በአስገድዶ መድፈር ጉዳይ ለምን ቆሞ ተመልካቾች ሆንን?

Views: 543

እስከ ኅዳር 30 የሚቆየውንና በአገራችን ለ14ኛ ጊዜ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ የሚካሔደውን የ16 ቀና ንቅናቄ በማንሳት የሚጀምሩት ቤተልሔም ነጋሽ፤ አስገድዶ መድፈርና የተለያዩ ጥቃቶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርሱም አሁንም የማይነገሩና በዝምታ የታለፉ ጥቃቶችና የሴቶች ታሪኮች እንዳሉ ያነሳሉ። በተለይም የደረሰባቸውን የመናገር አቅም ከሌላቸው አእምሮ ህሙማን ላይ የሚፈጹ በደሎችን አስከፊነት ጠቅሰው፤ የተለያዩ ሴቶች የተናገሯቸውንና ያካፈሏቸውን ታሪኮችም ቀንጨብ አድርገው አጋርተዋል።

 

“በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶችና ልጃገረዶች የአስገድዶ መድፈር ሰለባ ሆነው ሳሉ ስለዚህ እውነት ዝም ማለት እንዴት እንችላለን?” ይላል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በመካሔድ ላይ ባለው የ16ቱ ቀናት ፀረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ስታትስቲክስ መረጃዎችን አካትቶ ያወጣው ፖስተር።

የዘንድሮው የ16 ቀናቱ ዘመቻ መሪ ቃል “ዓለምን ብርቱካናማ እናድርግ፤ በእኩልነት የሚያምን ትውልድ አስገድዶ መድፈርን ይጠየፋል” የሚል ሲሆን በመሪ ቃሉ እንደሰፈረው ከሰብአዊነት ውጪ የሆነውንና ሴቶች ላይ አካላዊ፣ ሥነልቦናዊ ጉዳትና የማይሽር ጠባሳ የሚያስከትለው አስገድዶ መድፈር ነው።

ቀደም ካለው ጊዜ አንፃር በመገናኛ ብዙኀን መዘገቡ ጥቃት እየጨመረ ስለመምጣቱ ቢያሳይም፣ ሪፖርት በማድረግ በኩል ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። በቤተሰቦች በኩል ከማኅበረሰቡ መገለልን በመፍራት፣ በተጠቂዎች በኩል ደፋሪዎች በአብዛኛው የሚያምኗቸው የቤተሰብ አባላት፣ ጎረቤቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የህክምና ባለሙያዎች በመሆናቸው ብናገር ሰው አያምነኝም በሚል ለቤተሰቦቻቸው ሳይቀር ሳይናገሩ መቅረታቸው፣ አንድም በአጥቂዎች ማስፈራሪያና ዛቻ ስለሚደርስባቸው በቀልን ፍራቻ ዝምታን መምረጣቸው ሪፖርት ለሚደረጉት ጥቃቶች ቁጥር ማነስ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በተለያዩ አካላት በኩል ታሪኮችን ሪፖርት ከተደረጉ በኋላ የምንሰማ ሲሆን በአብዛኛው በተለይም የአዕምሮ ህመምና አካል ጉዳት ያለባቸው ሴቶች ከሌላው በበለጠ ተጋላጭ የመሆናቸውና ታሪኮቻቸውም ሳይወጡ መቅረታቸውን መመልከት ይቻላል።

ከዚህ በታች ያሉት ታሪኮች ይፋ ከተደረጉት መካከል ሲሆኑ ለዛሬ እነኚህን ካገኘሁባቸውና ከተጠቀሱት ምንጮች ጋር እንደሚከተለው አጋራለሁ።
“ወጣቷ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበረች። በመጀመሪያዎቹ የትምህርት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የአእምሮ መታወክ ይገጥማትና በአማኑኤል ሆስፒታል ህክምና ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ትመጣለች።

ህመሟ በረታ፣ ግን ነገሮችን ተከታትሎ ህክምናዋ ከዳር እንዲደርስ የሚያደርግ ሰው ከጎኗ ስላልነበረ ጎዳና ላይ ወደቀች። ከዓመታት በፊት ጎዳና ተዳዳሪነት ላይ ለሚደረግ ጥናት መረጃ እየሰበሰበች የነበረችው ዶ/ር ማጂ ኃይለማርያም ያገኘቻት ይህች ወጣት በወቅቱ አስራ አምስት በሚሆኑ የተለያዩ ወንዶች መደፈሯን ገልፃላት ነበር።

