ስለ ዳንስ – ከዳንስ ባለሙያው አንደበት

Views: 462

ጌታሁን ስሜ 1977 አዲስ አበባ መርካቶ አብነት አካባቢ ነው ትውልዱ፤ እድገቱም። ብርሃን ሕይወት፣ ተስፋ ኮከብ፣ ድላችን እና ተግባረ እድ የቀለም ትምህርት የቀሰመባቸው ትምህርት ቤቶች ናቸው፤ እንዲሁም ከኢንፎኔት ኮሌጅ በቢዝነስ ማኔጅመነት ዲፕሎማ ተቀብሏል። ቶም ቪድዮግራፊ ማሰልጠኛም በሲኒማቶግራፊ እና ዳይሬክቲንግ ሥልጠና ወስዷል።

በልጅነት የትምህርት ቤት ቆይታው ኢትዮጵያ የምታዘጋጀውን የስፖርት ውድድር ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ትርዒት ላይ ተሳታፊ መሆኑ አሁን ካለበት የውዝዋዜ ሙያ ጋር የመጀመሪያ ሆኖ አዋድዶታል። ‹‹ያኔ ጀምሮ የዳንስ ፍቅር አደረብኝ›› ይላል ሲያስታውስ። ራስ ቴአትርና ማዘጋጃ ቤት በሙያው አገልግሏል።

በውዝዋዜ ዳኝነት ኢትዮጵያን አይደል እንዲሁም ኮካ ሱፐር ስታር ላይ በተጨማሪም በተለያዩ አጫጭር ውድድሮች ላይ ተሳትፎ አለው። የተለያዩ የውዝዋዜ ትርዒቶችን (ኬሮግራፊ) በማዘጋትም ክዋኔዎችን አድምቋል፣ መልእክትም አስተላልፏል፤ በሙዚቃ ቪድዩ እንደ አቢ ላቀው፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ናቲ ማን ያሉ ድምጻውያንን እንዲሁም የአዳዲሶቹን የሙዚቃ ቪድዮ ክሊፕ አዘጋጅቷል።

ብዙዎች ጌታሁን ስሜ ሲባል ‹‹ስለ ዳንስ›› የተሰኘውን ቀደሞ በአዲስ ቲቪ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሚታየውን ሳምንታዊ መሰናዶ ሊያስታውሱ ይችላል። በዚህ ሳምንታዊ መሰናዶ ዙሪያ እንዲሁም በጠቅላላው ውዝዋዜን በተመለከተ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አዲስ ማለዳ፤ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዳንስ ናቸው?
ጌታሁን ስሜ፤ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዳንስ አይደሉም፤ በእኔ አረደድ። እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ዳንስ ማድረግ ይቻላል፤ ዳንስ የሚነሳው ከእንቅስቃሴዎች ስለሆነ። እንቅስቃሴ በሙሉ ዳንስ ሊሆን ግን አይችልም፤ እንቅስቃሴ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ዳንስ እንዲሆን ታሪክ፣ ስሜት፣ ምት (Rhythm)፣ ቅርጽ እንዲሁም ክዋኔ ይፈልጋል። እነዛ ካልተዋሃዱ እንቅስቃሴ ብቻ ነው የሚሆኑት። ዳንስ ግን ስንለው እነዚህ አዋሕዶ ሕይወት መዝራት አለበት።

‹‹እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዳንስ ናቸው›› የቴዲ ዮ ዘፈን ነው። እርሱም ሊል የፈለገው ዘና በሉ፣ አትፍሩ፣ ተንቀሳቀሱ ነገር ነው። ሰዉ ዳንስ እንዲደንስ እያበረታታና እያነሳሳ ነበር እንጂ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዳንስ ናቸው ማለቱ አልነበረም። ግን በዛው አረዳድ ተጽእኖ ፈጥሮ ሰው ሁሉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዳንስ ናቸው ይላል፤ ግን አይደሉም።

