መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ እና የተጠያቂነት ደረጃ

Views: 1721

በጥቅምት 11/2012 ጀምሮ ለቀናት የዘለቀው ከፊል የአዲስ አበባን አካባቢዎች በጥቂቱ የዳሰሰው እና በአብዛኛው የኦሮሚያ ከተሞች የተከሰተው እና መንግሥት ባመነውና ባስታወቅው መሰረት የ86 ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት የቀጠፈው ችግር የመንግሥትን ቸልተኝነት የሚታይበት አጋጣሚ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ። በተለይ ደግሞ በአዳማ ከተማ በውል ሚታወቁ 16 ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈው ግጭት በስፍራው ለነበረው የጸጥታ መዋቅር ከአቅሙ በታች እንጂ በላይ እንዳልነበር ሥሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳል። ስለ ሁኔታው ሲናገር ግጭቱ በተከሰተበት ወቅት የከተማው ፖሊስ እና የክልሉ ልዩ ኀይሎች ዳር ሆነው ይመለከቱ እንደነበር በዓይኑ የተመለከተውን ተናግሯል። “መንግሥት ብጥብጡን ይፈልገዋል እንዴ? የሚል ሐሳብም በብዙ ሰዎች ሲታሰብ ነበር” ሲልም ገልጿል።

ለዚህ ደግሞ እንደተጨማሪ ማሳያ እንዲሆን ከዚህ ቀደም በቡራዩ መስከረም 2011 ላይ በተፈጠረ ግጭት ቤት ንብረቱ ትቶ ልጆቹን እና ሚስቱን ይዞ ስለተፈናቀለው እና አሁንም ድረስ በአዲስ አበባ ስለሚኖረው ግለሰብ ከአዲስ ማለዳ ጋር ያደረጉትን ቆይታ ቀንጭበን እናቅርብ።

ነጋ ዘብሮ (ሥሙ የተቀየረ) ወልዶ ከብዶ ከኖረባት ቡራዩ በመስከረም 2011 በከተማው የተከሰተውን ግጭት እና ዘርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ተከትሎ ኹለት ልጆቹን እና ባለቤቱን ይዞ ወደ አዲስ አበባ ለመሰደድ መዳረጉን ይናገራል። ነጋ ስለ ነበረው ሁኔታ ሲገልጽ በቁጭት እና በተስፋ መቁረጥ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።
ከመስከረም 2011 በፊትም ጥቃቶች ጎልተው አይውጡ እንጂ በተደጋጋሚ ይደርሱ ነበር። ዘርን መሰረት ያደረጉ፣ ሃይማኖትን የተመረኮዙ ግን ደግሞ ይፋ ያልወጡ ጥቃቶች በተደራጁ ቡድኖች ይሰነዘሩ እንደነበር ነጋ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ይሁን እንጂ በመስከረም 2011 በቡራዩ የደረሰው ግን ከምንጊዜውም የከፋ እንደነበር በምልሰት “ሰው የሚገድሉትን አለፍኩ ስትል ቤትህን በእሳት ያያይዙታል፣ ከእሳቱ ለማምለጥ ወደ ውጭ ስትወጣ ደግሞ ቤቱን ያቃጠሉት ሰዎች ዱላ እና ስለት ይዘው ይጠብቁሃል” ሲሉ በሐዘን በረበበት ቅላፄ ይተርካል። እንደ ነጋ ገለፃ ነገሩን የባሰ አደገኛ ከሚያደርጉት ዋናው በአካባቢው የነበሩ የጸጥታ ኀይል አባላት ጥቃቱን መተባበራቸው አሊያም ባይተባበሩ እንኳን ግዴታቸው የሆነውን ጸጥታን የማስከበር ኀላፊነታቸውን በቸልተኝነት አለመወጣታቸው ነው።

