የአማራ ክልል የአንበጣ መንጋን ለመቆጣጠር የፌዴራል መንግሥት ድጋፉን እንዲጨምር ጠየቀ

Views: 577
  • የአንበጣ መንጋው በሦስት ዞኖች በ7 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ ሰፍሮ ይገኛል

የአማራ ክልልና የአፋር ክልልን የሚያዋስኑ አካባቢዎች፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደሮች በ8 ወረዳዎች እና በ23 ቀበሌዎች የበረሃ አንበጣ መከሰቱን ተከትሎ መንጋውን ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት በቂ ድጋፍ እያደረገልን አይደለም ሲል አማራ ክልል ግብርና ቢሮ ወቀሰ።
የአንበጣ መንጋው ካባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ በየመንና ሶማሌ ላንድ አድርጎ በነ አፋር እና ትግራይ ክልሎች ላይ ቀድሞ የተስፋፋ ሲሆን፣ ከመስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ አጎራባች አካባቢዎች በመዛመት በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

አንበጣዉ በተከሰተባቸዉ በቃሉ፣ አርጎባና፣ ወረባቦ ወረዳዎች የመከላከል ሥራዉ ወጣቶችን፣ የግብርና ባለሙያዎችን፣ ተማሪዎችን እና ባለሃብቶችን በማስተባበር እየተሠራ ሲሆን የፌዴራል መንግሥት ኬሚካል ለመርጨት የላከው አውሮፕላን ብልሽት በማጋጠሙ ነዋሪዎች ባህላዊ መንገድን ተጠቅመው ሰብላቸውን በመከላከል ላይ ይገኛሉ። ድንጋይ በመወርወር፣ ጅራፍ በማጮህ፣ ጥይት በመተኮስ እና የአንቡላንስ ድምፅ በመጠቀም የአንበጣውን መንጋ ለመበተን ጥረት እየተደረገ ነው።
‹‹የአንበጣው መንጋ በዚህ መንገድ ማስወገዱ ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚሰጥ ባለመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ሊያድረግ ይገባል›› ሲሉ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ አምሳሉ ጎባው ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ባህላዊ መንገዱ የአንበጣው መንጋ ካለበት ቦታ አባሮ ሌላ ቦታ ላይ እንዲሰፍር ከማድረግ ባሻገር አዲስ የተፈለፈሉ ኩብኩባዎችን በዘለቄታው ማጥፋት የሚያስችል ስላልሆነ አስተማማኝ አይደለም›› ብለዋል።

በዘለቄታዊነት የአንበጣውን መንጋ ለማጥፋት ስፋት ያለው የኬሚካል ርጭት ለማከናወን የክልሉ መንግሥት አቅም የሚፈቅደው ባለመሆኑ የፌዴራል መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ሲልም ክልሉ ጠቅሷል።

መንጋውን ለመከላከል የወሎ ዩኒቨርሲት ተማሪዎች እና ሠራተኞች እንዲሁም የአካባቢው ወጣቶች እና አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ እስካሁን በመከላከል ሥራው ላይ ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል ተብሏል።

የክልሉ መንግሥት የመከላከል ሥራውን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያደረገ መሆኑም ተገልጿል። የፌዴራል መንግሥት ከ ጎረቤት ሀገራትም ጭምር አውሮፕላን በመጠየቅ ድጋፍ ካላደረገ በሰብል ምርቱ ላይ ከፍተኛ አደጋን የሚያመጣ ነው ሲሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ አምሳሉ ጎባው ተናግረዋል። አክለውም አካባቢዎቹ በከፍተኛ ደረጃ የማሽላ ምርት የሚያመርቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች በሰብል ላይ ጉዳት እንዳደረሰ የተናገሩ ሲሆን፤ በአፋር ክልል በኩል በአዉሮፕላን የሚደረገዉ ርጭት በመቋረጡ በቀጣይ ቀናትም ጉዳት ማድረስ ሊቀጥል እንደሚችል እና የመከላከል ሥራዉን ከባድ ሊያደርገዉ እንደሚችል ገልጸዋል።

እስካሁንም 935 ሄክታር መሬት በ አውሮፕላን እንዲሁም በሰው ኀይል 2269 ሄክታር መሬት 1665 ሊትር ኬሚካል በመጠቀም የተረጨ ሲሆን በ አጠቃላይ ከ 3ሺሕ ሄክታር በላይ መሬት ለመሸፈን ተችሏል።

ሆኖም በአርሶ አደሮች ላይ መደናገጥ ተፈጥሯል ያለው የክልሉ መንግሥት፣ በአስቸኳይ ተገቢውን ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።
በተመሳሳይም የአፋር ክልል በፌዴራሉ መንግሥት ድጋፍ በአዉሮፕላን ሲደረግ የነበረዉ ርጭት በአውሮፕላኑ ርጭት ካልተካሔደ ሁኔታዉ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል በተመሳሳይ ትኩረት እንዲሰጠው ክልሉ ጥያቄውን አቅርቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com