ዳንስ ሰፊ ነገር ነው። እናም ደግሞ ዝም ብሎ አይደለም የሚከወነው፤ ለአንድ ዓላማ ነው፤ አንድ ዓላማ ተይዞለት። አንድ ድርሰት እንደሚጻፈው ማለት ነው። ለተፈለገው ዓላማ ይሠራል። ከዛ ያንን ያሳካል። ዳንስ መሣሪያም ነው፤ ቋንቋ ነው። ቋንቋ ለምሳሌ ይወለዳል፣ ያድጋል፤ ይሞታል እንደሚባው፤ ዳንስም ይፈጠራል፤ በደንብ ያድጋል ይሞታል። የሰውነት ቋንቋ ማለት ነው ዳንስ። እና እንቅስቃሴዎች ሁሉ ዳንስ መሆን ይችላሉ እንጂ ዳንስ አይደሉም።

በአገራችን በየጊዜው በሚወጡ የሙዚቃ ቪድዮዎች ላይ የሚቀርቡ ውዝዋዜዎች በተለያየ አንጻር ሲተቹ እንሰማለን፤ የማኅበረሰቡን ትችት እንዴት ታየዋለህ?
የሰውን አረዳድ በኹለት መንገድ ላየው እችላለሁ። መጀመሪያ ባህሉ የፈጠረበት ነገር አለ። ዳንስ የሚባለው ከሌላ ነገር ጋር ስለሚያያዝበት ነው። ዳንስ ቋንቋ ነው ብለናል፤ ቋንቋን ልታስታርቂበት ወይም ልታጣይበት፤ ብዙ ብዙ ነገር ልታስተምሪበት ትችለያለሽ። ዳንስን ሰው የሚያየው እንደ ብልግና ከራቁት ዳንስ ጋር ስለሆነ፤ ሰው ላይ ቀድሞ ብልጭ የሚለው ያ መጥፎ ነገሩ ነው። ስለዚህ ከዛ በተነሳ ለሙያው ያለው ነገር በዛ ልክ ነው ያለው። ትንሽ ማኅበረሰቡ ጋር ችግር አለ።

ኹለተኛ ደግሞ ይህን ሙያ የሚከተሉ ሰዎች ማኅበረሰቡ የሚሰጣቸውን ነገር ተቀብለው በንዴት ያልሆነ ባህሪ ይኖራቸዋል። እንደውም ይህ አስተሳሰብ መፈጠሩ በጣም ጉዳት ነው፤ በሙያው ላለመጠቀም። እንዳልኩት ሙያው ቋንቋ ነው፤ የሚያግባባና የሚያስተምር። ማኅበረሰቡ ጋር ያለው አረዳድ የተዛባ ስለሆነ ግን እንዳያድግ አድርጎታል፤ እንዲገፋና እንዲፈራ።

አሁን ለምሳሌ በባህል የሚሠሩ ሰዎች ይፈሩታል። ከመፍራትም ማግለል አለ። ዳንስን የሚሠራ ሰው ከዋልጌነትና ዱርዬነት ጋር ያገናኙታል። ግን አሁን ዓለም ላይ በዚህ ሰዓት ትልቅ መሣሪያና ማስተማሪያ እንዲሁም ማኅበረሰብን መቀየሪያ ዳንስ ነው። ማስታወቂያዎች ሳይቀሩ የሚሠሩት በውዝዋዜ ሆኗል።

ይህ መሣሪያ ለመሆኑ ማሳያ ነው። ስለዚህ ዳንስ ቋንቋ፣ መግባቢያና ማስተማሪያ መሆኑ የገባቸው ሰዎች ያንን እየሳቡ ይጠቀሙበታል። ዓለም ላይ ትልቅ ተጽአኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሦስት የቴሌቭዥን ሾዎች መካከል፤ አንደኛው በዳንስ ዙሪያ የሚሠራ ነው። ዳንስ ብቻ እየሠራ በዓለም ላይ በእይታ ሦስተኛ ነው ተብሎ ነበር።

እኛ አገር ስንመጣ ይሄ አመለካከታችን የተዛባ መሆኑ ሙያውን ጎድቶታል። አሁን ለይ ደግሞ የተወሰኑ መሻሻሎች አሉበት፤ መድረክ ላይ ሲቀርቡ እና እየተዋቡ ሲመጡ። ክሊፖች ላይ አሁን የምናየው የዳንስን አንድ ዘውግ ነው። እንጂ በጣም ሰፊ ዘውግ ነው ያለው።

