የአገራዊ ፓርቲዎች መመሥረት አዎንታዊ አንድምታ!

Views: 174

ከዘውጌነት ያተረፍነው ችግር ብቻ ነው የሚሉት መላኩ አዳል፤ ጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካው አሁን ላለንበት ምስቅልቅል ዋናው ምክንያት ነው ሲሉም ይተቻሉ። በተጓዳኝም አሃዳዊ እና ፌዴራላዊ ስርዓትን አነጻጽረው ያቀረቡ ሲሆን ፌዴራሊዝሙ እንዳለ ይቀጥል በሚሉ የዘውጌ ብሔርተኞች እና ፌዴራሊዝሙ መስተካከል አለበት በሚሉ የዜግነት/አንድነት ኃይሎች መካከል ስላለው ልዩነትና አንድነትም ነጥቦችን አንስተዋል። አገራዊ ፓርቲዎች መመሥረታቸውንም በበጎ ጎን ጠቅሰዋል።

የብዙዎቹ የ1960ዎቹ ወጣቶች ዓላማ ያደገች ኢትዮጵያን ማየት እንደነበረ እሙን ነው። ሆኖም የማርክስ ፍልስፍና ሳይገባቸውና ሌኒን እና ስታሊን ሶቬት ኅብረት ላይ ተግብረው አገር ያፈረሱበትን ሐሳብ በእኛ ማኅበረሰብ ተግባራዊ በማድረጋቸው ምክንያት ለሚታየው ችግር ዳርገውናል። የማርክስ ፍልስፍና በአደገ የካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ የሚከወን መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ባመዛኙ በገባር ስርዓትና ቅድመ ካፒታሊስት የነበረች መሆኗን ባለማስተዋላቸው ነው ይህን ስህተት የሠሩት። ላለፉት 29 ዓመታትም የትግራይ የገዥ መደብ የሆነው ወያኔ/ሕወሓት ይህን ሐሳብ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በመተግበር አገሪቱን ለትርምስ ዳርጓታል።

የኛ የኢትዮጵያውያን ዋናው ችግር የአንድን ሐሳብ ጠንካራና ደካማ ጎን ላይ በመነጋገር ሐሳቡ ችግር ካለበት የመተው ወይም የማሻሻል ሥራ አለመሥራታችን ነው። የዋለልኝ ሐሳብ ችግርም ይኸው ነው፤ ተቋማዊ አድሎ ነበር የሚለው ሐሳቡ ቅቡልነት ያገኘው ትክክል ሆኖ ሳይሆን የሐሳቡ ደጋፊዎች ወደ ሥልጣን በመምጣታቸው ነው። ይህም አገርን ወደብ አልቦ እንዲሁም በጣም ደካማ ሕገ መንግሥትና የጎሳ ፌዴራሊዝም እንዲኖረን አድርጓል፤ የዴሞክራሲያዊ መንግሥትና የብሔር ግንባታ ሒደትን አጓትቷል። የመሃሉን ፖለቲካ በመያዝ ቀስ በቀስ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመገንባት የሚካሔደው ሙከራ እንዳለ ሆኖ፣ የ2010ሩ ለውጥ መሠረታዊ ለውጥ እንዳያመጣ አሳስሮ ይዞታል።

‹‹አሃዳዊነትን ሊመልሱ ነው›› በምትለዋ ጉዳይ ደግሞ ትንሽ እንበል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ አገር እንገነጥላለን ከሚሉ ፓርቲዎች ውጭ ፌዴራሊዝምን የማይቀበል የፖለቲካ ፓርቲ የለም። በተለይ ከሽግግሩ ዘመን በኋላ ፌዴራሊዝም የፖለቲካ ልሂቃን የሚስማሙበት ሐሳብ ሆኗል። ይህ ማለት ግን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ያለውን ዘውጌ የቋንቋ የፌዴራል መዋቅር ይቀበላል ማለት አይደለም። ስለዚህ ትክክለኛው ክፍፍል ያለው ፌዴራሊዝሙ እንዳለ ይቀጥል በሚሉ የዘውጌ ብሔርተኞች እና ፌዴራሊዝሙ መስተካከል አለበት በሚሉ የዜግነት/አንድነት ኃይሎች መካከል ነው።

