ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚደረግ የሸቀጦች ንግድ መቀዛቀዙ ተገለፀ

Views: 521

በሐረር እና በድሬዳዋ ከተሞች በተፈጠረው ግጭት ላለፉት ሦስት ቀናት ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሸቀጣ ሸቀጦችን ለመላክ ችግር እንዳጋጠመ በአዲስ አባባ የሚገኙ ነጋዴዎች ተናገሩ።

ሸቀጦቹን ወደ አካባቢው ከመላክም በተጨማሪ ከ ጅቡቲ ወደ አዲስ አባባ የሚመጡ እቃዎችን ለማጓጓዝ ባለው ከፍተኛ ውጥረት ምክንያት እንዳልተቻለ ነጋዴዎች ተናግረዋል።

ከአዲስ አባባ ድሬዳዋን ጨምሮ ሀረር እና ወደ ሌሎች የምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ወራት በተከሰቱ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ወደ አካባቢዎቹ የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸውን ሸቀጣ ሸቀጦቹን ወደ አካባቢው ሲልኩ የነበሩ ሥማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልፀዋል።
በአካባቢዎቹ በተፈጠሩት አለመረጋጋቶችም በርካታ ነጋዴዎች ሸቀጦችን እንደማያዙ እና እዚህ ያሉ ነጋዴዎችም ቢሆኑ ወደ አካባቢዎቹ ሸቀጦቹን ለመላክ ስጋት እንደተፈጠረባቸው ምንጮቹ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በፍተሻ እና መንገዶች በተደጋጋሚ በመዘጋታቸው ሸቀጦቹ እስከ 15 ቀን በመንገድ ላይ ይቆያሉ ተብሏል። በዚህም ምክንያት በአካባቢው ካሉ ነጋዴዎች ጋር የነበረን ግንኙነት በመሻከር ላይ ነው ሲሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቅሰዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በድሬ ዳዋ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ያሬድ በላቸው እንደሚሉት፣ በአካባቢው ባለው ውጥረት ምክንያት ሸቀጦች በመንገድ ላይ በመዘግየታቸው አለ ብለን ከምንሸጠው ይልቅ የለም የምንለው ይበዛል ሲሉ ይገልጻሉ። አክሎም በአካባቢው ግጭቶች በድንገት ስለሚነሱ በማለዳ ወደ ንግድ እንቅስቃሴው አንገባም፤ ማታም ሱቃችንን በጊዜ እየዘጋን ስለምንሔድ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተዳክመዋል ብለዋል።

ግጭቶቹ ብሔርን እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ናቸው የሚሉት ያሬድ፣ አንዳንዴ ከየት እንደመጡ በማይታወቁ ወጣቶች እንደሚነሳም ተናግረዋል። በዚህ መሀልም የሚቃጠሉ የንግዱ ሱቆችም አሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ በበኩሉ በሀገሪቱ ካለው የፀታ ችግር አንፃር ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ዝውውር ለመቆጣጠር በመንገዶች ላይ ፍተሻ ቢኖርም የሸቀጦች መዘግየት ምክንያት ሊሆን አይችልም ብሏል።

የቢሮው ዋና ኀላፊ ዳኔ ቦሩ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የተዘጋ መንገድ የለም ያሉ ሲሆን ሐረርጌ እና ጭሮ አካባቢ ለአንድ ቀን ተዘግቶ የነበረው መንገድ መከፈቱን ገልፀዋል። ህብረተሰቡ እና በአካባቢው የሚገኙ ነጋዴዎች በተፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት የንግድ ሱቆችን ከፍተው አለመነገዳቸው እንዲሁም የጅመላ ነጋዴዎች ሸቀጦቹን ወደ አካባቢው ባለመላካቸው በንግድ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ አሳድሯል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበኩሉ ችግሮቹ ሲፈጠሩ ለሚመለከታቸው አካላት ከማሳወቅ የዘለለ አቅም የለንም የሚል ምለሽ ሰጥተዋል። አዲስ ማለዳ የድሬ ዳዋ ከተማ አሰተዳደር የሥራ ኀላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የሚላኩት ሸቀጦች በመንገድ ላይ በሚኖረው ፍተሻ ዕቃዎቹ ለበርካታ ጊዜያት ይዘገያሉ የተባለ ሲሆን፣ በሀረር እና በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንግዱ በመቀዛቀዙ ክፍያ በወቅቱ እየተፈጸመ ባለመሆኑ በርካታ ነጋዴዎች ሸቀጦቹን ለመላክ ያለቸው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑን ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com