የጊዮን ሆቴሎች የስብሰባ አዳራሽ ጣራ ድንገተኛ መፍረስ አጋጠመው

Views: 281

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የጊዮን ሆቴሎች የስብሰባ አዳራሽ ዛሬ ኅዳር 23/2012 ከሰዓት በኃላ ጣራው ሙሉ በሙሉ የመፍረስ አደጋ አጋጥሞታል። አዲስ ማለዳ በስፍራው ተገኝታ ማረጋገጥ እንደቻለችው የስብሰባ አዳራሹ ጣራ ሙሉ በሙሉ በድንገት የፈረሰ ሲሆን በአንዲት የሆቴሉ ሰራተኛ ላይም ቀላል ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

ሆቴሉ ረጅም ዕድሜ ከማገልገሉ ጋር ተያይዞ የስብሰባ አዳራሹም ከቀለም መቀባትና እና መለስተኛ ዕድሳት ከማድረግ ባለፈ አስፈላጊውን ዕድሳት ለረጅም ጊዜያት ሳይደረግለት በመቆየቱ ለድንገተኛ መፍረስ እንደተዳረገ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሆቴሉ ሰራተኞች ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪዎች ለአዲስ ማለዳ ጨምረው እንደገለፁት የስብሰባ አዳራሹ በዋነኛነት ለሆቴሉ ገቢ ከሚያስገቡ የአገልግት አይነቶች ግንባር ቀደም እንደሆነና ተገቢውን ክብካቤ አለመደረጉም ተገቢ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

በቀን አንድ እና ከዛ በላይ ስብሰባዎችን እንዲሁም አንዳንዴም ሰርገኞችን የሚያስተናግደው አዳራሹ ዛሬን ሲቀር ትናንት ኅዳር 22/2012 ቀኑን ሙሉ ስብሰባ ሲካሔድበት እንደቆየ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዛሬም ስብሰባ እየተካሔደበት ቢሆን ኖሮ የሚደርሰው ጉዳት እጅግ የከፋ ይሆን እንደነበር አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com