ሌላው ደግሞ አገር ውስጥ በዘርፉ ትምህርት ቤት ስለሌለ በእውቀት አለመደገፍ፤ የሚማር ሰው አለመኖሩና ሁሉም ራሱን እያሰተማረ ነው እዚህ ሙያ ላይ የሚቆየው። የዳንስ ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ መድረኮች ባለመኖራቸው፤ ወቅታዊ ብቻ በመሆናቸው ያ ሁሉ ሲዳመር አገሪቱ ከሙያው እንዳትጠቀም አድርጓታል። የማህበረሰቡ አመለካከትም ተጽእኖ አድርጎበታል።

ተወዛዋዥስ ዘመናዊ ዳንስን በምን መንገድ የተረዳው ይመስልሃል?
ራሱን እያስተማረ አይደለ የሚመጣው? ስለዚህ ሲሳሳትም ይሳሳታል። ትምህርት ቤት ገብቶ ወይም ሙያዊ በሆነ መንገድ አልተገራምና የገባውን ነው የሚያደርገው፤ የሳበውን። እድሜም ይወስናል። 13 እና 14 ዓመት ላይ ሆኖ ዳንስን መጀመር የሚስብ ነገር አለው። ከአለባበስ፣ ከፋሽን፣ ከጸጉር እና ከአደናነስ ዘዴ፤ በዛ መንገድ ዳንስን ለመታያ ብቻ ታደርጊዋለሽ። እንደ መሣሪያ ግን ዓላማው ሌላ ነው የሚለውን በዛ እድሜ ላትረጂ ትችያለሽ። መማሪያ ቦታ የለም፤ የሚያስተምርም የለም። ይህ ሁሉ ማኅበረሰቡ ላይም ተጽእኖ ከተፈጠሩት ምክንያቶች አንዱ ነው።

ሰው ይሳሳታል። ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው ሁሉ ይበላሻል። ዳንስ ስሜታዊ ያደርጋል፤ በፍቅር የምትሠሪው ሥራ ነው። ይጎትትሻል። ወጣትነት አለ፤ ሙዚቃና ፋሽና አለ። እነዚህ ሁሉ በዛ ውስጥ ይገኛሉና አስጥሞ ያስቀራል። በዛ ምክንያት ሌላ ዓላማን እንኳን ያስተዋል። በሳይንሳዊ መንገድና በትምህርት የተደገፈ ካልሆነ በመካከል መስመር ስለሌለ፣ ሁሉም በገባው መንገድ ስለሚሠራ በዘልማድ የሚሠራ ነገር የሐበሻ መድኃኒት እንደሚባለው አይመጣጠንም። ከዛ መነሻነት የሳተ ነገር ሊኖር ይችላል።

ባህል ዘመናዊ የሚባል ውዝዋዜ አለ?
ባህል ዘመናዊ የሚባል አለ፤ መኖርም አለበት ብዬ ስለማስብ። ለምሳሌ ዳንስ ከየት ይነሳል ነው። እንቅስቃሴ ነው መነሻው። ይህ ከሆነ ባህል ለምንድን ነው ማደግ የማይችለውና ዳንስ የማይሆነው? ስለዚህ እንደውም አንድ ትልቅ ዘርፍ መሆን አለበት፣ አገሬ መከተል አለባት ብዬ የማምነውና የማስበው፤ ‹‹ፋውንዴሽናል ካልቸራል ዳንስ›› የሚባል አለ። ይህም ያለውን የባህል ዳንስ በጣም አሳድጎና በዘመናዊ መንገድ አሳይቶ ለዓለም ማስተዋወቅ ነው።

በዓለም ላይ የሚታወቀው እስክስታችን ብቻ ነው፤ ከሰማንያ በላይ ብሔር ባለበት። እስክስታችን ብቻ እንጂ የሚታይው የወላይታና የሌላው ዳንስ አይታይም። ያ ማለት አልሠራንበትም ነው። ብንሠራበት፤ ዘመናዊ መንገዶችን ተጠቅመን ለዓለም ብናስተዋውቀው በጣም ትርፋማ እንሆናለን።