አንዳንድ የፌዴራሊስቶች ኀይሎች አሃዳዊ የመንግሥት ሥርዓትን መደገፍ እንደ የዘውጌ ማንነቶች መደፈቅን መደገፍና ተራማጅነትን ማጉደል አድርገው ይቆጥሩታል። የፌዴራል ሥርዓትን ከአሃዳዊ መንግሥት መምረጥ ከፓርላሜንታዊ ይልቅ ፕሬዝዳንታዊ፤ ከአብላጫ የምርጫ ሥርዓት ይልቅ ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ከመመርጥ የተለየ አይደለም። ኹለቱም ሥርዓቶች በብዙ መልኩ ሊተገበሩ የመቻላቸውን ያህል የራሳቸው የሆነ በድክመትም ሆነ በበጎ በኩል የሚጠቀስ ባህርይ አላቸውና።

የፌዴራል ሥርዓት ከአሃዳዊ መንግሥት የሚለይበት ዋናው ነጥብ ለክልል መንግሥታት በሚሰጠው ሥልጣን፣ አስተዳደር በሔደና በመጣ ቁጥር በማይቀይረው መልኩ ክልሎችንም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱን በሚገዛ ሕገ-መንግሥት የሚቀመጥ በመሆኑና ይህንንም ሕገ-መንግሥት የማሻሻል ሒደት ከሞላ ጎደል በፌዴራል መንግሥት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑ ነው። የዘውጌ ብዝኀነትን ከማስተናገድ ጋር በተያያዘም ቢሆን ፌዴራል መሆን ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ አድርጎ መውሰድ ተገቢ አይደለም፤ ፌዴራል አለመሆንም ከዚሁ የሚጣራስ አድርጎ መወሰድ እንዲሁ።

‹ባለፉት ኻያ ሰባት ዓመታት ፌዴራል ነኝ በምትለው ኢትዮጵያ በተፈጸሙ ሀጢያቶች ሁሉ ምክንያት ፌዴራሊዝሙ ነው› ማለት ትክክል ያልሆነውን ያህል፤ የተማከሉ የነበሩት የኢትዮጵያ ሥርዓቶች ዘውጌያዊ ብዝኀነትን በማስተናገድ ረገድ መውደቃቸው፣ በብዙ አገራት ተመራጭ የሆነውን አሃዳዊ የመንግሥት ሥርዓትን ያለ ግብሩ ሊያስወነጅለው አይገባም።

ሕገ መንግሥት የአንድን አገር ሉአላዊነት፣ የአገር ዳር-ድንበርና መለያን የሚያሳይ፣ የሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ስርጫትን የሚደነግግ፣ የዜጎችን መብትና ግዴታ የሚወስን፣ የአገር ሃብትና አጠቃቀምን በውል የሚያሳይ የአገሪቱን መንግሥት አደረጃጀትና አወቃቀር የሚደነግግ የሕጎች ሁሉ መሠረትና የበላይ ነው። በተለያዩ የመንግሥት አካላት የሚወጡ ሕጎች፣ አዋጆች፣ ድንጋጌዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መውጣት ያለባቸው ሕገ-መንግሥቱን መሠረት አድርገው ሳይቃረኑ መሆኑ ግዴታ ነው። ስለዚህም ከፍተኛ ጥናትና የሕዝብን ተሳትፎ የሚጠይቅን ሕገ መንግሥት ያህል ነገር በፖለቲካዊ ውሳኔ ብቻ ያለ ሙሉ ሕዝብ ተሳትፎ ማርቀቅና ማጽደቅ ስህተትና ለአገራችንም የማይበጅ አካሔድ ነበር።

በተጨማሪም ብሔር፤ በታሪክ ውቅር የጋራ ድንበር የገነቡ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ተመሳስሎ የሚንጸባረቅባቸው፣ የሰከነ ባህል የሚንጸባረቅባቸው የማኅበራዊ ቡድኖች የመገለጫ ሐሳብ ነው። ይህ ግን በኢትዮጵያችን ገና እውን ያልሆነ ሐሳባዊ ቡድን ነው። በኢትዮጵያ የሀገረ ብሔር ግንባታው እስከ 1983 የተጓተተው፣ እውቀትና የሃብት ባለመኖሩ፣ በኋላም ሥልጣንን ወደ ራስ የማማከል ሂደት በማየሉ፣ ይህንም ተከትሎ ፍትኀዊ የሃብት ክፍፍል (መሬት፣ ግብር ወዘተ)፣ ጥሩ የትምህርትና የቋንቋ ፖሊሲ፣ ሌሎችም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እውን ባለመሆናቸው ነው። ይህን የሀገረ ብሔር ግንባታ የኢሕአዴግ መንግሥት ማሳደግ አይደለም በጣም በብዙ ወደኋላ በመጎተት አገራዊ ማንነትና መተማመን እንዲጠፋ አድርጓል።

