ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኅዳር 10/2012

Views: 164

1-የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ታዛቢዎች ጥምረት የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ሂደት አስመልክቶ እሰከ እኩለ ቀን ድረስ የታዘበውን ይፋ አደርጓል።128 የጥምረቱ አባላት በተለያዩ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር ያደረጉትን ምልከታ የቡድኑ መሪ ብሌን አስራት ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል። ጥምረቱ ይፋ እንዳደረገው መረጃ አብዛኛዎቹ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በሰዓታቸው የተከፈቱ ሲሆን፤ በአንዳንድ ጣቢያዎች ከተስተዋለው የቀለም እጥረት ባሻገር ይህ ነው የሚባል የምርጫ ቁሳቁስ እጥረት አልነበረም። በተጨማሪም በኹሉም የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ተሟልተው መገኘታቸውን መታዘብ እንደቻሉ ብሌን ገልጸው፤ ከመራጮች ቁጥር መብዛት የተነሳ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች መጨናነቆች እንደተከሰቱ አስረድተዋል።በሌላም በኩል በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የአንድን ወገን የምርጫ ምልክት እንዲመረጥ በመራጮች ላይ ጫና ሲደረግ መስተዋሉን የቡድን መሪዋ ጠቁመዋል።(ዋልታ)

…………………………………………………………………………………

2-በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከሰሞኑ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ  ተቋርጦ የቆየው የመማር ማስተማር ሒደት ወደነበረበት እየተመለሰ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………………………

3-የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለዋልያዎቹ የ8 መቶ ሺሕ ብር የማበረታቻ ሽልማት አበረከተ።በ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኅዳር9 /2012 በባህር ዳር ስታዲየም የኮትዲቯር አቻውን 2ለ1 የረታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበበ ስካይ ላይት ሆቴል የምሳ ግብዣ እና የማበረታቻ ሽልማት ተደርጎለታል።የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ትናንት ላስመዘገቡት ውጤት ከ20 እስከ 30 ሺሕ ብር የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።ብሔራዊ ቡድኑ ወደፊት በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ውጤታማ ከሆነ በእንያዳንዱ ጨዋታ ከ8 መቶ ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  አስታውቋል።(ኢቢሲ)

…………………………………………………………………………………

4-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በኔትወርክ እና በኮምፒውተሮቻችን ውስጥ ባሉ መተግበሪያዎች የሚመጡ ጥቃቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል “ጋሻ” የተባለ አንቲ-ቫይረስ ማበልፀጉ ተነግሯል። አንቲ-ቫይረሱ በአገራችን ላይ የሚቃጡ የቫይረስ ዓይነቶችን ታሳቢ በማድረግ እና ዓለም ላይ አሉ የተባሉ ዋነኛ የቫይረስ ዓይነቶችን እንዲከላከል ተስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ባለሙያው ገልፀዋል።“ጋሻ” አንድን የቫይረስ ዓይነት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የቫይረስ ዓይነቶችን መከላከል እንዲችል ታሳቢ ተደርጎ መሠራቱ ታውቋል።(ዋልታ)

…………………………………………………………………………………

5-በአዲስ አበባ ከተማ 325 የሚሆኑ የአገር ውስጥ አሰሪ እና ሰራተኛን የሚያገኛኙ ኤጀንሲዎች እና ደላሎች ሕግን ተከትለው እንደማይሰሩ የአዲስ አበባ ከተማ ሰራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አለምፀሐይ ጳውሎስ ገልጸዋል።ከሕግ እና ከመመሪያ ውጭ የሚሰሩ አሰሪና ሰራተኛን የሚያገናኙ ኤጀንሲዎች እና ደላሎች አዲስ በተሻሻለው የአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት ከ2 እስከ 10 ዓመት እስራት በተጨማሪም አዋጁን ጥሰው በተገኙ ኤጀንሲዎች እና ደላሎች ከብር 75 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚያስቀጣ ኃላፊዋ ገልጸዋል።(ዋልታ)

…………………………………………………………………………………

6-በአፋር ክልል ሎጊያ መውጫ በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ አገር ቤት ሊገቡ የነበሩ 6 የጦር መሳሪያዎች እና ከ10 ሺሕ በላይ ጥይቶች  የክልሉ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።የአፋር ክልል የመንግስት ኮሚንኬሽን ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አሕመድ ካሎይታ ሕገ ወጥ መሳሪያዎቹ የተያዙት የአካባቢው ማኅበረሰብ በደረሰው ጥቆማ እና የፀጥታ መዋቅሩ ባካሄደው ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ማዋል እንደተቻለ አስታውቀዋል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)

…………………………………………………………………………………

7-በደብረ ታቦር ዩንቨርሲቲ የምግብ መመረዝ ተከስቷል በሚል የተሳሳተ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ 15 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ዩንቨርሲቲው አስታወቀ።ደብረ ታቦር ዩንቨርሲቲ እንደስታወቀዉ ትናንት በዩንቨርሲቲዉ የተማሪዎች ምግብ አዳራሽ ዉስጥ በመገኘት ምግቡ ተመርዟል ብለዉ የሀሰት መረጃ ያስተላለፉት አካላት ላይ ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል ብሏል። (ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)

…………………………………………………………………………………

8-የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት በቢሾፍቱ ማሰልጠኛ ማዕከሉ በ2006 ያስጀመረው የግንባታ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ አራት አመታት እንደተጓተተ ተገለጸ።የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ጨረታውን ካሸነፈው ቡኤልኮን ኮንስትራክሽን ኃለፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከተባለ ስራ ተቋራጭ ጋር መጋቢት 24/2006 ውል የገባ ሲሆን ተቋራጩም ኢንስቲትዩቱ የሚያስገነባው ባለ አራት ፎቅ ሕንጻ 80 የመኝታ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ የሥልጠና ክፍል፣ ጋራዥ፣ የእንጀራ እና ዳቦ መጋገሪያ ክፍሎች ገንብቶ በ2008 በማጠናቀቅ ለማስረከብ ውል የገባ ቢሆንም ፕሮጀክቱ እስካሁን አለመጠናቀቁ ታውቋል።ግንባታው በአፈፃፀም ደረጃ 84 ነጥብ 5 በመቶ ላይ ደርሶ የነበረው ፕሮጀክት ከ2008 ጀምሮ በመቋረጡ ምክንያት በንብረትና ሐብት ላይ ከፍተኛ ውድመት እየደረሰ መሆኑ ተብራርቷል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com