የአማራ የስለላ እና ደኅንነት ድርጅት በሚል የተቋቋመ ሕገ ወጥ የስለላ ቡድን ነበር ተባለ

Views: 1252

ባሳለፍነው ሳምንት ኅዳር 12/ 2012 በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ከ ሰኔ 15/2011 ጥቃት ጋር ተያይዞ ከተከሰሱት 13 ግለሰቦች ውስጥ ዘጠኝ ተከሳሾች ከክልሉ መደበኛ የፀጥታ መዋቅር ውጪ የአማራ የስለላ እና ደኅንነት ድርጅት (አሳድ) በሚል ቡድን በማቋቋማቸው ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ በዚህ መዋቅር ጠላት ተብለው የተፈረጁ ኀይሎች በተለይም ህወሐት እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲን ለመሰለል እና በአስፈላጊው ወቅት መንግሥትን በማዳከም የኀይል እርምጃ ለመውሰድ የስለላ እና መረጃ ደኅንነት ሥልጠና ወስደው ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎችን ያቀፈ እንደነበር ያስረዳል።

በተለይም ኹለተኛ ተከሳሽ አስጠራው ከበደ የተባሉት ግለሰብ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ውስጥ የስለላ መዋቅሩን ለመገንባት ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ይህንን ተቋም ገንብተዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ግለሰቡ፣ በተቋሙ ውስጥ ከሠለጠኑት 100 ግለሰቦች ጋር በመሆን የአማራ ልዩ ኀይልን ልብስ በመልበስ ወደ ከሚሴ በመሔድ ጥቃት ሰንዝረዋል በሚልም ክስ ቀርቦባቸዋል።

በተመሳሳይም ተከሳሹ ሚያዝያ 22/2011 ከጎጃም እና ከጎንደር የተሰባሰቡ ግለሰቦች መተከል ገብተው በንፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ በማሰብ ከተለያየ አካባቢዎች ትጥቅ እና ጥይት አመቻችተዋል በሚል ዐቃቤ ሕግ ክሱን አስነብቧል።

በክስ መዝገቡ በወንጀሉ ላይ በቀጥታ ተሳትፈዋል የተባሉ 13 ተጠርጣሪዎች የተካተቱበት ሲሆን፣ ተከሳሾቹ በኀይል፣ በአድማ እና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የአማራ ክልልን እና የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ለመለወጥ በማሰብ ከሚያዚያ ወር 2011 ጀምሮ ባሉት ጊዜያት በአማራ ክልልዊ ብሔራዊ መንግሥት ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ውስጥ ‹‹የፀጥታ ኦፊሰር ሥልጠና›› በሚል ሽፋን አባላትን በመመልምል በመንግሥት ላይ በስውር የጦርነት ስልት ሳቦ ታጆ፣ የሥነ ልቦና ጦርነት፣ ኢኮኖሚያዊ ጦርነት በማካሔድ መፈንቅለ መንግሥት ለማከናወን ሞክረዋል የሚል ነው።

ሠልጣኞቹንም በአማራ ክልል ዞኖች በቤኒሻንጉል እና በአዲስ አባባ አስታጥቆ በመመደብ መንግሥትን በኀይል ለማስወገድ ሞክረዋል የሚለው የክስ መዝገቡ፣ ተከሳሾቹ በግል እና በቡድን በሚጠቀሙባችው የማኅበራዊ ሚዲያዎች ሕዝቡ በክልሉ መንግሥት ላይም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ በማድረግ በተለይም በአማራ ክልላዊ መንግሥት ተቋማት እና አመራሮች ላይ ጥቃት ሲፈፀም የፌዴራል መንግሥቱ መከላከል እንዳይችል አገር መከላከያ ሠራዊትን ዒላማ በማድረግ፣ አመራሮችን በመግደል፣ ሠራዊቱን በመበተን የሚፈፀመውን ጥቃት መከላከል እንዳይችል ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን የክስ መዝገቡ ይገልፃል።

የክስ መዝገቡ ሰኔ 15 ቀን 2011 በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቀድሞው የክልሉ የሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኀላፊ ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በተመራው ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በኀይል የማፍረስ ተግባር፤ የክልሉን ፕሬዝዳንት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ የክልሉ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ ምግባሩ ከበደ፣ የክልሉ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ እዘዝ ዋሴን በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ጄኔራል ሰዓረ መኮንንን፣ የመከላከያ ሠራዊት ኢታማጆር ሹም እንዲሁም ሜ/ ጄኔራል ገዛኢ አበራ ግድያ ላይ ከመሳተፋቸው በተጨማሪ፣ በአማራ ክልል ተቋማት ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሕዝቡ እንዲሳተፍ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት መቀስቀሳቸውን ያትታል።

አንደኛ ተከሳሽ መሳፍንት ጥጋቡ ቀኑ በውል ባልታወቀ ጊዜ በ2011 ጽጌ በተባለ ግለሰብ አማካኝነት ከብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር በመገናኘት ‹‹ጄኔራል ሰዓረ የአማራን ሕዝብ እያስገደለ ነው፤ ለአማራ ሕዝብ የማይጠቅሙ አመራሮችን በማስወገድ ክልሉን እንቆጣጠራለን፤ አንተም ጄኔራል ሰዓረን ትገድለዋለህ፤ እንዲሁም ሌላ ደፋር እና ወንጀሉን የሚፈፅም ሰው ታገናኘኛለህ›› የሚል ግዳጅ በመቀበል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በክሱ ላይ ምስክር ሆነው ከቀረቡት ግለሰብ ጋር ስታዲየም አካባቢ እንደተገናኘ በክስ መዝገቡ ተብራርቷል። ተያይዞም ጄኔራል ሰዓረ ከተገደለ በኋላ ከሚሰበሰቡት ሰዎች መካከል ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን እንዲገድል ተልዕኮ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንን ገድሎ ሊያመልጥ ሲል ተከብቦ መያዙ በክስ መዝገቡ ሰፍሯል።

ሌሎቹ 12 ተከሳሾች የአማራ ክልል ወጣቶችን ለአመፅ እንዲነሳሱ በማድረግ እንዲሁም ወጣቶችን የአማራ ክልል ልዩ ኀይልን ልብስ አመሳስለው በመልበስ ጥቃት እንዲፈፅሙ በመመልመል እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሕዝቡ ለጦርነት እንዲዘጋጅ በማነሳሳት ላይ መሳተፋቸው ተገልጿል።

ከህክምና ተቋማት የተገኙ የአስክሬን ምርመራ ውጤቶች፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በወንጀል ስፍራ የተሰበሰቡ የጦር መሣሪያ ተተኳሾች፣ የተከሳሾች ቤት ሲበረበር የተገኙ ልምምድ የተደረገባቸው ማስታወሻ ደብተሮች እና የግል የኤሌክትሮኒክስ ማስረጃዎችን በመፈተሽ የተገኙ 24 ማስረጃዎች ከክስ መዝገቡ ጋር ተያይዘው ለፍርድ ቤቱ ቀርበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com