በ 300 ሚሊዮን ብር የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ሊገነቡ ነው

Views: 390

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 12 ገጠራማ እና ከዋና የኤሌክትሪክ መስመሮች ርቀው የሚገኙ ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩን እና በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገለፀ።

ፕሮጀክቶቹ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ክልሎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ ከብሔራዊ የኃይል ማሰራጫዎች ርቀው ለሚኖሩ 68 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች ኃይል የማቅረብ አቅም ይኖራቸዋል።

ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እና በአገልግሎቱ ወጪ የሚገነባ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ 300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረግበታል። ግንባታውን ለማከናወን የወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ያሸነፉ ሦስት የቻይና እና አንድ የስፔን ኩባንያዎች ጋር የውል ስምምነት መፈፀሙንም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጥላሁን ለገሰ አስታውሰዋል።

ከአምስት ዓመታት በኋላ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማዳረስ የተያዘው ግብ አካል የሆነው ፕሮጀክቱ፣ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ በዘርፉ ልምድ ካላቸው አገራት የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና በአገር ውስጥ ያለውን የዕውቀት ክፍተት ለመድፈን እንደሚጠቅምም ተገልጿል።

የአገር ውስጥ ድርጅቶችን ከማሳተፍ አንፃርም አብዛኛዎቹ ልምድ የሌላቸው በመሆናቸው ለሥራው ዓለም ዐቀፋዊ ድርጅቶች ተመርጠዋል የተባለ ሲሆን፣ በቀጣይ በሚኖሩ ፕሮጀክቶች ላይ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጪዎቹ ጋር በጥምረት የሚሠሩበትን መንገድ ለማመቻቸት እንደሚሠራ ጥላሁን ጠቅሰዋል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ በታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረት እንዲደረግ ምክንያት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ በቀጣይም በመሰል አካባቢዎች የሚገነቡ የኃይል ማመንጫ መሰረተ ልማቶች በአካባቢው ያለውን ታዳሽ የተፈጥሮ ሀብት መሰረት ያደረጉ ይሆናሉ።

የምጣኔ ሀብት አማካሪ ጌታቸው ተ/ማርያም በበኩላቸው፣ የግሉ ዘርፍ በእንደዚህ ዓይነት ሥራዎች ላይ በበቂ ሁኔታ የተደራጀ አለመሆኑ እና ለግንባታ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ ከውጪ የሚገቡ በመሆናቸው ከአገር ውስጥ ምርቶች ይልቅ ከውጪ በሚመጡት ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ያስረዳሉ።

መስመሮችን ለመዘርጋትም ሆነ ጥገናዎችን ለማድረግ የሠለጠነ የሰው ኃይል በሚፈለገው ልክ አለመኖሩ፣ የትምህርት ስርዓቱ ለእነዚህ ቴክኖሎጂዎች በቂ ሥልጠና የማይሰጥ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ጉዳዩን አስቸጋሪ አድርጎታል፤ እንደ ጌታቸው እይታ። ፕሮጀክቶቹ በተበታተነ መልኩ በተለያዩ አካላት የሚተገበሩ መሆናቸው እና የሚያስተባብረው አካል ትንሽ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዳያመጣ እንቅፋት ይሆናልም ብለዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው በበኩላቸው፣ በአገሪቱ በዘርፉ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የተማሩ ምኁራን ቢኖሩም በተግባር የተደገፉ ሥራዎች ላይ ክፍተት እንዳለ ገልፀው፤ አሁን የግንባታ ውሉን የፈፀሙ ድርጅቶች ለአገልግሎቱ ባለሙያዎች የእውቀት ሽግግር ሥልጠናዎች እንዲሰጡ በማድረግ ላይ ነን ሲሉ ገልፀዋል።

አክለውም በአገር ውስጥ የሥራ እድል ለመፍጠር እና በቀጣይ ለሚገነቡ መሰል ፕሮጀክቶች የጥገና እና መሰል ሥራዎችን የሚያከናውኑ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከስምምነት ላይ መደረሱን ሥራ አስፈፃሚው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአገራችን 56 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኝ ሲሆን፣ እስከ አሁንም ታዳሽ ኃይልን መሰረት ባደረጉ ሥራዎች 11 ከመቶ ለሚሆኑ ዜጎች ኤሌክትሪክ ማቅረብ ተችሏል። ከ44 በመቶ የኤሌክትሪክ ሽፋን ውስጥም እስከ 33 በመቶ የሚደርሰውን የኃይል ፍላጎት በዋና የኤሌክትሪክ ቋቶች በማሟላት ላይ ይገኛል።

በቀጣይም በሁሉም ክልሎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው በሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎች 25 ፕሮጀክቶችን ለማከናወን በዝግጅት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ120 ሺሕ በላይ ዜጎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com