ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኅዳር 22/2012

Views: 460

1- ባለፈው ክረምት በአዲስ አበባ ከተተከሉት 6 ሚሊዮን ችግኞች መካከል 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወይም 20 በመቶው አለመፅደቃቸውን የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ እና የአረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን አስታወቀ።ችግኞቹ ያልፀደቁበት ምክንያት የጥራት ችግር እና የእንክብካቤ እጥረት መሆኑን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዋለልኝ ደሳለኝ ገልጸዋል ።(ኢቢሲ)
……………………………………………………………………………
2-የጀርመን መንግስት ለኢትዮጵያ የ352 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ።ከገንዘብ ድጋፉም 110 ሚሊዮን ዩሮ በቀጥታ ለመንግስት በጀት ድጋፍ የሚውል መሆኑም ታውቋል።ስምምነቱን እውን ለማድረግ የኹለትዮሽ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ጀርመን በኢትዮጵያ የለውጥ አጋርነትን እንዲሁም ቀጣይ የትብብር ማዕቀፍን ለማስቀጠል 352 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ የለገሰችበትን ስምምነት አፈራርመዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)
……………………………………………………………………………
3-የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ4ኛ የወንጀል ችሎት የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በነበሩት በአብዲ ሙሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) የክስ መዝገብ ክስ በተመለከተው 47 ግለሰቦች ላይ ከጥር 14/2012 ጀምሮ የዓቃቤ ሕግን ምስክር መስማት ሊጀምር መሆኑ ታውቋል።ዓቃቤ ሕግ በሁሉም ተከሳሾች በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብሔርን ከብሔር በማጋጨት፣ ግድያና ሌሎች ወንጀሎችን በመጥቀስ 11 ክሶች መስርቷል።(ኢቢሲ)
……………………………………………………………………………
4-የአፍሪካን የሕዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂን ለማሳደግ አፍሪካውያን በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ።ስምንተኛው የአፍሪካ የሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አመራርነት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን አሜሪካ ፣ሩስያ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና የበጀታቸውን ከ0.1 እስከ 0.23 በመቶ ለሕዋ ሳይንስ ኢንደስትሪ እንደሚያወጡ የተናገሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) የአፍሪካ አገራት የበጀታቸውን 0.005 ከመቶ ለዘርፉ እንዲያውሉ የሚጠይቀውን የእስቴዛ ስምምነትን እንዲተገብሩ ጠይቀዋል።(አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………………………
5-የኦሮሞ ፖለቲካ አቀንቃኝ ጀዋር መሐመድ በቅርቡ በሚደረገው ምርጫ እንዴት እንደሚወዳደር እንዳልወሰነ አስታወቀ። ጀዋር ለዶቼቬለ እንዳለው ፓርቲ መስርቶ ወይም ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ ስለመወዳደር ከአመራሮቹ ጋር ተወያይቶ ይወስናል።(ዶቼቬለ)
……………………………………………………………………………
6-የደብረታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል ከደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ የመጀመሪያ የሆነዉን የሱስ ማገገሚያ ማዕከል አስገንብቶ አስመረቀ።የማዕከሉ የክልል ጤና ቢሮ ተወካይ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ጊዎን ሆስፒታል የመጡ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።(ዋልታ)
……………………………………………………………………………
7-በሐዋሳ ከተማ የዘመናዊ የገበያ ማዕከል የግንባታ ስራ በይፋ ተጀመረ ።ላለፉት ስምንት ዓመታት በሐዋሳ ከተማ በሳውዘርንጌት ኢንቨስትመንት አክሲዮን ማኅበር ሊገነባ ታስቦ በልዩ ልዩ ምክንያት ሲጓተት የቆየው ዘመናዊ የገበያ ማዕከልና የቢሮዎች ሕንጻ ኮምፕሌክስ ፕሮጀክት የግንባታ ስራ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እና የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የፕሮጀክቱ ተወካዮች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።ፕሮጀክቱ 176 የአክሲዮን ማኅበር አባላት የተቋቋመና በ10 ሺሕ ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን ወደ 600 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘለት መሆኑ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
……………………………………………………………………………
8-የኢፌዴሪ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት በሽታውን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እየሰራ ያለው ስራ መቀዛቀዝ በማሳየቱ በሽታውን የመቆጣጠሩ ስራ አዝጋሚ እንደሆነ አስታወቀ።በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ የስርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 91 በመቶ ሲሆን ከ649 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝ የ2019 አገራዊ የኤች አይ ቪ ስርጭት ያሳያል።የስርጭት ምጣኔውም ከክልል ክልል የሚለያይ ሲሆን በሽታው በጋምቤላ፣ አዲስ አበባና ትግራይ የስርጭት መጠኑ ወረርሽኝ በሚያስብል ደረጃ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዳንኤል በትረ ገልጸዋል።(ኢዜአ)
……………………………………………………………………………
9-በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመናገር ነጻነት ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ካዬ በኢትዮጵያ ዛሬ ጨምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው።በጉብኝታቸውም ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።የተመድ የመናገር ነጻነት ልዩ መልዕክተኛ ከፈረንጆቹ 2006 በኋላ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርግ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።(ፋና ብሮድካስቲንግ)
……………………………………………………………………………
10-በኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሚንስትር ለማ መገርሳ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ እና የአሜሪካንን የሁለትዮሽ የመከላከያ ትብብር ለማጠናከር ዋሽንግተን ዲ.ሲ. ገብተዋል። (አዲስ ማለዳ)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com