የኹለት ስብሰባዎች ወግ

Views: 266

ባሳለፍነው ሳምንት ኹለት ስብሰባዎች የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችለው ነበር። ከብዙ የግጭት፣ የሞትና የእሳት ዜና አረፍ ያለ የሚመስለው ሳምንት፣ መቀሌ እና አዲስ አበባ በተከናወኑ ስብሰባዎች መነጋሪያነት ወደማብቂያው ተቃርቧል። ይህንንም እንደ ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ መገናኛዎች አሳብቀዋል። ብዙዎች ሲቀባበሉት፣ አስተያየት ሲሰጡበትና ሲነጋገሩበት የነበረው ጉዳይ ይኸው የስብሰባዎቹ ነገር ነው። ስብሰባዎቹ አንዱ አገር በማበልፀግ ሌላው አገር ለማዳን የሚል መሪ ሐሳብ የተከናወኑ ስብሰባዎች ናቸው።

የአዲስ አበባው የብልጽግና ፓርቲ ስብሰባ በእርግጥ የመቀሌውን ያህል መነጋገሪያ አልነበረም ማለት ይቻላል። ሆኖም ብዙዎች ይሄ ነው ባይሉም በተስፋ የተመለከቱት ይመስላል። በእርግጥ በጥልቅ የተመለከቱ ምኁራንና ፖለቲከኞች የብልፅግና ፓርቲ ዴሞክራሲያዊነትን እያቀነቀነ ፓርቲውን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ያልሆኑትን መዝለፉን ሲወቅሱ ነበር። ያም ብቻ ሳይሆን በሙሉ ድምጽ መጽደቁን በማንሳት ‹‹ይህቺ ነገር!›› ብለው ከቀደመ ልምድ እያጣቀሱ በጥርጣሬ መመልከትን የመረጡም አልጠፉ።
በአንጻሩ የቀመሌው ስብሰባ ዱላ የበዛበት ይመስላል። ‹‹ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ ስርዓቱን ማዳን›› የሚል መሪ ሐሳብ የነበረው የመቀሌው ስብሰባ ትኩረት ያገኘው ከስብሰበው ዓላማ ባሻገር በታዩ ክስተቶች ነው። ይልቁንም አሁን ያሉትን አመራሮች የሚዘልፉ፤ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ከማንሳት ይልቅ የፈረደባቸውን ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አንስቶ ‹‹ምኒልክ መጣላችሁ!›› ዓይነት ንግግሮችን ያደረጉ ግለሰብ ከስብሰባው ዓላማና ጭብጥ የበለጠ ከንግግራቸው ጋር ምስላቸው በማኅበራዊ ገጽ ብዙዎች ሲቀባበሉት ነበር።

እንደሚታወቀው የትግራይ ክልልን በማስተዳደር ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) አጋር ፓርቲዎች ከነባሮቹ ተስማምተው የፈጠሩት ውህድ ወይም አዲስ የሆነውን የብልፅግና ፓርቲን በግልፅ ተቃዉሟል። ያም ሆኖ ምን ሊያደርጉ ወስነዋል የሚለው በተመለከተ በግልጽ የተባለ ነገር የለም።
ይህም ለግምት መቹ ሆኖ፣ ሳምንቱን ብዙዎች መላምት እየሰጡበት የከረሙ ሲሆን፣ በመቀሌው ስብሰባ ላይ በሕወሐት ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ ፓርቲዎች ሳይገኙ መቅረታቸውና አንዳንዶችም ‹መምጣት አንችልም› ብለው በግልጽ መግለጫ መስጠታቸው ጉዳዩን የበለጠ ሳቢ አድርጎታል። በድምሩ ሳምንቱ በዝምታ ከማለፍ የታደገው የእነዚህ ኹለት ስብሰባዎች መከናወን ነው።

በስብሰባው መካከል ታድያ የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ መደመርንም ሆነ ውህደቱ ቢቆይ ይሻላል፤ እኔ በበኩሌ አልስማማም ማለታቸው ጣልቃ የገባ ጉዳይ ሆኖ አነጋጋሪነቱ ሳይቀንስበት ቆይቷል። በተለይም ልክ የዛሬ ሳምንት ቪኦኤ ዜናውን ካሰማ በኋላ ስጋትም፣ ተስፋ መቁረጥም፣ ግራ መጋባትም ከብዙ የፌስቡክ አስተያየት ሰጪዎች ቃል የታየ ነበር ማለት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com