በዓለም ባንክ ታዛቢነት በህዳሴው ግድብ ላይ የሚደረገው ውይይት ተጀመረ

Views: 269

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ለዓመታት ሲደረግ የነበረው የሦስትዮሽ የመንግሥት የቴክኒክ ስብሰባዎች ላይ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ እንዲገቡ መወሰኑን ተከትሎ በተገባደደው ሳምንት በሚካሔደው ስብሰባ ላይ በታዛቢነት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሦስቱ አገራት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች በነጩ ቤተ መንግሥት በመገኘት ያደረጉት ውይይት ብሎም ስምምነት አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። እስከ ግንቦት 2012 ድረስም አራት ስብሰባዎችን በማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ከኻያ ዓመታት በፊት የአባይ ተፋሰስ ልማት ሲመሰረት ከ10 የሚልቁ ለጋሽ አገራት ገንዘብ ሰብስበው ሲመድቡ፣ የትረስት ፈንዱን የዓለም ባንክ እንዲያስተዳድር መወከላቸው በተፋሰሱ ዙሪያ ባሉ ድርድሮች ባንኩ የቀረበ ተሳትፎ እንዲኖረው አድርጎ ነበር።

በተለይም ዴቪስ ግሬይ የተባሉት የባንኩ ባልደረባ በዓለም ባንክ ውስጥ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ለግብጽ በማድላት ይወነጅሏቸው እንደነበረም ባለሞያዎች ያስታውሳሉ። ‹‹በወቅቱ ኢትዮጵያ ባደረገችው ጫና ሰውዬው እንዲነሱ ቢያደርጉም ዓለም ባንክ በአባይ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጎራ በመልካም እንዳይታይ አድርጎት ቆይቷል›› ሲሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እና ለዓመታት በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮችን በቅርበት የሚከታተሉ ግለሰብ ይናገራሉ።
የዓለም ባንክ በቅርበት የሚከታተለው ይህ የተፋፈሱ አገራት ስብስብ፣ ካሉት አባል አገራት መካከል ግብፅ ራሷን ያገለለች ሲሆን ሱዳን በድጋሚ በአባልነት ወደ ተፋሰስአሃገራቱ ተመልሳ መግባቷ ይታወሳል።

ታዛቢ በተገኘበት የሚደረገው በያዝነው ሳምንት ከኅዳር አራት እስከ ስድስት የሚዘለቅ ዓለም ባንክ እና የአሜሪካን ኢንዲሁም የግብፅ ተዳራዳሪዎች የሚገኙበት ውይይት በአዲስ አበባ እንደሚደረግ ይጠበቃል። በድርድሩ ዙሪያ የሱዳን አቋም ምን ሊሆን ይችላል በሚለው ጥያቄ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ባለሞያው፤ የሱዳን ተደራዳሪዎች እና የውሃ ሃብት ሚኒስቴር በግድቡ ባለቤትነት እና የመጠቀም መብት ላይ ፅኑ አቋም እንዳላቸው። ነገር ግን የሱዳን ፖለቲካ ሁኔታ ያለመረጋጋት ቀጣይ የሱዳን አቋምን ለመተንበይ እንዲስቸግር ያደርጋል ሲሉ ይናገራሉ።

በተለይም በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት እና አሁን በሱዳን አምባሳደር በመሆን በማገልገል ላይ ያሉት ሙሐመድ ደሪል፣ የሱዳን የሽግግር መንግሥት መቋቋም ላይ ፊተኛውን ሚና ኢትዮጵያ እንድትይዝ በማድረግ የግድቡን እና የተፋሰሱን ፀባይ ተረድተዋል ብለው እንደሚያምኑ የአዲስ ማለዳ ምንጭ ይናገራሉ።

‹‹ኢትዮጵያ በሱዳን የሽግግር መንግሥት ላይ የተጫወተችው ሚና ግብፅን ባይተዋር ያደረገ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሱዳናዊያን ዘንድ ፍቅር እና አክብሮት እንዲያተርፉ ያስቻለ እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች ላይም የራሱን ጫና ያሳርፋል ብዬ አምናለሁ›› ሲሉ ለድርድሩ ቅርብ የነበሩት ግለሰብ ይናገራሉ።
አክለውም የህዳሴ ግድብ ለሱዳናዊያን በአባይ ወንዝ ዙሪያ ያላቸውን የመካከለኛ ተፋሰስነት ሚና በአግባቡ የመለሰ እንዲሁም የሉአላዊነት ጉዳይ ነው ብለው እንደሚያምኑም ይገልጻሉ። አክለውም ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥበትም የህዳሴ ግድቡ ይፋ ሳይደረግ ጭምር የሱዳን የቀድሞ ፕሬዘዳንት ዑመር ሐሰን አልበሽር ያውቁ እንደነበር እና ይህም የግብፅ መንግሥትን አስቆጥቶ እንደነበር ይናገራሉ።

የቴክኒክ ቡድኑ ከሚወያይባቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው ከሦስቱ ሃገራት የተወጣጣ የባለሞያዎች ቡድን በአስዋን ግድብ እንዲሁም በህዳሴው ግድብ ላይ የእለት ተእለት ሥራውን እንዲቆጣጠሩ የሚለው የግብፅ ጥያቄ ሲሆን፣ ይህ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደረገቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል።

