ባለፉት ሦስት ወራት ለሴቶች ከ 800 ሺሕ ብር በላይ ብድር መሰጠቱ ተገለፀ

Views: 344

ባለፉት ሦስት ወራት 3 ሺሕ 317 ሴቶች 140 ሺሕ 872 ብር እንዲቆጥቡ መደረጉን እና 250 ሺሕ 817 ሴቶች 891 ሺሕ 569 ብር በረጅምና በአጭር ጊዜ የሚከፈል ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያከናወናቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ተከትሎ 195 ሺሕ 241 ሴቶች በጥቃቅንና አነስተኛ፣ 166 ሺሕ 283 በራስ አገዝ እና 83 ሺሕ 889 በኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ ተገልጿል።

እንዲሁም 269 ሺሕ 552 በግብርና እና 2 ሺሕ 341 በገጠር ከግብርና ሥራ ውጭ ባሉ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የኑሮ ደረጃቸውን እንዲያሻሻሉ ለማድረግ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪም ለ969 ሴቶች የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ በማዘጋጀት እንዲሁም ለ1 ሺሕ 837 ሴቶች የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው በማድረግ ያለባቸውን የመሥሪያ ቦታ እና የገበያ ትስስር ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርተዋል።

በገጠር የሚኖሩ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ዐቅም ለማሳደግ 1 ሺሕ 220 ሴቶች ተደራጅተው ሥልጠና እንዲሰጣቸው በማድረግና ለእያንዳንዳቸው ከ4 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ብር የመነሻ ብድር በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ እንደተቻለም ተገልጿል።

የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት ለማሳደግ በሴቶች ትምህርት ተሳትፎ እና ተግባር ተኮር ፕሮግራሞች ዙሪያ 793 ሺሕ 848 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት 361 ሺሕ 141 ሴቶች የተግባር ተኮር ትምህርት እንዲከታተሉና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆቻቸውንም ወደ ትምህርት እንዲልኩ ማድረግ መቻሉን መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የሴቶችን ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንጻር እኩል ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የእናቶች ሞት ምጣኔን በመቀነስ ረገድም እንደዚሁ በአመጋገብና ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ለ575 ሺሕ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ ሴቶች ትምህርት በመስጠት ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com