በእነ በረከት ስምኦን መዝገብ ተከሰው ፍርድ ቤት የቀረቡት አሜሪካዊ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

Views: 237

የአማራ ክልል መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በእነ በረከት ስምኦን መዝገብ ክስ መሥርቶባቸው ከሚያዚያ ሦስት 2011 ጀምሮ በእስር ላይ ያሉት ዳንኤል ግዛው የቀረበባቸውን ክስ እንዲያስተባብሉ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዘዘ።

የዲቬንቱስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ዳንኤል፣ ከጥረት ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ውል አማካኝነት ከአንደኛ እና ከኹለተኛ ተከሳሾች ጋር በመሆን የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ስምምነት ፈጽመዋል ሲል ክሱን መሥርቷል።
ጥቅምት 2007 ተፈፀመ የተባለው በዚህ ውል ውስጥም፣ ተከሳሽ የተበደሩት የቤተሰብ ብድር የዴቬንትስ ባለሃብቶች ሊከፍሉ ቢገባም ባለማድረጉ የሕዝብ ሃብት የሆነውን የጥረት ኮርፖሬት 46 ሺሕ ስድስት መቶ ብር እንዲባክን አድርጓል በሚል አቃቤ ሕግ ክሱን መሥርቷል።

ክሱን የተቃወሙት ተከሳሽ በበኩላቸው በዋነኝነትም ክሱ አንደ ግለሰብ ይቅረብ ወይስ በኩባንያቸው ላይ የሚለው ያልተለየ መሆኑ ላይ ዝርዝር ተቃውሞ አሰምተዋል። ጥረት ኮርፖሬት ለሥራ ማስኬጃ በኩባንያው አካውንት ውስጥ ገቢ ተደረገ የተባለው ገንዘብም የዋለው በድርጅቱ የቀድሞው ባለድርሻዎች ሥም ለየግላቸው ለወሰዱት ብድር ማወራረጃ ይሁን ወይም ለድርጅቱ የኩባንያ ብድር መክፈያ የሚለው በክሱ ተዘርዝሮ አልቀረበም ሲሉም ተከራክረዋል። ገንዘቡ እንደተባለው ለግል እዳ ማወራረጃነት መዋል አለማዋሉ ላይም በኦዲተር የተረጋገጠ ማስረጃ አልቀረበም ሲሉ ዳንኤል በጠበቃቸው በኩል ተከራክረዋል።

ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሠራም በሚለው መርህ መሰረትም፣ ተከሳሽ ወንጀሉን ፈጽሞታል ቢባል እንኳን ሊጠየቅ የሚችለው በወንጀል ሕጉ ሲሆን በዚህ መሰረትም የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ በሙስና ወንጀል እንደሚጠየቁ ስለሚደነግግ ተከሳሽ የግል ባለሃብት በመሆናቸው ሊጠየቁ አይችሉም ሲሉ ጠበቃቸው ክሱን ተቃውመዋል።

ተከሳሽ የደረሳቸው የክስ ግልባጭ በግልፅ ያልተቀመጠ እና ይህም ወንጀሉን ለመከላከል የሚያዳግት እንዳደረገባቸው ተናግረዋል። ‹‹የግል እዳውን በራሱ መክፈል እየተገባው ይህንን ባለማድረጉ›› የሚል ሃረግ ያለበት ክስ መቼ፣ ከማን እና ለምን ዓላማ የሚለውን በአግባቡ ያላስረዳ የተድበሰበሰ ክስ ቀርቦብኛል ሲሉም ተከራክረዋል።

ከ25 ዓመት በላይ በምህንድስና ሙያ ልምድ ያላቸው ግለሰቡ፣ ፎርድን ጨምሮ በአሜሪካን አገር ባሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ውስጥ ልምድ አካብተዋል።
የጥረት ኮርፖሬት አባል ያልነበሩ መሆናቸውን የገለጹት ተከሳሽ፣ አንደኛ በእነ በረከት ስምኦን መዝገብ ክሴ ሊታይ አይገባም፣ የጥረትን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲሁም በጥረት በኩል ያለውን የሕዝብ አደራ ለመጠበቅ የሚያስችለኝ የሕግ ሥልጣንም ሆነ ኀላፊነት ያልተሰጠኝ በመሆኑ ክሴ እንዲነጠል ሲሉም ጠይቀዋል።

የአቃቤ ሕግን ማሰረጃ ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፣ ዳንኤል እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ሲሆን የተከሳሽ መከላከያ ምስክርን ፍርድ ቤቱ ካዳመጠ በኋላ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑት እና አሜሪካ ዜግነት ያላቸው ዳንኤል፣ በቅርቡ ህመም አጋጥሟቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ህክምና አግኝተው መመለሳቸውን አንድ የቤተሰብ አባላቸው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ነገር ግን በቂ ህክምና ሳያገኙ ሔደዋል ብለው እንደሚምኑ ገልጸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲም በተከታታይ እንደሚጠይቃቸው ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ከአሜሪካን ኤምባሲ መረጃ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ኤምባሲው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 54 ህዳር 6 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com