የአራዳ ምድብ ችሎት በኹለት ወር ውስጥ ወደ አዲስ ሕንፃ ሊዘዋወር ነው ተባለ

Views: 131

በተለምዶ ስሙ ማዕከላዊ ተብሎ ለሚጠራው የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ እና የማሰቃያ ቤት እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ማረፊያ ቤት ባለው ቅርበት የተነሳ ትልልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸውን ሃገራዊ መዝገቦች ሲያስተናግድ የቆየው የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በታህሳስ ወር ውስጥ ወደ አዲስ ህንጻ ሊዘዋወር ነው።

በጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስገንቢነት በየካ ክፍለ ከተማ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ከፍ ብሎ የተገነባው ባለ 10 ፎቅ ህንፃ ውስጥ የተወሰነውን ቦታ ለአራዳ ምድብ ችሎት እንደሚሰጥም በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የጠቅላላ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኤፍሬም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የህንፃው ግንባታም 96 በመቶ መጠናቀቁን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያስረዳል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሚያስገነባቸው የተለያዩ ህንፃዎች የችሎት ቦታዎችን ያካተቱ ሆነው እንዲገነቡ ታስቦ እንደሚሠራ የተናገሩት ኀላፊው፣ ከእስከ ዛሬው በተለየ መንታ ህንጻዎችን በመገንባት የሕግ አስፈፃሚውን ከችሎቶች ለመለየት መታሰቡንም ጨምረው ገልፀዋል።

የመጀመሪያው የአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት በመሆን ያገለገለው እና በጭቃ ቤቶች የታነጸው ግቢ እጅግ በፈራረሱ፣ በቂ ብርሃን በማይገባባቸው ክፍሎች ውስጥ የችሎት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። የምግብ ቤት እና ሬጅስትራር መስኮቶች እና በሮችም ጥንካሬ የሌላቸው እና ግድግዳውም የፈራረሰ በመሆኑ ለሥራ የማይመች ከመሆኑ ባሻገር የመዝገቦችን ደኅነት አደጋ ላይ ይጥላል።

ፍርድ ቤቱ ለቆ ሊወጣ ባለመቻሉ ሲንከባለል የቆየው የቅርሱ እድሳትም በ10 ሚሊዮን ብር የሚካሄድ ሲሆን በግቢው ውስጥ የነበሩ ሰነዶችን እና የቋሚ ቅርሱ አካል የሆኑ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዲወጡ ተደርጓል። በ2012 በጀት ዓመት እድሳት እንዲደረግላቸው በጨረታ ላሸነፉ ድርጅቶች ከተሰጡ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ግቢ ተዛማጅ ከሆኑ ቅርሶች እና ታሪኮች ጋር በማያያዝ ለሕዝብ ክፍት እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ለኣዲስ ማለዳ አስታውቋል።

‹‹የቀድሞ አገልግሎቱን እና በአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሚደረግለት ጥገና የተለያዩ አገልግሎቶችን በማጠቃለል በከተማዋ እንዳሉ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች አንዱ እንዲሆን እንሠራለን›› ሲሉ በቢሮው የቅርስ ቁጥጥርና ምዝገባ ኃላፊ ደረጄ ስዩም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ህንጻዎችን በሚያስገነባበት ወቅትም ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተወሰነ ቦታዎችን ማመቻቸት የተለመደ አሰራር መሆኑንም ኤፍሬም ገልፀዋል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግም በተመሳሳይ ለችሎቶቹ ቦታ ማመቻቸቱን እና ወደ ፊትም ይህንን ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በፍርድ ቤቱ ውስጥም ችሎቶች የሚገኙ ሲሆን በተለይም ከዚህ ቀደም የፖለቲካ እስረኞችን ለመያዝ እና ለማሰቃየት በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለውን ማዕከላዊ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአቅራቢያው በመገኘቱ አማካኝነት ትልልቅ ሃገራዊ ትኩረት የሳቡ ጉዳዮችን የጊዜ ቀጠሮ ችሎቶች ሲያስተናግዱ ቆይተዋል።
በአሁኑ ጊዜም በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ የተደረጉ የመፈንቅለ መንገሥት ሙከራዎችን በተመለከተ ተጠርጥረው ያሉ እስረኞችን ጉዳይ ጨምሮ የአገር ውስጥ እንዲሁም ዓለማቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት የሚሰጣቸው መዝገቦችን በፈራረሱ እና ባረጁ ጭቃ ቤቶች ውስጥ የሚቻልበት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com