያለዉን ምርታማነትን ማፋጠን ላይ ነዉ። ‹‹ለምሳሌ አዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን መገንባት አያስፈልገንም። አሁን ዋናው ሥራ ተመርቆ የሚወጣውን የሰው ኃይል ወደ ቅጥር መምራት እና መሰረተ ልማቱን ከምርት ጋር ማያያዝ ነው።›› ብለዋል የናገር።

የኢኮኖሚ ተንታኞቹ እንደሚሉት የኢኮኖሚው ውጽዓት (አውትፑት) ድጋሚ መመዘን የሚያስፈልገው ሲሆን ያለው መሰረተ ልማትም ኦዲት ተደርጎ ለሚቀጥለው የምርታማነት ጥረት ምን ያህል ብቁ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ኦዲት መደረጉ ያሉ ክፍተቶችን በማሳየት አዲስ መገንባት ያስፈልግ እንደሆነ፣ ደረጃቸውን ማሻሻል ማስፈለጉን ወይም እንዳሉ መጠቀም እንደሚያስችሉ ያስገነዝባል። ተንታኞቹ እንደሚሉት በክሎሎች መካከል ያለው ያለመመጣጠን የሚቀጥል ከሆነ የምርታማነት ክፍተቱ ይበልጥ ይሰፋል።

ገንዘብ ሚኒስቴር የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ኮሚቴ አቋቁሞ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ከአንድ ሺህ በላይ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ወጪያቸውን እየመለሱ ያሉበትን መጠን መዝኖ ሊጨርስ እንደሆነ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሃጂ ኢብሳ ገልፀዋል። ፕሮጀክቶቹ በኢኮኖሚው ላይ ያመጡትን እውነተኛ ተፅዕኖ መገምገም ከማስፈለጉ በተጨማሪ ኮሚቴው የተቋቋመው ክልላዊ መንግሥታት የፕሮጀክቶች ስርጭት ላይ ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ከገለፁ በኋላ ነው። በ2011 የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል መሰረተ ልማት ስርጭት ፍትሃዊ መሆኑን የሚዳስስ አዲስ ግብረ ኃይል አቋቁሟል። ምክር ቤቱ በጀቱን እና የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመርንም እየከለሰ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com