ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኅዳር 23/2012

Views: 148

1-በሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ና የፀጥታ ኃይሎች ግድያ የተጠረጠሩ 55 ግለሰቦች ላይ ዛሬ ኅዳር 23/2012 የክስ ማመልከቻ መደመጥ ጀምሯል። በነሻምበል መማር ጌትነት መዝገብ ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት ከሚገኙት መካከል 14 ተጠርጣሪዎች በማደራጀት፣ በመምራት የክልሉን ከፍተኛ ባለስልጣናትና የፖሊስ አባላትን በመግደልና በማቁሰል ተሳታፊ መሆናቸውን የሚያመለክት ክስ ተነብቦላቸዋል።አብዛኛዎቹ ወጣቶች ሲሆኑ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እንደነበሩም በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል።(ዶቼቬሌ)

……………………………………………………………………….

2-የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ላይ የሚያገለግል ገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ።አገልግሎቱ ዘመናዊ በሆነው የብሮድባንድ ኢንተርኔት መተግበሪያ “ኬ ባንድ” የሚሰራ ሲሆን የገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎቱ ለጊዜው የተጀመረው በ10 ኤርባስ 350 አውሮፕላኖች ላይ መሆኑ ታውቋል።ተጓዦች አገልግሎቱን በጥሬ ገንዘብ፣ በኦንላይን ክሬዲት ካርድና በሼባ ማይልስ እንዲሁም በቦሌና በሌሎች ቦታዎች ከሚገኙ የአየር መንገዱ የመንገደኞች አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ወይም በጉዞ ላይ ከበረራ አስተናጋጆች መግዛት እንደሚችሉ አየርመንገዱ ገልጿል።(ኤዜአ)

……………………………………………………………………….

3-የኢትዮጵያ መንግስት ለውጭ አገር ባለሀብቶች የአገር ውስጥ የባንክ እና የኢንሹራንስ ገበያው ላይ እንዲሳተፉ ፈቃድ ለመስጠት ዕቅድ እንደሌለው የገለፀ ሲሆን፤ በሌሎች የኢንቨስመንት ሰራዎች ላይ ግን መሳተፍ እንደሚችሉ አሰታዉቋል።(ሮይተርስ)

……………………………………………………………………….

4–በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ በምዕራብ ጉጂ ሱሮ ባርጉዳ የተገነባው የኢፈ ቱላ ሱሮ ብርሀን ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ትምህርት እየተሰጠበት  እንደሚገኝ የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቋል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

……………………………………………………………………….

5-የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ኢትዮጵያውያን በኬንያ የአገራቸውን ያህል ሠርተው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ መንግሥታቸው እንደሚሠራ ገለጹ።(ኢቢሲ)

……………………………………………………………………….

6-የዲላ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ያለበትን የሕክምና መስጫ ቦታ ችግር ለመቅረፍ በ894 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።ሆስፒታሉ የጌዴኦ ዞንን ጨምሮ ለሲዳማ ዞን አጎራባች ወረዳዎች፣ ለአማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች፣ ኦሮሚያ ክልል ጉጂና ቦረና ዞኖች ለሚኖሩ ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።የግንባታው አፈጻጸምም 84 ነጥብ 6 በመቶ የደረሰ ሲሆን  በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የሆስፒታሉ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የቦርድ ሰባሳቢ ዶክተር ዮናስ ሰንደባ ተናግረዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

……………………………………………………………………….

7-በሐዋሳ ከተማ በሚገኙ ጤና ተቋማት ውስጥ የሚስተዋለው የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት መፍጠሩ ተገለፀ።ችግሩ የተፈጠረው ከዓመታት በፊት የተከፈለባቸው የሕክምና ቁሳቁሶች እና መድሃኒቶች ሐዋሳ በሚገኘው የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ቅርንጫፍ ባለመድረሱ እና በተለያየ ጊዜ የተጠየቁት የመድሃኒት አይነቶች በሚፈለገው ደረጃ እና ጊዜ አለማግኘት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር መሆኑን የከተማው ጤና መምሪያ ኃላፊ ቡሪሶ ቡልዓሾ ተናግረዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

………………………………………………………………………

8-ኢትዮጵያ በመጪው ቅዳሜ በሚጀመረው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር /ሴካፋ/ እንደማትሳተፍ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።ኢትዮጵያ ከሕዳር 27 እስከ ታህሳስ 9/2012  በዩጋንዳ በሚካሄደው ውድድር እንድትሳተፍ የምድብ ድልድል ውስጥ  ብትካተትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከውድድሩ ከሚገኘው ጥቅምና ከሚወጣበት ወጪ አንጻር መሳተፉ አስፈላጊ አይደልም ብሏል።(ኢቢሲ)

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com