የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሕጋዊ የግዢ ስርዓትን አልተከተለም ተባለ

Views: 986

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የስንዴ፣ አልሚ ምግብ፣ የመኪና ወንበርና ተጓዳኝ ልብስ በድምሩ በ1.9 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ግዥ የፈጸመ ሲሆን ለግዢዎቹ ሕጋዊ ደረሰኝ አላቀረበም ተባለ።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን የ2012 በጀት ዓመት በተመለከተ የሂሳብ ኦዲትን በገመገመበት ወቅት፤ ቋሚ ኮሚቴው በኮሚሽኑ በተከናወነ ሂሳብ ኦዲት ግኝቶችን አስመልክቶ ባዘጋጀው ጥያቄ መሰረት ኮሚሽኑ ሕጋዊ የግዢ ስርዓትን እንዳልተከተለ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ቋሚ ኮሚቴው መንግሥታዊ ባልሆኑት የውጭ ድርጅቶችም ግዢ ተፈጽመው ለእርዳታ በመጡ እህሎችና አልሚ ምግቦች ላይም ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለኮሚሽኑ በድምሩ 1.3 ቢሊዮን ብር የቀረጥ ሂሳብ ወጪ ተደርጎ የገቢ ደረሰኝ በዝርዝር ያለመቅረቡ ኦዲት ግኝት ያሳያል ተብሏል።
ኮሚሽኑ የፌዴራል የግዥ መመሪያን ባልተከተለ መንገድ በተለያዩ ቀናት የመኪና ጎማ፣ የምግብ ዘይት እና ወተት በአጠቃላይ 544 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም 556 ሚሊዮን ብር በላይ በቀጥታና ከአንድ ድርጅት ግዥ መፈጸሙ ተገምግሟል።

ቋሚ ኮሚቴው ኮሚሽኑ ለሠራተኞች የተከፈለውን ውሎ አበል ሳያወራርድ በውዝፍ የተያዘ ከ608 ሚሊዮን ብር በላይ የተያዘ እና ለጉልበት ሠራተኞች ክፍያ፣ ለመጋዘን ኪራይ እንዲሁም ዝናብ ዕጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ድርቅን ለመቋቋም ተብሎ ለክልሎች የተሰራጨ 806 ሚሊዮን አምስት መቶ ሺሕ የሚደርስ ብር የወጪ ማስረጃ ያልቀረበ መሆኑን በድክመት አንስቷል።

ኮሚሽኑ በሰውና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱት አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያደርግ እና ለእነዚህ ግዢዎች አሁን ላይ ምቹ ያልሆኑ የፋይናንስ አሰራሮችም እንዳሉ የገለፀ ሲሆን፣ በክልል ቅርንጫፎች የተፈፀሙ ግዢዎች ደረሰኝ በክልሎች እጅ እንደሚገኝ ገልጿል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ፣ በኮሚሽኑ የተለያዩ የግዥ አማራጭ አሠራሮች እያሉ ስርዓትን ያልተከተለ የግዥ ሂደትን መከተል እንደመረጠ አንስተዋል።

ኮሚቴው ኮሚሽኑ በዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት ሆነው ከተነሱ ኻያ አንድ ነጥቦች ሦስቱ ላይ ብቻ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱ ከበቂ በታች እንደሆነና ችግሮችን በትኩረት በማየት አሁን ካለበት ኦዲት ግኝት ለመውጣት መሥራት እንዳለበት ማሳሰቡን ከፓርላማ የተገኘ ማስረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com