ባህል ዘመናዊ ብሎ ስያሜ መስጠትም ይቻላል። ለምሳሌ የኮርያው ዘፋኝ ‹‹ጋንጋም ስታይል›› ብሎ ሲመጣ የፈረስ አካሔድን ነው ያመጣው። ‹‹ጋንጋም ስታይል›› ብሎ ስም አወጣለት። ስለዚህ እኛ ለምን ጋሞ ስታይል፣ ለምን ጎጃም ስታይል አንልም? ያን ባልን ቁጥር በዛች ምልክትነት አገር ትታያለች፤ ባህልን ለዓለም ማስተዋወቅም ይቻላል። ትልቁ ውድድርም ያ ነው። ዳንስ ስም ይወጣለታል። ባህል ዘመናዊ ብሎ ስም ማውጣት ይቻላል። ርዕስ ሊሰጠው ይችላል፤ ነጻ ነው።

አሁን ላይ ምን ያህል ትኩረት ለውዝዋዜ ተሰጠ ማለት ይቻላል?

ሙያው ላይ 16 ዓመቴ ነው። ሒደቱን ሳየው በጣም ብሩህ ነገር ነው የሚታየኝ። ለምሳሌ ለዳንስ ሲ.ኦ.ሲ ተዘጋጀ፤ አምስት ደረጃ ድረስ። አሁን ማንኛውም በዘፈቀደ የሚደንሰው የዳንስ ባለሙያ ልመዘንና ሙያዬን ልያዝ ካለ ይህን የሚመዝን ተቋም አለ። ይህ አንዱ እርምጃ ነው።

ሌላው እርግጥ ነው ትምህርት ቤቶች የሉም። አሁን ከሲ.ኦ.ሲ ራሱ ያስመዘነውና አሠልጣኝ መሆን ይችላል ያለው ማስተማር ከቻለ፣ ትንሽ በእውቀት ሊመራ ነው [ዳንስ] ማለት ነው። ሌላው ቴአትር ቤቶች አካባቢ ከለውጡ ጋር በተያያዘ አዳዲስ አደረጃጀቶችን እየፈጠሩ ነው። አሁን ዳንሱን በራሱ ሰፋ አድርጎ ለመሥራት፤ እየገባቸው ነው። እናም ጥናት እየተደረገ ነው። ጥናቱ ትንሽ ገፋ ተደርጎ ሔዷል። ይህ ተግባራዊ ሲሆን ዳንስ ራሱን ችሎ ሾው፣ ፊልም፣ ድራማ ይኖረዋል። መንግሥት በጀት ሊሰጠውና ሊሠራበት ነው ማለት ነው። እስከ አሁን ዳንስ በዓል ማድመቂያ ብቻ ነው።

አሁን ግን ራሱን ችሎ ወቅቱን እየጠበቀ የዳንስ ድራማና ፊልሞችን፣ የዳንስ ፌስቲቫሎችን መንግሥትም ራሱ ሊሠራ ጥናት ላይ ነው። ተግባራዊ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እሱም ሲመጣ ሌላው እርምጃ ነው።

የአርት አካዳሚ /የሥነ ጥበብ ማዕከል/ ይሠራል እየተባለም ነው። ይህም ተስፋ የሚሰጥ ነው። አርት አካዳሚ ኖረ ማለት ዳንስ አንዱ ዘርፍ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የተማረ ዳንሰኛ አገሪቱ ታገኛለች። ሌላው ተስፋው አሁን ላይ ከተማው ውስጥ የሚሠሩት ቴአትር ቤቶች ናቸው። ከ5 ዓመት በኋላ ቴአትር ቤቶቹ ለትርዒት ክፍት ይሆናሉ። ሲከፈቱ ባዶ ቤት አይቀመጡም፤ ትርዒት ሊታይባቸው ይችላል።

ማዘጋጃ፣ ራስ ቴአትር እና ሌሎችም እድሳትና ማስፋፊያ ላይ ናቸው፤ አድዋ እና ዋተር ፓርክ፤ አዳዲስ ይሠራሉ የተባሉትም በሙሉ ትርዒት መከወኛ ናቸው። ስለዚህ በጣም የሠለጠነ የጥበብ ሰው ይፈልጋሉ ማለት ነው። እነዛ ሲሟሉ በትክክል ዳንስ ብቻ ሳይሆን በተጓዳኝ ያሉ ሙያዎች አብርው ማደግ ይችላሉ የሚል ተስፋ አለኝ።
‹‹ስለ ዳንስ›› በርካታ ዓመታት የቆየ መሰናዶ ይመስለኛል፤ እንዴት ነበር አጀማመሩ?

