የህፃናቱን የንፅህና ክብር የተጋፋው ግለሰብ ተፈረደበት

Views: 336

በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ የመድረሳ ቁርአን ቤት ውስጥ የግብረ ስጋ ግንኙነት የመሰለ እና ለንጽህና ክብር ተቃራኒ የሆነ ድርጊትን በሦስት ሴት ህፃናት ላይ የፈፀመው ግለሰብ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርቦ ጥፋተኛ ተባለ።
ግለሰቡ የግል ተበዳዮች የመድረሳ ትምህርታቸውን ለመከታተል በሔዱበት ወቅት ህጻናቱን ወደ ባዶ ክፍል በማስገባት እና ልብሳቸውን በማስወለቅ ባካሔደው የፆታዊ ትንኮሳ ወንጀል ነው ክስ የተመሰረተበት። የስምንት ዓመት ታዳጊ የሆነችው አንደኛ የግል ተበዳይ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳቸው፤ በግምት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ‹‹ነይ ፑሽ አፕ ላሠራሽ›› በሚል ወደ ክፍሉ እንዳስገባት ለፍርድ ቤቱ ተናግራለች።

‹‹የራሱንም የእኔንም የውስጥ ሱሪ ዝቅ በማድረግ ያነካካኝ ሲሆን ከንፈሬንም ስሞኛል›› በማለት የምስክርነት ቃሏን ሰጥታለች። በተመሳሳይም ኹለት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሴት ህፃናት ላይ ለንፅህና ክብር ተቃራኒ የሆነ ድርጊት መፈጸሙን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱ የግል ተበዳዮችን እና ምስክሮችን ቃል፣ ህክምና ማስረጃ እንዲሁም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፤ በተከሳሹ ላይ ሦስት ዓመት ከ 11 ወር ፅኑ እስራት ፈርዶበታል።

በህፃናት ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶችን መፈጸም ተደጋጋሞ የሚያጋጥም ድርጊት እንደሆነ የሚያስረዱት በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የልደታ ክፍለ ከተማ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ፂዮን ሽፈራሁ ናቸው።

‹‹ድርጊቱ ከአስገድዶ መድፈር ያነሰ ሲሆን ነገር ግን ለሴት ልጅ ክብር ተቃራኒ ከሆነ የወንጀል ሕጉ ለንጽህና ክብር ተቃራኒ የሆነ ተግባር ነው ሲል ይገልጸዋል›› ይላሉ። ‹‹ይህም አስገድዶ የጾታ አካላትን መንካትን የሚጨምር ሲሆን አሁን አሁን በጣም በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለ ወንጀል ነው›› ሲሉም ይናገራሉ።

በአዋቂ ሴቶች ላይም ተመሳሳይ ወንጀል እንደሚፈፀም በማንሳት፣ አስገድዶ መሳም እንዲሁም አስገድዶ ክብሯን የሚቃረን ተግባር መንካት እንደሆነ ተናግረዋል።
‹‹እንደ ማንኛውም የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መረጃ በቀላሉ የማይገኝበት ድርጊት ሲሆን ልጆቹ በወቅቱ ለቤተሰብ ከተናገሩ ምንም እንኳን የክብረ ንፅህና መገሰስ ባያጋጥምም በኀይል የተነኩበት ቦታዎች ላይ ምልክቶች ይገኛል። ይህ ግን ከሦስት እሰክ አራት ባለው ቀን ለቤተሰቦቻቸው ከተናገሩ ነው። ነገር ግን የሥነ ልቦና ባለሞያዎች ልጆቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ልጆቹን በማጫወት ቃል የሚቀበሉ ሲሆን ደጋፊ ማስረጃዎችን በመጠቀም ለፍርድ ቤቱ እናስረዳለን›› ሲሉ አቃቤ ሕጓ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ከሚደርሱ የፆታዊ ጥቃቶች ውስጥ ከ 25 በመቶ በላይ የሚሆነው በህፃናት ላይ የሚፈፀም እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ከግዜ ወደ ግዜ በወንድ ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች እየጨመሩ መምጣታቸውንም ጥናቶች ያመላክታሉ። ለጥቃት ተጋለጭ ከሆኑት ህጻናት ውስጥም በጎዳና የሚኖሩ ህጻናት ይበልጥ ተጠቂ እንደሆኑ እና የቤት ውስጥ ትቃቶች ይበልጥ የጥቃት ምንጭ እንደሆኑም ጥናቶቹ ያመላክታሉ፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com