አጥኚዎቹ ወጣቷ አማኑኤል ሆስፒታል በቋሚነት ገብታ እንድትታከም አደረጉ። በተደጋጋሚ የሚደፈሩ የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶች ኤች አይ ቪ የሚያዙ ቢሆንም ይህቺ ወጣት ግን እንደ እድል ሆኖ ውጤቷ ኔጌቲቭ ወይም ደሟ ከኤች አይ ቪ ነጻ ሆነ።

ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ወጣቷ ከአማኑኤል ሆስፒታል አገግማ ወደ አንድ መጠለያ ተላከች። ቢሆንም ከዓመታት በኋላ ይህቺን ወጣት ዳግም አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ የምትወስደውን መድኀኒት አቁማና ተጎሳቁላ ጎዳና ላይ እንዳገኘቻት ዶ/ር ማጂ ታስታውሳለች።

ስለደረሰባቸው ነገር፣ ስለማንነታቸው እንዲሁም ከየት እንደመጡ፤ እንዲህ እንዲያ ነው ብለው መናገር የማይችሉ የተደፈሩ የአእምሮ ህመምተኛ ሴቶች ሁሌም ለተደፈሩ ሴቶች ድጋፍ ወደሚሰጠው የሴቶች ማረፊያና ልማት ማህበር ይሔዳሉ።

ዶ/ር ማጂ በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው የሴቶች ለጥቃት ተጋላጭነት ላይ የአእምሮ ህመምተኝነት ሲጨመርበት ነገሩ ምን ያህል እንደሚከፋ “ተከታትሎ የሚያሳክማት ሰው የሌላት፤ ለራሷ መናገርና መቆም የማትችል የአእምሮ ህመምተኛ ሴት ለመደፈር ተጋላጭነቷ ከሁሉም የከፋ ይሆናል” ትላለች።
አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ሴቶች አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው፣ አርግዘው ወይም ጨቅላ ሕፃን ይዘው ወደ መጠለያው እንደሚሔዱ የሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር ኃላፊ ነርስ የሆነችው ስምረት ተስፋዬ ትናገራለች።

ስምረት እንደምትለው ስለተፈጸመባቸው ጥቃት መናገር አለመቻላቸው ለእነሱ የሚደረገውን እርዳታ እጅግ ከባድ ያደርገዋል።
ይሄ ቅንጫቢ ታሪክ ቢቢሲ አማርኛ ህዳር 15 ቀን 2012 “በየቤቱ እና በየጎዳናው የሚደፈሩ ሴት የአእምሮ ህሙማን” በሚል ርዕስ ባወጣው ሐተታ ላይ የተጠቀሰ ነው።

ሰሞኑን የሚካሔደውን የ16 ቀናት ፀረ-ፆታዊ ጥቃት ዘመቻን አስመልክቶ፣ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የተካሔደው የዓለም ዐቀፉ “እኔም” በሚል የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ታሪካቸውን ባካፈሉበት ንቅናቄ ወቅት የተጋራ የአንዲት ማየት የተሳናት ወጣት ታሪክ በድጋሚ ቀርቧል። ከታሪኩ የተወሰደ ክፍል እነሆ፤
“በመጀመሪያ የቤታችንን እቃ ለመስረቅ የመጣ ሌባ ነበር የመሰለኝ። ከዛ ግን በጭካኔ ሲደፍረኝ ልጅነቴን ሊሰርቅ የመጣ ሌባ መሆኑን አወቅሁ። ከመደፈሬ በላይ ያመመኝ ግን ማየት አለመቻሌን ተገን አድርጎ ማንነቱን እንዳላውቅ ድምጹን ቀይሮ ለአንድ ሰው ብትናገሪ እገድልሻለው ማለቱ ነው። ከህጻንነቴ ጀምሮ እጄን ይዞ ሲመራኝ የነበረው የአባቴ መዳፍ እንዴት ይጠፋታል ብሎ እንዳሰበ እንጃ። ይኼኛው ይበልጥ ያማል።