ዲጄ ሆኜ እሠራ ነበር፤ ማታ ላይ ነበር የማጫውተው። ሰዉ ቤት ቁጭ ብሎ እንዲህ ባለው ነገር ለምን መዝናናት አይችልም የሚል ነበር መነሻው። እንዲሁም ሙያችንን መጀመሪያ አገራችን ውስጥ ለምን አናስተዋውቅም አልን። አስቀድሞ እንዳልነው የማህበረሰቡ አረዳድ ሌላ ስለሆነ፤ ቢያንስ ዳንስን ዓለም እንዲህ እየተጠቀመበት ነው የሚለውን ሰው እንዲያይና ትንሽ ግንዛቤን እንዲቀይር ማድረግ ነበር ሐሳባችን። የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኀን (አዲስ ቲቪ) ስናመጣው በጣም ወድደውት ባክሎግ ሥሩ አሉን። በወቅቱ ስሜታዊ ስለነበርን ሠራን። አየር ላይ ሲውል አዲስ ነገር ስለነበር ሰው በጣም ወደደው። እኛ አይደለም የምናዝናናው፤ ዓለም የሠራውን ስላየ ሰው ተቀበለው።

የተጀመረው በ2002 ነው፤ 9 ዓመት በአዲስ ቲቪ ተላለፈ። አምስት ወር አረፍ ብሎ አሁን ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካት ኮርፖሬሽን (ኢቲቪ) ሔደ። እስከአሁን ዓላማችን ማህበረሰቡ ላይ ያለውን አረዳድ መቀየር ነው። ዳንስ ዓለም እንዲህ እየተጠቀመበት ነው፤ እኛ ከዚህ እየጎደለብን ነው የሚለውን። ወደፊት ያሉ ልጆች ዋጋውን የሔደበትን መንገድ ሊያመሰግኑት ይችላሉ። አሁን ላይ ግን እስከ አሁንም የማህበረሰቡን ሐሳብ መቀየር ላይ ነው ያለነው።

ተሳክቶልናል ብለንም እናስባለን። በተወሰነ ደረጃ የዳንሶችን ቃና እያየን ነው። ተቀባይነቱ ጥሩ ነው። ሰውም እየተዝናናበት ይገኛል። አሁን ሐሳባችን እኛ የምናሳያቸውን ቪድዮዎች በአገር በተሠሩ ቪዲዮዎች መቀየር ነው። ስፖንሰር ኖሮን አያውቅም፤ የምንሠራውም በእልህ ነው። ያለንን ገንዘብና ጊዜአችንን እንጨርሳለን እንጂ፤ በገንዘብ ያገኘነው ትርፍ የለም። የቀጠልነው ሙያተኞቹ እንዲነሳሱ፤ እኛ ያለብንን ኃላፊነት ወደ እነርሱ እያጋባን ነው። ምንም በሌለበት አገር ጀማሪ መሆን ከባድ ነውና አብረን እንጀምርና አብረን የሆነ ውጤት እናምጣ ነው። እኛ ያሳለፍነውን መንገድ የሚቀጥሉ ወጣቶች ያንን ፈተና እንዳያዩት ነው።

ብዙ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ቢበዛ ከዓመትና ኹለት ዓመት የዘለለ ሲቆዩ አይታይም። ከተጠቀሱት ችግሮች አንጻር ፕሮግራሙን እንዴት ማቆየት ቻላችሁ?
እልህ ነው። እኛ የምንፈልገወው ገንዘብ ስላልሆነ ነው። ዓላማችን ይሄ ማህበረሰብ አስተሳሰቡ ተቀይሮ ማየት ነው። በአንድ ጊዜ አይቀየርም፤ ግን የሆነ ነገሩ ተቀይሮ ማየት፣ ዘርፉ ተቋቁሞ ማየት፤ ገፍቶ እንዲሔድ ማድረግ ነው። እልህ ብቻ ነው እዚህ ያደረሰን። በጣም ሙያውን እስኪጎዳሽ ድረስ ነው የምትወጂው፤ እስኪጎዳን ድረስ ነው የምንወደው። ዳንስ የሚታይበት ነገር የለም። የዳንሰኞችን ታሪክ፣ ዳንሳቸውን ምን ላይ ታያለሽ? ምንም ላይ አይታይም። እኛ ደግሞ ብናቆም ጭራሽ ከሰው እእምሮ ይጠፋል። ዳግም ማምጣት ደግሞ ሌላ ፈተና ነው። ቢያንስ ሌላ የሚቀበለንና የሚያሳድገው ነገር እስኪመጣ መተንፋሻ፣ መተያያ፣ ማውሪያቸው ቢሆን ብለን ነው እስከ አሁን ያለነው።