በህዳሴው ግብ የውሃ በግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያም በተደረው ውይይት ላይ ግብጽ ባቀረበችው ሐሰብ መሰረት፣ የግድቡ የውሃ አሞላል ሂደት በሰባት ዓመታት ውስጥ እንዲሆን ከመጠየቋም በላይ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ ለግብፅ እንድትለቅና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ በዋናነት ውሃ እንዲለቅ የሚጠይቅ ነው። ይህም ግብፅን በወንዙ ላይ ያለተቀናቃኝ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ከማሳየቱም በላይ በግብፅ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የነበረው ውይይት እና ድርድር ያለውጤት እንዲጠናቀቅ ምክንያት ሆኗል።

ኢትዮጵያ በዓመት ምን ያህል ውሃ ለግብፅ ትልቀቅ የሚለው በሚኖረው የአየር ሁኔታ ላይ የሚወሰን ነው የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፤ በቀጣይ ደረቅ የአየር ንብረት የሚኖር ከሆነ በኹለቱ አገራት መካከል ያለው አለመግባባት እንዲያይል ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ይገልፃሉ።

በ1929 እና በ1959 የተደረጉ እና የኢትዮጵያ እና የሌሎች ተፋሰሱ አገራት ተጠቃሚነት በግብፅ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያደርገውን ስምምነት ተፈፃሚ ለመድረግ በእጅ አዙር ውይይቶች አሁን ላይ መልሳ ለመተግበር ትፈልጋለች የሚል ሐሳብንም ያነሳሉ።

ሱዳንን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱ አገራት እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ ለጋሾች ለግድቡ ግንባታ መልካም ዕይታ አላቸው። በወንዙ ላይ 85 በመቶ ወሃ የምታዋጠው ኢትዮጵያ ከወንዙ ያላትን ፍትኀዊ ተጠቃሚ የመሆን መብት ባለፉት ዓመታት የተደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ማረጋገጥ እንድትችል ረድቷታል ሲሉም ይገልጻሉ።
ለዚህም ይመስላል አሜሪካንን ጨምሮ የበርካታ አገራት አምባሳደሮች የግድቡን ግንባታ መጎብኘት ግድቡ ላለው ተቀባይነት ማሳያ ነው ይላሉ። የግድቡ ግንባታም ይሁን ውሃ አሞላል በስኬት መጠናቀቁ አይቀርም የሚሉት በአባይ ተፋፈስ አገራት ዙሪያ ከ15 ዓመታት በላይ ጥናት ያደረጉት ወንድወሰን ሚቺጎ፤ ኢትዮጵያ ከዐስር ዓመታት በፊት የነበራትን ዝቅተኛ ተሰሚነት መቀየር መቻሏ በአባይ ጉዳይ አትንኩኝ የምትለዋ እና እስከዛቻ የሚደርስ ማስፈራሪያ ስታሰማ የነበረቸው ግብፅ አሁን በግድቡ ውሃ አሞላል እና ወደፊት ስለሚኖረው የውሃ አለቃቅቅ በጠረጴዛ ዙሪያ እንድትደራደር አድርጓታል ይላሉ።

የግድቡ ጉዳይ ታዳሽ የኀይል ምንጭን የሚያመጣ መሆኑ በራሱ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲያገኝ እንዳደረገው ባለሞያው ይናገራሉ። የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታትም ለግድቡ 150 ሺሕ ዶላር እርዳታ ማድረጋቸው ግድቡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የቀጣናውም ሃብት በመሆኑ የድምፅ ሚዛኑ ላይ የራሱ ጫና አለውም ይላሉ።

ብሎም ከቀጠናው አልፎ የአፍሪካ ፕሮጀክት እንደሆነ የአፍሪካ ኅብረት አምኖ ተቀብሎ በሕብረቱ ስር ያለው የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት በስሩ ካሉ ፕሮጅክቶች መካከል የህዳሴ ግድቡን አንዱ አድርጎታል ያሉት ወንድወሰን፤ ይህ የግድቡን እውን መሆን እና የድርድሮቹን መጨረሻ የሚያመለክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹ግድቡ ከግማሽ አልፏል፤ ይህም የሰባት ወር ፅንስ ማለት ነው፣ ስለዚህ መወለዱ አይቀርም፣ ሊጨነግፍ የሚችልበትን ጊዜ አልፏል። የግድቡ ጉዳይ ላይ እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች የግድቡን መገንባት ግብፅ ተቀብላ ስለ አሞላሉ ነው። ይቅር ግድብ መገንባት አባይን ለመጠቀም ማሰብ በግብፅ የሚያስኮንን ተግባር ነበር›› በማለት የውይይት እና የድርድሮች መልክ መቀየሩን ያስረዳሉ። ‹‹ኢትዮጵያ የተሸነፈች ቢመስልም በግድቡ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ በበለይነት እየመራች ነው›› ሲሉ ያጠቃልላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com