በኢትዮጵያችን ያለው ማንነት የብሔር ብቻ ይመስል ሕገ መንግሥቱን፣ አስተዳደራዊ መዋቅሩን፣ ፖለቲካውን፣ የትምህርት ስርዓቱን ወዘተ በብሔርና ብሔር ብቻ እንዲቃኝ መደረጉ የህወሓትና የኦነግ ጥፋት ነው። አገራዊ አንድነታችን ያደከመው፣ የሕዝብ ግጭትና መፈናቀል ያስከተለው፣ የጋራ እሴቶቻችንን ያዳክመውና እንዳናበለጽግ እንቅፋት የሆነው፣ የጋራ ማንነትን አኮስሶ ዘውጋዊ ማንነትን ያገነነው፣ ለዜጎች ሕይወት ህልፈት፣ ልዩነት የሚያባብሰው የብሔርተኝነት መዋቅርና ሕገ-መንግሥቱ ምክንያት ነው። የግልና የቡድን መብቶችን አጣጥሞ ማስከበር የሚችል ፌዴራሊዝም ለአገር አንድነትም ለዘላቂ ልማትም ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የኛ ፌዴራሊዝም ድክመት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተሰጠው ቡድን ውስጥ ያሉ የቡድኑ አባል ያልሆኑ ዜጎችን ውክልናና ሥልጣን ነፍጎ ኹለተኛ ዜጋ እንዲሆኑ ማስገደዱ ነው።

የዜጎች መብት ከዜግነት የሚመነጭ ቢሆንም የየክልሎች ሕገ-መንግሥቶች ግን ሕዝብን ነባርና መጤ ብለው የሚከፍሉ፣ ነባር ለሚሏቸው የክልሉ መሬትም ሆነ ሀብት ላይ ሌላው ዜጋ የሌለውን የልዩ ባለቤትነት መብት የሚሰጡ ናቸው። የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ሕዝብ በመረጠው ከንቲባ ለመተዳደር አለመቻልም በዚሁ ምክንያት ነው። ስለዚህም በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ፊዴራሊዝም አብረው የነበሩትን ተጠቅሚነትን በማረጋገጥ አብሮ የማዝለቅን (holding together) ዓላማ ይዞ ነው። ነገር ግን መሬት ላይ የታየው ለፌዴራሊዝም ወሳኝ የሆኑት ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ያልታዩበት ስርአት ነው። ለዚህም ከዴሞክራሲና ተቋማት ግንባታ በተጨማሪ መግባባት፣ መተማመን፣ ሕግ አክባሪነት፣ የፖለቲካ ባህልን ማሳደግ፣ የሃብት ክፍፍል ፍትኀዊነት ላይ ሊሠራ ይገባል።

የኢትዮጵያ የዘውጌ ፌዴራሊዝም ብዙ ችግሮች አሉበት። ማንነት ከመደብ፣ ከዜግነት፣ ከሃይማኖት፣ ከጾታ ወዘተ ማንነት ጎልቶ መውጣቱ እነዚህን ማንነቶች አቀጭጯል፤ የቤተሰቦችና የጥቅመኞች መንግሥት እንዲመሠረት፤ ፖለቲካዊ አሠራሩ ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ ሁኔታ ከላይ ወደ ታች እንዲሆን፤ ሕዳጣንን ከሥልጣን እንዲርቁ፤ በየክልሉ የሚገኙ ዜጎችን ኹለተኛ ዜጋ አንዲባሉ አድርጓል። እንዲሁም በልዩ ዞን መንገድ ለመፍታት የተኬደበትም መንገድ በቂ ሆኖ አልተገኘም፤ የዘውግ አደረጃጀቱ ግጭቶች እንዲሰፉ፣ የጋራ ኢትዮጵያዊ ማንነትና ርእዮት እንዳይኖረን፤ የታሪክ አረዳድ እንዲዛባና የሐሰት ትርክቶች እንዲበዙ አድርጓል።

አንድ ማኅበረሰብ የለማ እንዲሆን በመጀመሪያ ፖለቲካው መስተካከል አለበት። የፖለቲካው መስተካከል የኢኮኖሚውንና የማኅበራዊ እድገቱን ለማምጣት ተጨማሪ መድኅን ይሆናል። ስለዚህም የፖለቲካ ልኂቃን ለአገር የሚበጀውን ሊመርጡ ይገባል። በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ተግባር ላይ ውሏል ቢባልም እውነታው ግን በወያኔ ብቻ የሚመራ አስተዳደር ነበር የነበረው። ይህም ራስን የማስተዳደሩን ተግባርና መብት ፉርሽ አድርጎታል። በማንነት ብቻ በመመሥረቱም አገራዊ ራእይ እንዳይኖረን አድርጓል።