ሚድያን የሚውቅ ሰው ያውቀዋል፤ እንዴት እንደሚመጣ። ኀላፊነትና ሸክሙ ጠቅላላ እኛ ጋር ነው። እንግዳ ቀጥረን፣ ጥያቄ ወጥቶ፣ ፕሮፋይል ተዘጋጅቶ፤ ዝርዝር ተወርቶ፣ ከተቀረጸ በኋላ ኤዲት የማደርገው ራሴ ነኝ። ኤዲት ተደርጎ ኢዲቶርያል ካላለፈ ድጋሚ ተልሶ ተሠርቶ። እነዚህ ሁሉ ሲለመዱ ሸክሙን ትችይዋለሽ።
ጉዳቱ እኛንም ጎድቶናል፤ አንዳንዴ ከማትታገይው ጋር ትታገያለሽ። ግን ምንም አይደል። አንድ ቀን የሆነ ጥሩ ነገር ይመጣል፤ አሁንም ጥሩ ነገር ስላየን። ብዙ ሰዎች ቢያንስ የምትሉትን ነገር አገራችን እናምጣው ብለው ጥናት ላይ ግቡ ይሉናል፤ ጥናቶች ላይ ገብተንም ሠርተናል።

ብቻ የማየው ነገር ደስ ይለኛል። ልፋቴን ዝም ብዬ አላጣሁትም ብዬ አስባለሁ። ትውልዶች ደግሞ ከእኛ በላይ አስፍተውት ይሔዳሉ። በጣም ምርጥ ምርጥ ልጆች ይመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። እነሱ ደግሞ ይህን አይተው ከእኛ አርቀው ሊሔዱበት ይችላሉ።

በውዝዋዜ ሥራ ምሳሌ ይሆናል የምትለውና የምታደንቀው ሰው አለ?

አንዱ ችግር እሱ ነው። የምታደንቂው ሰው ብልጭ ብሎ ነው የሚጠፋው። ጀግና አለመፈጠሩ ይመስለኛል ሙያው ብልጭ ጥፍት እንዲል ያደረገው። የሆነ ወቅት ላይ አንድ ልጅ ይሄ ተስፋ አለው ስትይ የሆነ ነገር ይወስደዋል። ጽናት የለውም። እንደ መሸጋገሪያ ነው የሚያዩት። ብልጭ ብሎ ችሎታ አለው ሲባል በዛው ይቀራል።
ለምሳሌ (ይቅርታ ይደረግልኝ፤ ለብዙ ባለሙያዎች ምሳሌ ይሆናል ብዬ ነው የምናገረው) ኢትዮጵያ ውስጥ በውዝዋዜ ጎበዝና ፊት መሪ የነበረው አብዮት ደመቀ ነው። አብዮትን የማያውቀው ተወዛዋዥ የለም። አብዩት አሁን ምን እያደረገ ነው ‹ኡበር› ታክሲ እየነዳ ነው። ያደገበትን የለፋበትን በሙሉ ትቶ ሌላ ነገር ውስጥ ነው ያለው። ልጁ ያን መንገድ መምረጡ ግድ ይሆናል። ግን መሆን አልነበረበትም። እንደሱ ዓይነት ሺሕ አብዮቶችን በከተማችን ፈጥሮ በእውቀት ተመርተው እርሱ ያለፈበትን ቻሌንጅ ሌሎች እንዳይሔዱበት ማድረግ ነበር።

እንዳልኩት ብታደንቂም ጥሩ ነው ብትይም ግን ጽናቱ ነው ዋናው። ነገ የእኔን እጣ ፋናት አላውቀውም። አሁን የምችለው ያህል ነው የምችለው። ካልቻልኩኝ እኔም እንደ አብዮት ሌላ ነገር ልመርጥ እችላለሁ። እንዲህ ያሉ ልጆች አሉ፤ ግን ቶሎ ነው ከሙያው ዞር የሚሉት። እገሌ ማለት ይከብደኛል፤ ለማድነቅም የሚከፍለውን መስዋዕትነት ማየት እፈልጋለሁ። ያ ነው የጎዳው፤ ተተኪዎችም ያልመጡት።