የሆነው ሆኖ ነጋ ባለቤቱን እንዲሁም በ10 እና በ12 ዕድሜ ላይ የሚገኙትን ኹለት ወንድ ልጆቹን ይዞ ወንደሙ ወደሚኖርበት አዲስ አበባ መሸሽን መርጧል። ከዓመት በላይ ከቀዬው ርቆ የቆየው ነጋ መንግሥት የተፈናቀሉትን በመመለስ ረገድ በርካታ ሥራዎችን ሰርቻለሁ ቢልም በጊዜው በቡራዩ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ አሁንም ወደ ቀያቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ እንዳላስቻለ ነጋና መሰሎቹ ማሳያ ናቸው።
በሱቅ የችርቻሮ ንግድ ሥራ ይተዳደር ለነበረው ነጋ አሁን መርካቶ በሚገኘው ወንድሙ ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ በመሥራት ላይ ይገኛል። “ባለቤቴ ወደ ቡራዩ በተደጋጋሚ በመሔድ ቤታችን ያለበትን ሁኔታ እየቃኘች ትመለሳለች እንጂ ጠቅልለን ለመመለስ ሥጋታችን አለቀቀንም። ሱቃችን ተቃጥሏል፤ ነገር ግን መኖሪያችን ብዙም ጉዳት ስላልደረሰበት በርካሽ ዋጋ አከራይተነዋል” ሲል ተናግሯል።

የነጋን ታሪክ እንደማሳያ አስቀመጥን እንጂ አዲስ ማለዳ በርካታ ግጭቶች በተከሰቱባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውራ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን እንዲሁም በተፈጠረው ግጭት ወዳጅ ዘመድ ፣ የቤተሰብ አባል ያጡ ግለሰቦችን በማነጋገር በርካታ አስተያየቶችን ለመሰብሰብ ችላለች።
በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ ከወራት በፊት በመገኘት ለመታዘብ እንደተሞከረው በርካታ የጌዴኦ ብሔር ተፈናቃዮች ተጠልለውበት የነበረ ቦታ ነበር። በዚህ ስፍራ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ከምዕራብ ጉጂ የተፈናቀሉ የጌዴኦ ብሔር ተጠልለውበት የነበረ ሲሆን አዲስ ማለዳ በደረሰችበት ግንቦት 2011 በተወሰነ ደረጃ መንግሥት ወደ ነበሩበት ስፍራ የመመለስ ሥራ የሠራ ቢሆንም በዛው በገደብ ወረዳ በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ ከኹለት መቶ በላይ ሰዎች ንፅሕናው ባልተጠበቀ እና ለመኖር ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ይኖሩ እንደነበር ታዝባለች።

በተመሳሳይም በጌዴኦ ዞን ጭርቁ ሳይት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዞኑ በዋናነት ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ጋር በቅርበት የሚዋሰንበት አካባቢ ነው። በዚህም ስፍራ የኦነግ ታጣቂዎች ከቤት ንብረታቸው አፈናቅለው፣ ቤተ እምነቶቻቸውን ጨምሮ መኖሪያቸውን በማቃጠል እንዳፈናቀሏቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ በሥፍራው የሚንቀሳቀሰው ወርልድ ቪዥን የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሠናይ ድርጅት ከግሎባል አሊያንስ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ 500 መኖሪያዎችን ገንብቶ ወደ ቀያቸው መመለስ ችሎ ነበር። በወቅቱም አዲስ ማለዳ ተመላሾችን በስፋት ለማነጋገር ችላም ነበር። ከተመላሾችም መካከል በወቅቱ ሥጋት እንዳለባቸው እና በየትኛውም ጊዜ እና ሰዓት ጥቃት ሊሰነዘርባቸው እንደሚችል የሚያስቡ እንደነበሩ ታዝባለች፤ ምክንያታቸው ደግሞ መንግሥት በአካባቢው በቂ የደኅንነት ከለላ ለማድረግ አለመቻሉን በሥጋት ተውጠው አጋርተዋል። አዲስ ማለዳ በወቅቱ በአካባቢው አንድ በሻለቃ ደረጃ የተዋቀረ የመከላከያ ሠራዊት መኖሩን የታዘበች ቢሆንም የመከላከያ ኀይሉ በሰፈረበት ስፍራ በአጭር ርቀት ውስጥ ሰዎች ይገደሉ ወይም ጥቃት ይደርስባቸው እንደነበር ታዝባለች። ይህንንም በማስረጃ ለማስደገፍ ያክል አዲስ ማለዳ በሥፍራው በተገኘችበት ወቅት አንድ ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተወግቶ የተገደለበትንና መንደሩ በሐዘን ድባብ ተውጦ የነበረበት ሁኔታን መጥቀሱ የሥጋቱን ነባረዊነት ማረጋገጫ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።

መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት እና ሰላም ማረጋገጥ ዋነኛ ኀላፊነቱ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው ስርዓት አልበኝነት ግን ለአብዛኛው ዜጋ የወጥቶ መግባት ሥጋት እንዲያድርበት ሆኗል። በአራቱም የኢትዮጵያ ክፍል በአንጻራዊነት ሰላም የሚታይባቸው አካባቢዎች ቢኖሩም በርካታ ዜጎች ግን ከዛሬ ነገ ምን ይከሰታል በሚል ሥጋት ውስጥ መሆናቸው ነባረዊ ሃቅ ነው፤ የአገር ሕልውናም ቀጣይነትም አሳሰቢ ሆኗል።

ከዚሁ ከደቡብ ክልል ሳንወጣ በጉራጌ ዞን መስቃንና ማረቆ ወረዳ የተቀሰቀሰው ግጭት በየዕለቱ የንፁሐንን ሕይወት እንደሚቀጥፍ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አሁንም ይናገራሉ። ከአካባቢው ተወክለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሁሴን ዳሪ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ኅብረተሰቡ የመንቀሳቀስ ሥጋት ውስጥ መሆኑን እና ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ መርገብ ሲኖርበት ጭራሹኑ እየተባባሰ መምጣቱን ገልፀዋል። በጉዳዩ ላይ ሰላም ሚኒስቴር ድረስ የአካባቢው አባቶች ገብተው ቢያነጋግሩም ተገቢውን ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ እና በስፍራው የመከላከያ ኀይል ቢሰማራም የተጠበቀውን ያህል ጥበቃ እያደረገ እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

እንደ ሁሴን ዳሪ አስተያየት የሕዝብ መጓጓዣዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል፤ ይህንም ተከትሎ አሽከርካሪዎች አገልግሎት ለመስጠት የማይደፍሩባቸው አካባቢዎች ከመኖራቸው የተነሳ ኅብረተሰቡ ለትራንስፖርት ችግር መጋለጡንም ጨምረው ገልፀዋል።

ወደ ምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍልም ይህ ችግር ያልዳሰሰው አካባቢን ማግኘት የሚከብድ እስከሚመስል ድረስ የግጭቶች ሰለባ የሆኑ ንፁሐንን ማግኘት ቀላል ነው። አዲስ ማለዳ ወደ ጥንታዊቷ የሐረር ከተማ በተጓዘችበት ወቅት ሒርና በተባለ አካባቢ የተሸከርካሪው ጎማ በመፈንዳቱ ለመቆም ተገደን ነበር። በጊዜው ታዲያ ዕድሜያቸው ከ17 እስከ 20 የሚደርሱ ታዳጊዎች ሜንጫ ድምጽ አልባ መሣሪያቸውን ይዘው በመክበብ ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ቢሆንም ጋዜጠኞች መሆናችንን ስለተነገራቸው መረጋጋት አሳይተውን ሔደዋል።

በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚመላለሱት አሽከርካሪዎች የዓይን እማኝ በመሆን ከታዘቧቸው ኹነቶች በጥቂቱ ለአዲስ ማለዳ ሲያጋሩ፥ በአካባቢው ምንም ዓይነት የመንግሥት የጸጥታ መዋቅር ያለ እስከማይመስል በርካታ ዝርፊያዎች እና ግድያዎች እንደሚከሰቱ፤ አሽከርካሪዎችም የዝርፊያውና የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን በወቅቱ ገልጸዋል። ይህንም በመፍራት የረጅም ርቀት የከባድ መኪኖች አሽከርካሪዎች ተከታትለው በሰልፍ (በ‘ኮንቮይ’) ለመጓዝ እንደተገደዱ እንዲሁም አንዳንዶቹ ደግሞ የጦር መሣሪያ ለመታጠቅ እንደተገደዱ መናገራቸውን እማኝነት መጥቀስ ይቻላል።