ስለዚህ የፌዴራል አስተዳደር የኢትዮጵያን ብዝኀነት ለማስተናገድ ተመራጭ የአስተዳደር መዋቅር እንደሆነ አምነን፣ ነገር ግን ይህ ዘውግን መሰረት ያደረግ አከላለልና ሕገ መንግሥቱ ጥናትን መሰረት ባደረገ መንገድ መስተካከል እንዳለበት መተማመን አለብን። ለአስተዳደር መሰናክል፣ ለግጭትም መሰረት ሆኗልና። የዘውግ ፖለቲከኞች ግን ይህን ማመን አይፈልጉም። ለዚህም የጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲዎች መመስረት ወሳኝ ነው። በዚህ በኩል የኢዜማ መመሥረትና የኢሕአዴግ ወጥ ብልጽግና ፓርቲ መዋሐድ ጥሩ ነው።

የኢሕአዴግን ወጥ የብልጽግና ፓርቲ የመሆን ሒደትን ተከትሎ የተለያዩ ሐሳቦች ሲቀርቡ ይሰማል። አንዱ ጉዳይ የአዲሱ ፓርቲ ውህደት አሃዳዊነት ያሰፍናል፣ ብሔረሰቦችን ይጨፈልቃል የሚል ነው። ይህ አባባል ለ27 ዓመታት የተነዛውን የጥላቻ ፖለቲካ ከማስቀጠል የዘለለ ምንም እውነትነት የለውም። በረጅም ጊዜም የፌዴራል አስተዳደርን ከማስተካከልና ሕገ መንግሥቱን ከማሻሻል የዘለለ የሚከወን ተግባር አይኖርም። ይህ ሐሳብ አላዋጣ ሲል ደግሞ ውህደቱ አዲስ ፓርቲ መመሥረት ስለሆነ ውህደት አይደለም። ስለዚህም ሕገ ወጥ ነው ይላሉ። ይህም የግንባሩ መሥራች የነበሩ ፓርቲዎች ከግንባሩ መውጣትም፣ ውህድ ፓርቲ መፍጠርም መብታቸው ነው። እናም ሕጋዊ ያልሆነ ነገር የለውም። ይህም ውህዱ ፓርቲ ከኢሕአዴግ ፕሮግራም የሚወስደውን መውሰድ፣ የሚቀይረውንም የመቀየር መብት ይሰጠዋል።

የብልጽግናን መመሥረትን ተከትሎ የአንድነት ኀይል መጣብህ ሰበካ እጅግ ተጧጡፋል። የዚህም ዋናው ምክንያት የዘውግ ፖለቲካን ወደ ፌዴራል ሥልጣን የመምጣት እድል እንደሚዘጋ ስላወቁ ነው። ይህም ፖለቲካውን ወደ መሀል በመሳብ የአገራችንን ፖለቲካ ከጊዜ ጋር ያስተካክላል ብለን እንጠብቃለን። በረጅም ጊዜም የዘውግ ፖለቲካውን በማዳከም አገራዊ ፓርቲዎችን የሚያጠነክርና በየቦታው ተበትነው የሚገኙትንም ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው የሚያስከብር ስርአት ለመገንባት መሰረት እንደሚሆን እሙን ነው።

ለአጭር ጊዜ ግን የዘውግ ፓርቲዎች የፌዴራል ምርጫን የማሸነፍ እድል ባይኖራቸውም የክልል ምርጫዎችን የማሸነፍ እድል ሊኖራቸው ስለሚችል፣ የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታ በተሻለ ግንኙነት ሊሠሩ የሚችሉበት መንገድ መታሰብ አለበት። ይህም የሚያሳየን ሕዝብ ድምጽ ሲሰጥ እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ባደረገ መንገድ መሆን እንዳለበት ነው። በተጨማሪም ለተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ ተወካዮች የምልመላ ጉዳይና የምርጫ ወረዳ አደረጃጀት የሕዝብን የመወከል መብት ባረጋገጠ መልኩ መሆን አለበት።

ሕገ-መንግሥት፣ መንግሥትና ሕጎች ያስፈለጉበት ምክንያት የሰው ራስ ወዳድነት ነው። የዘር ፖለቲካና የዘውጌ ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ህልውናና በዜጎች የትም የመኖር መብት ላይ ችግር አስከትሏል ይስተካከል እንጂ፣ ዘውጌ ብሔርተኞች እንደሚሉት የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር ይፍረስ ያለ የለም። የፓለቲካ ፓርቲ መሰረቱን በቋንቋ ላይ ካደረገ ከእውቀት የፀዳ ርዕዮት አልባ ተከታዮቹን ወደ ጨለማ ገደል የሚመራ ነው። የብሔር ፖለቲካ የማይታረም አስቀያሚና አስከፊ ባህርዩ ነጻነትን፣ እኩልነትን፣ ፍትኅን እና የሕግ ልዕልናን በመሠረታዊነት እወክለዋለሁ ከሚለው ብሔር ጥቅም አንጻር ብቻ ማየቱ ነው።

