አዳዲሶቹ ጥምረቶች – እጅ ከምን

Views: 380

ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ በሕዝብ ተቃውሞ ከፊት ተሰላፊውን ቡደን ቀይሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ከቀድሞ በተለዩ የፖሊስ እና የፖለቲካ ለውጦች አገር ማስተዳደር ከጀመረ ዓመት ከመንፈቅ አለፈው። ይህ ለውጥ ካስተናገዳቸው አዳዲስ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው ደግሞ ከዚህ ቀደም በዐይነ ቁራኛ ሲታዩ ከሰነበቱት፤ አሸባሪ ተብለው ተሰይመው በትጥቅ ትግል እስከ ቆዩት ድረስ እርቅ ማካሔድ ድረስ ያሉት ይነሳሉ። ተባብሮ የመሥራት ሙከራዎች አንዳንዴ እንደ ስኬት አልፎ አልፎም እንደ ፈታኝ ሒደት ሆነው ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለመንግሥት የቤት ሥራ መስጠታቸው አልቀረም።

ግንባር ቀደም ተብለው ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው ልዑክ “ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል ወደ ሰሜን አሜሪካ ያደረገው ጉዞ እና ውጤቶቹ ናቸው። የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮችን ጨምሮ ከተለያዩ ፖለቲከኞች ጋር ውይይት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነበር።

ተመሳሳይ ውይይቶች ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች ጋርም በማድረግ ወደ አገር እንዲመለሱ እንዲሁም ጥርጣሬዎችን በማስወገድ የለውጡ ደጋፊ እንዲሆኑ የተደረጉ ሙከራዎች በመጠኑም ቢሆን የተሳኩ ነበሩ ለማለት ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን በማገልገል ላይ ያሉትን ብርቱካን ሚደቅሳን፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑትን ጃዋር መሐመድን፣ የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋን (ፕሮፌሰር) እንዲሁም ሌሎች ከአገር ሸሽተው የቆዩ የፖለቲካ ሰዎችን ወደ አገር ቤት ጠቅልው እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል።

ቀጥሎም የቀድሞው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በነበሩት ለማ መገርሳ በወርሃ ሐምሌ 2010 ወደ ኤርትራ በማምራት ከኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ጋር ያካሔዱት ድርድርም የኦነግ/ሸኔ ሠራዊት እና የፖለቲካ አመራሮቹ እንዲመለሱ አስችሏል።
ታዲያ አጀማመሩ ላይ እንዲህ የሰመረው እርቅ እና የትብብር ጉዞ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሞቅ እና ቀዝቀዝ ሲል ሰንብቷል። እነዚህ ትብብሮችም በስምምነት ሲታሰሩ ተመልክተናል። በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ “አብሮ የመሥራት ውል” ሲፈራረሙ ከርመዋል ቢባል ማጋነን አይሆነም። የስምምነቶቻቸውን ይዘት፣ ዓላማ እንዲሁም ውጤት ለመገምገም እንዳይቻል ግን አብዛኛው ውል በተዘጉ በሮች ጀርባ የተደረጉ መሆናቸው ለፖለቲካ ተንታኞች እንዲሁም ለተፈራራሚ ወገኖች ጭምር ችግር መፍጠሩ የሚታወስ ነው። የውል ነጥቦች ይፋ እንዲወጡም ተፈራራሚ ወገኖች መጠየቃቸው ይታወሳል።

በቁጥር በርከት ያሉ የፖለቲካ ተዋናዮችን የሚያስተናግደው የኦሮሚያ ክልል ‘ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ’ (ትርጉሙ ቢቀመጥ?) በሚል ሥያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ምሁራንን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ጭምር በማካተት ከኹለትዮሽ ስምምነቶች በዘለለ አምስት የፖለቲካ ድርጅቶችን ያጣመረ “ጥላ” መስከረም 20/2012 በስካይ ላይት ሆቴል መሥርቷል።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ጨምሮ አምስት ፓርቲዎች በአባልነት የመሠረቱት ይህ ጥምረት ምን ይመስላል የሚለውን ከመፈተሽ እንጀምር።

ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ
የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ይህ ስብስብ ግርድፍ ትርጉሙ <<የኦሮሞ መሪነት ጥላ>> ማለት ነው። ይህ ስድስት ወራትን ያህል በፈጀ ድርድር እና ውይይት ተመሥርቷል የተባለው ጥላ በ15 አጀንዳዎች ላይ በመስማማት ለመሥራት እና ይህንንም ለማስፈጸም በሚረዱ የሥነ ምግባር ደንቦች ላይ ስምምነት ላይ ደርሶ ጉዞውን አንድ ብሎ ጀምሯል።