የአዲስ ማለዳ አንባቢዎች አጋጣሚውን አግኝተው መታዘብ ችለው ከሆነ፤ በሦስተኛው የሆሄ ሽልማት ላይ ብዙዎችን ያስጨበጨበ ኬሮግራፊ አቅርባችሁ ነበር። ከዛው ጋር ተያይዞ ኬሮግራፊ ምንድን ነው?
ኬሮግራፊ በጣም ትልቅ ነው። አንዳንድ ሰዎች ኬሮግራፊ ያላቸው እውቀት ስናይ፤ ትምህርት ቤት ስለሌለ አንፈራረድም። በገባው ነው ሰው የሚሔደው። ኬሮግራፊ ማለት እገሌና እገሌ ማቆምና ማሰለፍ ይመስለዋል፤ ያ አይደለም። ኬሮግራፊ ስታወሪ ቋንቋ ለምንድን ነው የምታወሪው እንደሚለው፤ ለማስታረቅ፣ ለማፋተት፣ ለማፋቀር ነው፣ ታሪክ ነው፤ ምንድን ነው የምትናገሪው ነው። ኬሮግራፊ በጣም ሰፊ የሆነ ሐሳብ ነው። ለአንድ ዓላማ ኘው።

ሆሄ ላይ ያለውን ብናነሳ፤ የሥነ ግጥም ሽልማት ነው። ቦታው ላይ የተገኙት በቋንቋ የሰከሩ ሰዎች ናቸው። ለእነዚህ ሰዎች ዳንሳችን ምን ሊላቸው ነው። እነሱ ብዙ ቋንቋ የሚያውቁ ናቸው፤ የዳንስ ቋንቋ ለእነዚህ ሰዎች ምን ይላቸዋል ነው። መጀመሪያ ሰዎችን የሚመጥን ሰዎች ለአእምሯቸው እንዳይጎረብጣቸው መጨነቅ ያስፈልጋል።
የተሠራው ‹‹ከእክሱም ጫፍ አቁማዳ›› በተሰኘው የደበበ ሰይፉ ግጥም መነሻነት ነው። ይህን ቋንቋ እንዴት አድርገን ነው በእንቅስቃሴ ሕይወት ልንሰጠውና ታሪክ መንገር የምንችለው፤ እንዴት አድርገን ነው እንዲከታተሉን ማድረግ የምንችለው ነው። ረጅም ጊዜ ነበር የሠራነው/ የተለማመድነው። ዳንስን፣ እስክስታን፣ ሰርከስን እንዲሁም በአገራችን ያሉ ፉከራና ሽለላዎችን በሙሉ አዋሕደን ነው ለማሳየት የሞከርነው።

ኬሮግራፊ በዓላማ ስንሠራው ሰው እንዲህም መሥራት ይቻላል እንዲል ነው። ምንአልባት ሙከራችንን ያደንቃል። ጥሩ ነው ያሉን ሰዎች አሉ። ሌላው ግባችን ደግሞ አገራችን እየተጠቀመች አይደለም፤ ብትጠቀምበት ከዚህም በላይ ማሳየት ትችላለች ነው። ብዙ አገራት በወጣቶች ነው ታሪካቸውን የሚናገሩት። እኛም ግጥሙን በ50 ደቂቃ ገለጽነው።

ኬሮግራፊ ‹‹ዲዛይን ኦፍ ፒክቸር›› ነው። የሚያምር፣ የተዋበ፣ ቋንቋ ያለው፣ መልዕክት ያለው ነገር የሚናገር ማለት ነው። ከብዙ ነገር የተሠራ። ያንን ውበት በኬሮግራፊ ይታያል።

የኢትዮጵያ ውዝዋዜ በዓለም መድረክ ይታየል፤ እንታወቃለን?
እንዴት ልንገርሽ? በጣም ከሚቆጨኝ ነገር አንዱ ይሄ ነው። ሌላው አንድ ነገር ብቻ ይዞ በጉራ አደባባይ ይሸጣል። እኛ ደግሞ በጣም ሸክም ኩንታል ሀብት ይዘን የለንም። እርግጠኛ ነኝ የሆነ ወቅት ላይ ዓለምን ይቆጣጠርል [የኢትዮጵያ የባል ውዝዋዜ] ብዬ በሙሉ ልቤ አምናለሁ።

