ኒኩሌር ለጤፍ ምርት ማሻሻያ ጥቅም ላይ ዋለ

Views: 779

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ዘይት የእርሻ ምርምር ተቋም ውስጥ ለሦስት ዓመታት ሲደረግ የነበረው የአቶሚክ ጨረርን በመጠቀም የጤፍ ምርጥ ዘርን የማሻሻል ምርምር የላቦራቶሪ ሙከራውን በተሳካ መልኩ በማጠናቀቅ በመስክ ላይ መሞከር ተጀመረ።

በሶሎሞን ጫንያለው (ዶ/ር) የሚመራው እና አራት ባለሞያዎችን አሳትፎ በኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ የፋይናንስ ድጋፍ የሚደረግለት ይህ ምርምር፣ የኒኩሌር ጨረርን በመጠቀም የጤፉን ዘረመን በማሻሻል የተሻለ ዘርን ለማግኘት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች መታየታቸውን ለመታዘብ ተችሏል።

በቁመቱ ያጠረ እንዲሁም በአጭር ጊዜ በመድረስ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ምርጥ ዘር ላማግኘት የተለያየ መጠን ያለው የኒኩሌር ጨረርን በመጠቀም ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ተመራማሪው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹ከተለያዩ ዝርያዎች የተወሰዱ የጤፍ ዝርዎች ላይ የተለያየ የጨረር መጠንን በመጠቀም የጤፉን ዘረመን በማሻሻል ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያለው፣ በጥቂት ውሃ በአጭር ጊዜ የሚደርስ ሰብል ለማምረት የሚስችሉ ምልክቶችን ተመልክተናል›› ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹በተያዘው ዓመት ምርቱን ወደ መስክ ወስደነዋል፣ የጤፍ ተክል ቁመቱ ሲረዝም የመውደቅ አዝማሚያ ስለሚኖረው የምርታማነት አቅሙ የሚቀንስ ሲሆን በቁመቱ ያጠረ እና በአጭር ጊዜ የሚደርስ ዝርያን በመፍጠር ድርቅን የሚቋቋም ምርት እናገኛለን ብለን እናምናለን›› ሲሉ ሶሎሞን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የተለያዩ ኬሚካሎችን በመጠቀም ምርጥ ዘሮችን ሲያዘጋጅ የቆያው ተቋሙ፣ የኒኩሌር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተመሳሳይ ጥናት ሲያካሒድ የመጀመሪያው ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በጤፍ ምርት የሚለማ ሲሆን በየ ዓመቱ ስድስት ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳታፊ ናቸው።
ተመራማሪዎቹ ከኤክስ ሬይ ጋር ሲነፃፀር ከ10 እስከ 100 ሚሊዮን እጥፍ የሚበልጥ ጨረርን እንደሚጠቀሙ ለማወቅ ተችሏል። ዓለም ዐቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ተቋምም፣ ለጥናቱ የቴክኒክ እና ሥልጠና ድጋፎችን ያካሔደ ሲሆን በተመሳሳይም የጥንቃቄ እርምጃ ላይ ድጋፍ ማድረጉን ይፋ አድርጓል።

‹‹የምንጠቀምበት የኒኩሌር ጨረርን የሚሰጠን መሣሪያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግበታል። በጥንቃቄ ካልተያዘ የሽብር ጥቃትን ጨምሮ ለተለያዩ እኩይ ተግባራት ሊውል ስለሚችል ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ ከፍተኛ ቁጥጥር በኢትዮጵያዊያን ባለሞያዎች ይደረግለታል›› ሲሉ ሶሎሞን ተናግረዋል።

ጤፍ በዓለማቀፍ ደረጃ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ ዘሩን በማሻሻል የምግብ አቅርቦት እንዲሁም የኢኮኖሚ ጥቅሞችን እንዲያመጣ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ተመራማሪው ተናግረዋል።

መደበኛ የኤክስሬይ ማሽን ከሚጠቀመው ከ10 እስከ 100 ሚሊዮን ጊዜ የሚልቅ የጨረር ኀይል የሚጠቀመው ይህ ምርምር፣ የኒኩሌር ቴክኖሎጂው ለሌላ ዓላማ እንዳይውል ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግበትም ታውቋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ጥናቶች ግሉቲን የተባለውን የፕሮቲን አይነት መጠቀም የሚያመጣውን የጎንዮሽ ጉዳቶች በመሸሽ እንደ ጤፍ ያሉ ከግሉቲን ነጻ የሆኑ ጥራ ጥሬዎችን መጠቀም ተመራጭ እየሆነ መጥቷል። ይህም በኢትዮጰያ እና በኤርትራውያን ዘንድ ብቻ በሰፊው ሲዘወተር የቆየውን የጤፍ ምርት በዓለማቀፍ ደረጃ እንዲጨምር አድርጎታል።

ምርምሩ ተጠናቆ ምርጥ ዘሩ ይፋ እስኪደረግ ከአራት እስከ አምስት ዓመት ሊፈጅ እንደሚችልም ሶሎሞን ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com