ከ15ቱ አጀንዳዎች መካከልም የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ተብለው የተለዩ የቋንቋ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የመጪው ምርጫ እና የሰላም እና የመረጋጋት ጉዳዮች ዋና ዋና ስምምነት አጀንዳዎች እንደሆኑ የኦፌኮ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ይናገራሉ።

“ከመጠላለፍ እና ከግጭት በፀዳ መልኩ በመነጋገር እና በመደራደር ችግሮችን ለመፍታት በማለም የምንተዳደርበትን ደንቦችን በመንደፍና ቃል ኪዳን በመግባት የሠለጠነ የፖለቲካ ምኅዳርን ለመፍጠር በማለም ጥላው ተመሥርቷል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህ ጥምር ውስጥ የአምስቱ ፓርቲዎች አባል ያልሆኑ ሰዎች ያላቸው ተሳትፎ ምን ድረስ እንደሆነ ያብራሩት መረራ፣ የማማከር እንዲሁም ሒደቱን የማሳለጥ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቅለል አድርገው ገልፀዋል። ጥምረቱ ወደ አንድ ፓርቲ የመምጣት ወይም የመዋሐድ ግብ ይዞ እንዳልተነሳ እና በእያንዳንዱ ፓርቲ መልካም ፈቃድ ላይ የሚመሠረት የድርጅቶች ውሳኔ እንጂ የስብስቡ ዋነኛ ዓላማ እንዳልሆነም ተናግረዋል።

“ለውጡ የተሳካ ሆኖ በአገራችን የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን ማድረግ ዓላማችን ነው” ያሉት መረራ “ኦሮሚያ ክልል የአገሪቱ ትልቁ ክፍል እንደመሆኑ በዚህ አካባቢ የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲመጣ ማድረግ ለመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥቅም አለው” ሲሉ የጥምረቱን ተግባር በታለመው መሰረት የሚሔድ ከሆነ ስለሚያመጣው ውጤት ያብራራሉ።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት መረራ፣ ኦሮሚያ ክልል ላለፉት 30 ዓመታት ግጭት ያላጣው ክልል እንደመሆኑ ይህ የሕዝቡን ሕይወት እንዲመሰቃቀል ያደረገ፣ ቀጠናውን በግጭት የተሞላ እንዲሆን፣ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ እና ለተለያዩ ቀውሶች ዳርጎ አልፏል ሲሉም ይናገራሉ።

“ምንም እንኳን የጥምረቱ ውጤት በተግባር የሚታይ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ሁሉም ተቻችሎ፣ ተሰባስቦ እና የነፃነቱን ያክል ተጠቅሞ እንዲሔድ እንዲያስችል ሆኖ ተቀርጿል” ሲሉ መረራ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ሽግግር ወሳኝ በሆነ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኑ በመገባደድ ላይ ባለው ጥቅምት ወር እንደተከሰው ዓይነት ግጭቶች እንዲነሱ አድርጓል ያሉት ሊቀመንበሩ “ኦሮሚያ ውስጥ የትጥቅ ትግል የሚያካሒዱ ቡድኖች አሉ፣ እነዚህ ነገሮች በቀላሉ ይፈታሉ ብሎ መገመት ስለሚያስቸግር ሁሉም የድርሻውን ለችግሩ መፍትሔ መዋጮ ቢያደርግ የሚረዳ በመሆኑ መደራደር [እና] መወያያት አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ። “ይህ ማለት ግን ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን በ24 ሰዓት ያስወግዳል ማለት አይደለም” እንደ መረራ ገለጻ።

“የጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ ሚና ለውጡን በሚደግፉ ኀይሎች የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተለይም የተቋማት ግንባታ ላይ የሚያተኩር ነው” በማለት የኦነግ ቃል አቀባይ የሆኑት ቶሌራ አደባ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። “አስተማማኝ ሰላም ማምጣት ቁልፍ የሕዝብ ጥያቄ ሆኖ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ይህንን ከባድ ኀላፊነት ለመንግሥት ብቻ የምንተው ሳይሆን ሁሉም ድርጅት ርብርብ የሚያደርግበት ነው” ሲሉ ይናገራሉ። “ድርድሮች በሙሉ አንድ ዓላማ አላቸው ይህም የኦሮሞ ትግል ሌሎችን ያቀፈ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓትን መገንባት እንዲችል ማድረግ ነው” ይላሉ።