ከዘውጌነት ያተረፍነው ረሃብን፣ ስደትን፣ ወደብ ማጣትን፣ ሙስናን፣ የሞራል ውድቀትን፣ የጋራ ርዕዮት ማጣትን፣ ዘረኝነትንና ግላዊ ስግብግብነትን ነው። ጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካ አሁን ላለንበት ምስቅልቅል ዋናው ምክንያት ነውናም ሊስተካካል ይገባል። ለሁሉም መፍትሄው ያለው የሕገ መንግሥት፣ የመዋቅርና የስርአት ለውጥ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ከገባችበት አጣብቂኝ እንድትወጣ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል፣ በዘውግ የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋምን በሕግ በመከልከል፣ በዘር የተማከለውን የክልል ፌዴራሊዝም በማስተካከል ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች በርዕዮተ-ዓለም መሠረት በማዋሃድ ለቀጠይ አገር ደኅንነት መሥራት ይኖርብናል። የፖለቲካ ድርጅቶች የብሔራዊ ቅርጽ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። በኢዜማና በብልጽግናም ያየነው ጥሩ ጅምር ነው። በብሔር እና በቋንቋ ላይ መሰረት ያላደረጉ፣ የርዕዮት መሰረት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መመሠረትና ከዘርና ቋንቋ በተጨማሪ የሕዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት ተመጣጣኝነት፣ የመልክዓ-ምድር አቀማመጥና አሰፋፈርን፣ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን፣ የአስተዳደርና የልማት አመቺነትን፣ የአኗኗር ዘይቤን፣ የታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ሥነ ልቦናና የባህል ትስስርን ያካተተ የፌዴራል አወቃቀር እውን መሆን የችግሮቻችን መፍትሔ ነው። የብሔር የፓለቲካ ፓርቲዎች የሲቪክ ማኅበር ብቻ ሆነው የብሔራቸውን መብት ያስጠብቁ፣ ሕዝብ በቀጥታ የመከረበት እና ድምፅ የሰጠበት ሕገ መንግሥት እንዲረቅም ማድረግ ያስፈልጋል።

መንግሥትም አራቱን መሠረታዊ የመንግሥት ግዴታወች ማለትም 1) ሕግና ስርአትን ማክበርና ማስከበር፤ ብሎም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ 2) የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ 3) ዜጎች አገራቸውን “አገራችን” ብለው ይጠሩ ዘንድ የዜግነት ስሜትን እንዲፈጥሩና እንዲያዳብሩ ማድረግና 4) መሠረተ ልማትን ማስፋፋትና አገራዊ ሀብትን በፍትኀዊነትና በእኩልነት ተመሥርቶ ለዜጎች እንዲደርስ ማድረግ ይኖርበታል።

የጋራ ርዕዮት እስከሌለን ድረስ በ137 ፖርቲ በጎጥ ተደራጅተን መባላታችን የማይቀር ነው። የሁሉም ችግራችን መንስኤ ድንቁርና፣ ኋላ ቀርነት፣ ደካማ ባህል ብሎም እሱን ተከትሎ የመጣው የልኂቃን ጠባብ የሆነ የዘር ፖለቲካና የዘር ፌዴራሊዝም ነው። የምንመኘውን ዴሞክራሲና የበለፀገች አገር ለመገንባት በዕውቀት የሚያምን፣ ዴሞክራሲን መሸከም የሚችል ባህል እንዲኖረን ያስፈልጋል።

በተጨማሪም በጠቅላላው የትምህርት ጥራት መውረድ፣ በተለይም የመምህራን ጥራትና የሞራል መውረድ፣ ከቀደመው የጉልት ስርዓት አስተሳሰብ አለመውጣታችን ከምንመኘው ለመድረስ እንቅፋት እየሆነብን ነው። ለዚህም ጥሩ የሆነ የትምህርት ስርአት እንዲኖረን በማድረግና የማንበብ ባህልን ለማሳደግ መሥራት ይኖርብናል። ከድንቁርና እና ከደካማ ባህል የመውጫ መንገዱም ይኸው ነውና።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው።
በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com