ልማት ባንክ በሩብ ዓመቱ 213 ሚሊዮን ብር አተረፈ

Views: 140
  • የተበላሸ የብድር መጠን ከ39 በመቶ ወደ 33 በመቶ ዝቅ ብሏል

በ2011 በጀት ዓመት ኪሳራ ውስጥ ገብቶ የነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2012 የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሦስት ወራት ከኪሳራ በመውጣት 213.77 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገለጸ።

ለትርፉ መጨመርም በባንኩ የተወሰዱ ልዩ ልዩ እርምጃዎች በምክንያትነት የተቀመጡ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ባንኩን ኪሳራ ላይ ጥለውት የነበሩ የተበላሹ ብድሮች እና ተቋሙ ይዟቸው ያሉ ንብረቶች በብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ መመሪያ መሰረት መለየታቸው እና በድጋሚ መዋቀራቸው ይገኙበታል።

ባንኩ ተረክቦ ሳይሠራባቸው እና ገቢ ሳያመነጩ የቆዩ ንብረቶች ባለፈው ዓመት ለደረሰው ኪሳራ አስተዋፅኦ ነበራቸው ተብሏል። ንብረቶቹንም ለመሸጥ ዋጋቸው ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ለመግዘት አቅም የላቸውም የተባለ ሲሆን፣ የውጪ አገር አልሚዎችም እነዚህን ያገለገሉ ንብረቶች ከመግዛት ይልቅ የራሳቸውን እቃዎች ይዘው የማስገባት ፍላጎት በማሳየታቸው ከፍተኛ ወጪ እያስወጡ ያሉ ንብረቶቸን ማስወጋድ አልተቻለም ሲሉ የባንኩ ፕሬዘዳንት ኃይለ ኢየሱስ በቀለ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ንብረቶች ከአሁናዊ የገበያ ዋጋ ጋር በማጣጣም በመሸጥ የተገኘውን ትርፍ ከዚህ በላይ ከፍ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 84 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሲሆን፤ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ካፒታል እንዳለው ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ባንኩ በያዝነው ዓመት ባጠናቀረው ሪፖርት ላይም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ከሰጣቸው ብድሮች ውስጥም አምስት ቢሊዮን ያህሉ እንደማይመለስ ማረጋገጥ ችሏል። ባንኩ ከሰጠው 16 ቢሊዮን ብር ውስጥም 11 ቢሊዮን የሚሆነውን ስለመመለሱ አጠራጣሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ተመሳሳይ ሰነድ ያመላክታል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም እነዚህን ብድሮች ከባለ ሃብቶች ጋር በመነጋገር የመክፈያ ጊዜ በመስጠት እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የተበላሸ ብድር መጠኑን በስድስት ነጥብ ከመቶ ቀንሶ ወደ 33 በመቶ ማውረዱንም የባንኩ ፕሬዘዳንት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የብድር አሰጣጥ እና አሰባሰብን በተሻለ መንገድ በመቆጣጠር ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን ባለመቀበል እና የተሻለ የውጪ ምንዛሬን በማቅረብ ባንኩ ከኪሳራ አንዲወጣ ብሎም አትራፊ እንዲሆን ለማድረግ መቻሉን ኀይለየሱስ ገልፀዋል።

የባንኩን አስተዳደራዊ ለውጥ በተመለከተም ከዚህ ቀደም በባንኩ በተደረገው ለውጥ መሰረት አንዳንድ ቦታዎችን የሟሟላት ሥራ ቢጀመርም፣ አሁንም አንደሚሠራበት የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ የባንኩን አጠቃላይ ዝርዝር አሰራር ከሌሎች ሀገራት ተመሳሳይ ባንኮች በማጥናት በኢኮኖሚው ላይ ከሚደረገው አገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ጋር የሚጣጣም ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል።

በቀጣይም የተበላሸ ብድር መጠኑን ለመቀነስ የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ በማድረግ በቀጣይ ጊዜያት ባንኩን ትርፋማ ለማድረግ እየሠራን ነው ሲሉ ገልፀዋል። በተመሳሳይም በአጠቃላይ ለልማት የሚሆን ብድር የሚያቀርቡ የፋይናንስ ተቋማት የቢዝነስ ሞዴል ማሻሻይ እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች በ2012 በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከታክስ በፊት 6.65 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን የገለፀ ሲሆን፣ ልማት ባንክ ለዘርፉ አጠቃላይ ትርፍ የ3.21 በመቶ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ይህ ገቢም የልማት ድርጅቶቹ አቅደውት ከነበረው የብር 4.1 ቢሊዮን ትርፍ አንጻር ሲታይ ክንውናቸው ከዕቅዳቸው ከ60 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው የድርጅቶቹ አፈጻጸም በኤጀንሲው መሰብሰቢያ አዳራሽ ከጥቅምት 2 እስከ 4 ቀን 2012 በተገመገመበት ወቅት ታውቋል።

የልማት ድርጅቶቹ ይህንን ትርፍ ሊያገኙ የቻሉት የባንክ እና የመድን አገልግሎቶች በመስጠት በሩብ ዓመቱ ብር 16.92 ቢሊዮን ገቢ ለማግኘት አቅደው ብር 18.99 ቢሊዮን ወይም የእቅዳቸውን 112.29 በመቶ ማግኘት በመቻላቸው ነው።

ከተገኘው የብር 6.5 ቢሊዮን ትርፍ ከፍተኛውን ብር 6.1 ቢሊዮን ወይም ከአጠቃላዩ 93 በመቶ ያህል ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በብር 250.63 ሚሊዮን ወይም በ3.77 በመቶ ኹለተኛ ደረጃ ይዟል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com