ይህን ቁስል ለማከም እየጣርኩ ባለሁበት ሰዓት ሌላ ቁስል ተጨመረልኝ። የዐስር ዓመት ልጅ እያለሁ አጎቴ አባቴ ስምንት ዓመቴ እያለ ያደረገውን ደገመው። ይባስ ብሎም በዚህ እንኳን አገልግይ እንጂ አለኝ። ያኔ ለቤተሰቦቼ የማልጠቅም ሸክም የሆንኩ ስለመሰለኝ ቤቱን ለቅቄ ጠፋሁ። ለቀናትም በቤተክርስትያን ደጃፍ አደርኩ። ከዚህ በኋላ ነው እቴቴ አግኝተው የረዱኝ።

አሁን ያ ጊዜ አልፏል። ነገር ግን አሁንም ወንድ ሲነካኝ እፈራለሁ። አንድ ጊዜ አሞኝ ሀኪም ቤት ሄጄ ዶክተሩ ለምርመራ ቲሸርቴን ከፍ ሲያደርገው ተንቀጥቅጫለሁ። እርግጥ አሁን የሚረዱኝ እናት ልጆች ልክ እንደ ወንድሞቼ ናቸው። ግን ቁስሌ ሙሉ በሙሉ አልዳነም መሰለኝ፤ አሁንም እሰጋለሁ።”
በአገራችን ባለፉት ኹለት ዓመታት በነበረው ግጭትና መፈናቀል ሴቶችና ሕፃናት ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ ተጋላጭና ተጎጂ እንደነበሩ ማንም የማይክደው ሃቅ ሲሆን በጅምላ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈፀመባቸው ስለመሆኑም በስፋትና የሚገባውን ያህል ባይሆንም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሰምተናል።
ይህንኑ አስመልክቶ የ16 ቀናት ዘመቻ ተሳታፊ የሆኑ የሴቶች እኩልነት መብት አራማጆች ካጋሯቸው ሐሳቦች መካከል የሚከተለው ይጠቀሳል፤
“እድሜ ለፖለቲካችን የፕራዮሪቲ ነገር ሆኖ በደንብ ዶክመንት አልተደረገም እንጂ ፍትኅ አላገኘንም እንጂ ስለ ጅምላ አስገድዶ መድፈር ከየአቅጣጫው የሰማንበት ዓመት ነበር። ‹‹የቤቴ መቃጠል ለትኋኔ በጃት›› ነው፤ በግጭት ተሳብቦ አስገድዶ መድፈር። የሴት ጥላቻና ንቀት ጠርቀምቀም ብሎ በልባቸው የሰፈረ ጎረምሶች ግጭትና ጦርነት ሰርግና ምላሻቸው ይመስለኛል። ያለ ሃይባይ መረን የሚለቁበት፣ ያለ ጠያቂ የሚፈነጩበት (በእርግጥ ተጠያቂነቱ በሰላሙም ጊዜ ያዝ ለቀቅ ነው) የአገሪቷ ሰላም መሆን ለሴቶች የአካል ደኅንነት ጥበቃ ግድ ነው። የሴቶች እኩልነት ፖሊሲ ላይ ቢሰፍር፣ በሕግ ቢደነገግ፣ በሕገመንግሥት ቢፀድቅ ግጭት የተነሳ ጊዜ ‹‹ሁሉ ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ፤ ነፋስንም እንደመከተል›› ሆኖ ቁጭ ይላል።”

ከዚህ ሌላ አንድ ወጣት በሶማሌ ክልል በተከሰተው ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሴቶች በአስገድዶ መድፈር የተጎዱበትን ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ በዚሁ ሰሞን እንዲህ አጋርቶ ነበር፤
“ከአብዲ ኢሌ ጋር በተገናኘ በተነሳው ግጭት ብዙ ሴቶች ተደፍረው ነበር። አብዛኛዎቹ በክልሉ ልዩ ኀይል ነበር የተደፈሩት። በዚህ ምክንያት መውጫ የጠፋቸው ሴቶች ኤች አይ ቪ አለብን ብለው የውሸት ለማስፈራራት ሙከራ አድርገው ነበር። ይሄን የሚሰሙ ልዩ ኀይሎች ይተዋቸው እና፣ ኤች አይ ቪ ያለበት ሌላ የልዩ ኀይል አባል ተፈልጎ እንዲደፍራቸው ያስደርጉ ነበር። አስቡት! ይሄን መስማት ያለውን ሰቀቀን”