ቶሌራ በዴሞክራሲ መርህ መሰረት ብዙኀኑ አነስተኛ ቁጥር ያለውን እንዳይጨቁን ማድረግ የጥምረቱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አብራርተዋል። ከዚህ ቀደም የነበረው ኢሕአዴግ የአመራር ዕድሜውን ለማራዘም ሲል የዘራቸው ቁርሾዎች አሁንም አልተወገዱም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

አሁን አሁን እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እና ያለውን የለውጥ መንገድ ማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላትን መልክ በማስያዝ ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲቀጥል የማድረግ ዓላማ የያዘ ስብስብ መሆኑንም አብራርተዋል። ስድስት ወራትን የፈጀ ውይይት ተደርጎ ተመስርቷል የተባለው ጥምረት እያለ፤ በክልሉ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶች ተባብሰው መቀጠላቸውንም እንደ ፈተና የሚያዩት ቶሌራ፤ ይህም ችግሮቹ በአንድ ሌሊት ያልተፈጠሩ እና በአንድ ሌሊት የማይጠፉ መሆናቸውን ያመላክታል ብለዋል።

ስለ ኢሕአዴግ ውሕደት ጉዳይ ጥምረቱ እንደማይወያይ መረራ የጠቀሱ ሲሆን ቶሌራም “ምንም እንኳን የኢሕአዴግ ጉዳይ የአገር ጉዳይ ቢሆንም ፓርቲው ድርጅታዊ ነፃነቱን ተጠቅሞ የውሕደቱን ጉዳይ እንዲወስን የምንተወው እንጂ በጋዲሳ ሆገንሳ ጠረጴዛ ላይ ቀርቦ የምንወያይበት አይሆንም” ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ፓርቲዎች የምክክር ጉባኤ
ከአንድ ሳምንት በፊት በአማራ ምሁራን መማክርት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የተመሠረተው የአማራ ፓርቲዎች የጋራ የምክክር ጉባኤ ሦስት የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን እና የምሁራኑን ጉባኤ በማቀፍ ነው። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እንዲሁም የአማራ ማኅበራዊ ራዕይ ግንባር (አማራግ) ያቀፋቸውን አምስት ፓርቲዎችን አጠቃሎ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱንም ጉባኤው በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።

“ከዚህ ቀድም በተደረጉ ስምምነቶች ላይ እንደነበረው አሁንም ያለው የአማራ ሕዝብ ጥቅሞች ላይ በየወሩ እየተገናኘን የምንወያይበት ጉባኤ ቢሆንም የፉክክር ግብዓቱ ግን ይቀራል ማለት አይደለም” ሲሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። “ነገር ግን የምንስማማባቸው ጉዳዮች በማመዘናቸው ምክንያት በጋራ ለመሥራት እንድንስማማ አድርጎናል።”

እስከዛሬ በተለይ በአብን እና በአዴፓ መካከል ከተደረጉ ስምምነቶች በተለየ ሌሎች በአማራ ራዕይ ግንባር ሥር ያሉ ፓርቲዎችን ማጠቃለሉ አንዱ ሲሆን እንደ ደሳለኝ ገለጻም በቋሚነት በየወሩ የሚደረግ ጠንካራ የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱም ነው።

“ከመጠላለፍ፣ ከመነታረክ፣ እርስ በእርስ ሥም ከመጠፋፋት እንዲሁም ከተለመደው የፖለቲካ መደነቃቀፍ በመውጣት ችግሮች ሲኖሩ በውስጥ በመነጋገር የአማራ ሕዝብን ጥቅም እና ትግል ወደ ፊት ማራመድ ዋና ዓላማችን ነው” ሲሉ ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። “ይህ ሲባል ግን ሁሉም ነገር አንድ ሆነ ወይም ውሕደት ተፈጠረ ማለት አይደለም፣ እንደሚታወቀው አዴፓ አዲስ በሚፈጠረው የኢሕአዴግ ውህድ ፓርቲ ውስጥ ቢገባም እየተመካከርን ለአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄዎች መፍትሔ የምንፈልግበት ነው” ሲሉ አክለዋል።

“ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ እንዲሁም ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የአማራ ሕዝብን የአካል እንዲሁም የንብረት ደኅንነት ለማስጠበቅ የምንሠራቸው ሥራዎችም ቅድሚያ የምንሰጣቸው ናቸው” ብለዋል።

የአማራ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ አንጓ በመሆኑ በአማራ ፖለቲካ ውስጥ የሚፈጠር መስከን እና ከመጠላለፍ መውጣት ለኢትዮጵያ የራሱ አስተዋፅዖ አለው የሚል እምነት በአብን ዘንድ መኖሩን ሊቀመንበሩ ያስዳሉ። የሌሎች ብሔር ፓርቲዎች የጀመሯቸው ተመሳሳይ ጅማሮዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ መስመር እየያዙ ከሔዱ የአገሪቱን ፖለቲካ የማስከን እና ከጭቃ መቀባባት ፖለቲካ ወደ መደማመጥ ፖለቲካ ለመሸጋገር የራሱን አስተዋፅዖ ያበረክታል ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

በቀዳሚ ጉባኤው ለቀጣይ ስብሰባው የአጭር፣ መካከለኛ እና የረጅም ጊዜ የአማራ ሕዝብ የትግል ግቦች ምን እንደሆኑ ለማስቀመጥ ተመካክሮ መለያየቱንም ለማወቅ ተችሏል። የአማራ የፖለቲካ አጀንዳዎችን በጠራ መንገድ መዘርዘር እና እንዴት በቅደም ተከተል መፍታት ይቻላል የሚለው ላይም ለመነጋገር እንደሚያስፈልግ የአብን ሊቀመንበር ተናግረዋል።

በተመሳሳይም እንዲህ ዓይነት መሰባሰቦች ለሕዝብ የሚጠቅሙ እና ወደ ፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ኅብረቶችን የማፋጠን ሚና ይኖራቸዋል ሲሉም ደሳለኝ ይናገራሉ።
በተመሠረተው የአማራ ፓርቲዎች የምክክር ጉባኤ አንዱ አጀንዳ መጪው ምርጫ ሲሆን ምርጫውን ከኹከት የፀዳ ማድረግ አንዱ ዓላማው ሆኖ ተቀምጧል።
“መጪው ምርጫ ምንም ዓይነት ይሁን ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን አባሎቻችን እንዲሁም ደጋፊዎቻችን ውጤቱን እንዲቀበሉ የማገዝ ሥራ የምንሠራበት መድረክ ሆኗል” ሲሉ ደሳለኝ ጫኔ ተናገረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ እና የፖለቲካ ተንታኝ እና ተመራማሪ አደም ካሴ (ዶ/ር)፣ ጥምረቶቹ በተለይም በክልሎች ውስጥ ለሚፈጠሩ ያለመስማማቶች መፍትሔ ያመጣሉ ሲሉ ይከራከራሉ። በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ ያለመግባባቶችን ለመፍታት እና በውስጥ ያልተፈቱ ጉዳዮች ላይ በመደራደር መስማማት ላይ ለመድረስ የማይተካ ሚና ይዞ ይመጣል ሲሉ ያክላሉ። በክልሎች መካከል ድርድሮችን ከማካሔድ በፊት የውስጥ አጀንዳዎች ላይ መስማማት ላይ በመድረስ እንደ ሀገር ለሚደረጉ ውይይቶች የራሱ መሰረት እንደሚጥል ለአልጀዚራ በጻፉት አስተያየታቸው ላይ አስፍረዋል።

‹‹ብሔሮች በውስጣቸው እያጋጠማቸው ያሉ ያለመስማማቶች ለከፋ ግጭቶች እያጋለጡ ስለሆነ በውስጥ ያሉ ልዩነቶችን እንዲሁም በተለያዩ ብሔሮች መካከል ያሉ ያለመግባባቶችን ልሂቃን በመነጋገር እና በመደራደር መፍታት ይገባቸዋል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በይፋ ከተመሠረቱት ኹለት ጥምረቶች ባሻገር በሶማሌ ክልልም ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት የጀመሩ ሲሆን በቅርቡ ተመሳሳይ ጥምረት ይመሠርታሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአፋር ክልል ያሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደተናገሩትም ኹለት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ምሁራን ተመሳሳይ ጥምረት በወራት ጊዜ ውስጥ ይመሰርታሉ።
አዲስ ማለዳ ከአዴፓ እና ኦዴፓ የሥራ ኀላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com