የሕብረት ኢንሹራንስ አጠቃላይ ዓመታዊ ትርፍ ቀነሰ

Views: 107

ሕብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በ2012 ዓመት 106.596 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ ትርፍ ማግኘቱን ያስታወቀ ሲሆን ትርፉ ካለፈው ከ2011 ጋር ሲነፃፀር በ17 ሚሊዮን ብር ቀንሷል።

ለባለ አክሲዮኖች የተከፋፈለው ድርሻም 167 ብር ቅናሽ ያሳየ ሲሆን የአረቦን ትርፉ ላይ ግን የ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር የ 55በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ባለፈው የበጀት ዓመት ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ዘርፍ 494 ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺሕ ብር እንዲሁም ከሕይወት መድን ዘርፍ ከ 38 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ሕብረት ኢንሹራንስ አስታውቋል። በአጠቃላይም 530 ሚሊዮን ብር በላይ በአረቦን ገቢ መሰብሰብ የቻለ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመትም 13 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ገልጿል።

ለቅናሹ በምክንያነት የተቀመጠውም የባለፈው ዓመት የራያ ቢራን የአክሲዮን ድርሻ በመሸጥ የተገኘው ገቢ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢው ከፍ እንዲል አስተዋፅኦ እንደነበረው የሕብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሰረት በዛብህ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ሆኖም ኢንሹራንሱ በሠራቸው ጠንካራ ሥራዎች የባለፈው ዓመት የራያ ቢራን የአክሲዮን ሽያጭ ገቢ ተቀንሶ ሲታይ በዚህ ዓመት አጠቃላይ የ55 በመቶ ጭማሪ አለው ብለዋል።

በአንፃሩ የካሳ ምጣኔ በ 2010 ከነበረው 60 በመቶ የስምንት በመቶ ጭማሪ በማድረግ ከ137 ሚሊዮን ብር በላይ የከፈለ ሲሆን በ 2010 በጀት ዓመት ከከፈለው 104 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ከ 23 ሚሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

ከባህር እና ከየብስ የጉዞ መድን ሽፋን የአረቦን ገቢ ላይ መቀዛቀዝ ያሳየ ሲሆን በአገሪቱ የነበረው የገቢ እና የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ እና የታሰበውን ያህል ስኬታማ አለመሆኑ ለገቢው መቀነስ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

ከ 15 ዓመታት በላይ በዘርፉ የሠሩት ፍቅሩ ፀጋዪ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ እድገት አሁን ባለበት ደረጃ ዝቅተኛ ነው የሚል ሐሳብ ያነሳሉ። በማሳያነትም የመድን አገልግሎት የመዳረስ መጠን ከአንድ በመቶ በታች መሆኑ እና ዘርፉ ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርቱ ያለው አስተዋፅኦ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉ ይገልፃሉ።
ከሌሎች በአፍሪካ ከሚገኙ አገራት ጋር እንኳን ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው የሚሉት ፍቅሩ፣ በኬንያ ዘርፉ ለጠቅላላ አገራዊ ምርቱ እስከ ሦስት በመቶ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ ጠቅሰዋል። ዘርፉንም ለማሳድግ እምቅ አቅም አለ ያሉ ሲሆን፣ አገሪቱ ያላት ከ 100 ሚሊዮን የሚልቅ የሕዝብ ቁጥር እና የመድን ሽፋን ያልተገባለት ሀብት መጠን ከፍተኛ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

‹‹ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የሀገራችን ኢንሹራንሶች አብዛኛውን ትርፋቸውን ከመድን አገልግሎት ይልቅ በሚሳተፉባቸው የተለያዩ ሥራዎች ማግኘታቸው ነው›› ሲሉ ይናገራሉ። ‹‹በዋናነትም በርካታ የአገሪቱ ሕዝብ ተሰማርቶ በሚገኝበት በግብርናው ዘርፍ ላይ እና ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ደረጃ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን በብዛት የመድን ተጠቃሚ በማድረግ የዘርፉን ተደራሽነት እና ትርፋማነት ማሳድግ ይገባል። ከእምነቶች ጋር ተጣጥመው የሚሔዱ የመድን አማራጮችም ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል›› ሲሉ ያሳስባሉ።

እንዲሁም በጤና እና በሕይወት መድን ላይ ትኩረት ተደረጎ ቢሠራ ካለው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ጋር ተዳምሮ ጥቂት የፈጠራ ሐሳቦች ቢጨመሩ ዘርፉ በሚገባ ማደግ ይችላል የሚል ሐሳብ ያነሳሉ።

ሕብረት ኢንሹራንስ በመላው ሀገሪቱ 50 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 12ቱ አገናኝ ቢሮዎች ናቸው። 202 ሴት ሠራተኞች እንዲሁም 180 ወንድ ሠራተኞችን በድምሩ 387 ሠራተኞችን ቀጥሮ በማስተዳደር ላይ ይገኛል።

የተፈቀደ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል እና የተከፈለ 375 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያለው ኢንሹራንሱ ከ 406 በላይ አክሲዮን ባለ ድርሻዎች አሉት።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com