የሚያሳዝነው ድሮም ብዙም ስለ ጉዳዩ በማይወራበት፣ አሁንም የተሻለ የመረጃ ዝውውርና ግንዛቤ አለ በሚባልበት አስገድዶ መድፈርን በሚመለከት ከእውነታው ይልቅ ወደ አፈታሪክ የሚያዘነብል እምነት በስፋት ይታያል። የሴቶችን አለባበስ፣ መጠጥ መጠጣት እንዲሁም በጥቅሉ “ከባህል ውጪ መሆን” በመጥቀስ ጥፋቱን ወደ እነርሱው ማላከክ ይታያል። ሴቶች ይህቺ አገር የእኛም ናት ወይ እስኪሉ አቅመ ቢስነት እንዲሰማቸው ሆኗል። አንዲት ሴት ያጋራችው የሚከተለው ሐሳብ ይህንኑ ያጠናክራል፤
“የኔ ኢትዮጵያ እኩል አይደለችም ብዬ እንዳስብ ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው በሴትነቴ የሚደርሱብኝ ከቀላል እስከ ከባድ ፈተናዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በከተማም ሆነ ገጠር የምትኖር ማንኛዋም ሴት ከሚገጥማት ፈተናዎች መካከል ለከፋ፣ ጉንተላ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጠለፋ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት እስከግድያ፣ በመሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያሉ መገለሎች፣ መጎንተሎች እና ስልታዊ የሆኑ የማሳነስ እና ወደኋላ የመጎተት ዑደቶች እንዲሁም መሰል ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ናቸው።”
ችግሩን ከመዘርዘር ባለፈ ይህን መጠነ ሰፊ ችግር ለመፍታት ምን ይደረግ የሚለው ላይ አንዳንድ መፍትሔ ጠቆም ለማድረግ ያህል አንዱና የመጀመሪያው ከላይ የጠቀስኩትን አጥቂውን ሳይሆን ተጠቂዎችን ጥፋተኛ የማድረግ ባህል ሊቀር የሚገባው ነው።

ከዚህ ሌላ ማኅበረሰቡ በባህልና ልማድ ሃይማኖትም ጭምር ሰበብ ሴቶችን ከጥቃት መጠበቅ አለመቻሉን ለመሸፈን የሚጠቅሳቸው “ወንዶች ስሜታቸውን መቆጣጠር አይችሉም”፣ “ሴት ልጅ እንቢ ስትልህ መግደርደር ነው” “መጠጥ ጠጥታ ነበር፣ ማን ስከሪ አላት” የሚሉ አስገድዶ መድፈርን እንደ ቀላል እና የተለመደ ነገር የሚቆጥሩ አባባሎች እንዲቆሙ ሊሠራ ይገባል። ማኅበረሰቡ ወንድነትን ከሃይለኛነት፣ የፈለጉትን ከማድረግ፣ ከቁጣ እና ከጉልበተኛነት ያዛመደበት የ “ወንድነት” ትርጉምም ሊቀየር ይገባል።

በሕግ አስፈፃሚዎች እና በህክምና ባለሙያዎች ሳይቀር ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ልጆች በአግባቡ በማስተናገድ በኩል ያለው የአመለካከት ችግርም ለውጥ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ተጠቂዎች ድርጊቱ እንደተፈፀመባቸው ወዲያዉኑ ማስረጃው ሳይጠፋ ሪፖርት እንዲያደርጉም የመገናኛ ብዙኀን ትኩረት ሰጥተው ሊወተውቱ ይገባል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ለምሳሌ ተጠቂዎች ሁሉን ዐቀፍ (የህክምና፣ የፖሊስ፣ የሕግ ድጋፍ) የሚያገኙባቸው ማዕከላት ሦስት ብቻ በመሆናቸው (ምኒልክ፣ ጋንዲ እና ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች) ተጨማሪ ማዕከላት እንዲከፈቱ መንግሥትና አጋሮች ትኩረት እንዲሰጡ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com