አሁን ምንም ነገር ስለሌለ፣ ኢንዱስትሪውን የሚመራ ግለሰብ ባለመኖሩ ነው የጫጨው። መንግሥት ነው ኃላፊነት ያለበት፣ ዘመናዊነት ባህልን ይገድላል ብሎ ከማሰብ ይልቅ ያስተዋውቃል፤ ያድናል ብሎ ማሰብ አለበት። አለበዚያ ስልክና ኢንተርኔት የመሳሰለውን ቴክኖሎጂና ሌላውን ምንም መጠቀም የለብንም፤ ቁጭ ነው የምለው። ስለዚህ በጣም ክፍት አድርጎ በጀት ማድቦ ማስፋት አለበት።

ዓለም ላይ አስክስታ ‹‹የትከሻ ዳንስ፣ በግሩፕ የሚደነስ፣ ሴትም ወንድም የሚጫወቱ›› ይላል እንጂ ሌላ ምንም አይነግርም። ቱሪስቶች ይመጣሉ፤ ምሽት ቤት ይሔዳሉ፤ እስክስታ ያስጨፍሯቸዋል። ይህ ነው በቃ የኢትዮጵያ ጭፈራ፤ ግን እንደዚህ ነው ወይ? ሌላ አገር ዳንስ ማየት እፈልጋለሁ ካልሽ እዚህ ቦታ ይህ ሾው አለ ብለው ምርጫ ያቀርባሉ፤ ፈለግሽውን ታያለሸ።

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አጥኚ መጥታ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚገልጽ ዳንስ ማየት እፈልጋለሁ የት ልሒድ፤ ሰዎች ምሽት ቤት ሒጂ አሉኝ ልሒድ ወይ አለችኝ። ግን አትሒጂ እዛ የሚያዝናናሽ ነው ያለው አልኳት። ያ ብቻ የኢትዮጵያ መገለጫ አይደለም። አንዱ ኤለመንት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ነገር ጋር አልደረስንበትም። ብዙ ኤለመንቶች አሉ፤ ግን ዘርፉ ደከም ያለ ስለሆነ እዛ መድረስ አልቻልንም። እድል ቀንቶሽ ክዋኔ ባለበት ጊዜ ብትመጪ እንጂ ፕሮግራም ተቆርጦለት በየሳምቱ በየወሩ የሚባል የመድረክ ትዕይንት የለም አልኳት። ለምንድን ነው የማትሠሩት፤ ታሪክና ብዙ አቅም አላችሁ። ከዛ አንጻር እየሠራችሁ አይደለም ነው ያለችው።

ዓለም ላይ የኢትዮጵያን ዳንስ ስናስብ፤ ለማስተዋወቅምኮ ስንሔድ ነው። እንዴት ነው የሚያዩን፤ የሠራነው ሥራ የለም። ስለዚህ ውጤት አይጠበቅም። ያሉት ትልቅ ቦታዎች ምሽት ቤቶች ናቸው የሚያስተዋውቁት። እሱም እየተዝናኑባቸው እየቀረጿቸው ነው የሚታዩት።

ከውጪ ሰው ሲመጣ ቁጭ አድርጎ አይደለም የዳንስ ታሪክ እንዲነግራቸው የሚፈልጉት። ዝም ብሎ ለሦስት ደቂቃ አጫውቷቸው እንዲሔዱ ነው። አንዱ መቀረፍ ያለበትም ይህ ነው፤ መከወን አለበት። ሆሄ ሽልማት አንድ እድል ፈጠረ፤ ግን በዓመት አንድ ብቻ ነው። ወርሃዊና መደበኛ መሆን አለበት። አሁን ግጥም ምሽት እንደበዛው ሁሉ ዳንስ ምሽቶች ቢኖሩ። ዳንስን ቅድም እንዳልነው ከሌላ ነገር ጋር ስለሚያገናኙት እንጂ ዳንስ እንደዛ አይደለም፤ እንዳልነው እንደ ቋንቋ እንደ አጠቃቀማችን፣ እንደፈለጉት መጠቀም የሚቻል ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com