በዚሁ በምሥራቅ ኢትዮጵያ አዲስ ማለዳ ለኹለተኛ ጊዜ በጥቅምት 2012 በድሬዳዋ አድርጋ በሱማሌ ክልል ሽንሌ ዞን ወደ ጅቡቲ ድንበር ባደረገችው ምልከታም የታዘበቻቸው ጉዳዮች አሉ። በድሬዳዋ የጥቅምት 11 ጀምሮ ለቀናት የዘለቀውን አለመረጋጋት ሳይጨምር ለቁጥር የሚያዳግቱ ግጭቶች በአጭር ጊዜ ተስተናግደዋል። ሃይማኖት መልክ የያዙ በተለይ ደግሞ ቤተ እምነቶችን ለማቃጠል የተሞከረበትን ጨምሮ ምዕመናንን ላይ ጉዳት የማድረስ እና መሰል ጉዳቶች ተስተውለው ነበር። በዚህም ወቅት መንግሥት በኀላፊነቱ ልክ የዜጎቹን ደኅንነት ባለማስጠበቁ የንጹሐን ዜጎች ደም ፈሷል፤ በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፤ ንብረት ወድሟል።

በተጨማሪም በርካታ ዜጎችን ደግሞ በከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት ውስጥ ከትቷል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት አካባቢው አንጻራዊ በሚባል መልኩ መረጋጋትን አሳይቷል።
ከድሬዳዋ – ደወሌ በሚዘልቀው የፍጥነት መንገድ ለመድረስ ከድሬዳዋ በ10 ኪሎ ሜትር ርቆ መጓዝን ይጠይቃል። የሆነው ሆኖ ወደ ፍጥነት መንገዱ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ጉዞ በአካባቢው በርካታ የጸጥታ አካላትን መመልከት ብንችልም በፍጥነት መንገዱ መዳረሻ አካባቢ የሚኖሩ ቻናዊያን ግን በተደጋጋሚ ሰዎች እንደሚገደሉ እንዲሁም በካምፓቸው ውስጥ ዝርፊያ መፈፀሙን ጠቁመውናል። በዚህ አካባቢ መንግሥት የሚጠበቅበትን ያህል ጥበቃ እያደረገ ካለመሆኑም በተጨማሪ ስርዓት አልበኝነትን እያየ እንዳላየ መሆኑ ችግሮቹ ሥር እየሰደዱ መመለስ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ የሚደርሱበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ሥጋታቸውን ቻይናዎቹ አጋርተዋል።
ስርዓት አልበኝነት መንሰራፋት፣ የተለያዩ አካባቢዎች ከመንግሥት መዋቅር ይልቅ የጎበዝ አለቆች አስተዳዳሪ መሆን እና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ መንግሥት የሚያሳየው የተለሳለሰ አካሔድ የችግሮቹ ኹሉ ቁልፍ መንስዔ ነው ሲሉም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሕግ ባለሙያዎች እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት በሕዝብ ደኅንነት ከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ ይናገራሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ችግሮች በተከሰቱባቸው የአገሪቱ ክፍሎች በዋናነት የግጭቱ አብራጅ ሆኖ እየተሰማራ የሚገኘው ደግሞ መከላከያ ኀይል መሆኑ ችግሩን በበቂ ሁኔታ እንዳይፈታ ምክንያት ነው ሲሉም ያብራራሉ።

መፍትሔ
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ በኀላፊነት ሲያገለግሉ የነበሩ እና ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ግለሰብ ስለ ጉዳዩ ለአዲስ ማለዳ ሲነገሩ፤ “ሲጀመር መንግሥት ቅድሚያ መስጠት ያለበትን ጉዳይ የሳተው ይመስለኛል” ሲሉ ይጀምራሉ። አያይዘውም ክልሎች ልዩ ኀይል የሚባል የጸጥታ መዋቅር እያላቸው መከላከያ እንዲገባ መፍቀዱ ራሱ የትልቅ ስህተት እንጂ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ያስረዳሉ። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ካላት ውስን የሎጅስቲክ መጠን መከላከያውን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማጓጓዙን ጨምሮ ተጨማሪ ወጪዎችን ማውጣቱ ራሱ ትልቅ ማነቆ እንደሚሆን ጠቅሰው “እንዲያው በልምድ መከላከያ ይግባ ይባላል እንጂ በበቂ የኀይል መጠን ሊሰማራ የማይችልባቸው አካባቢዎች አሉ” ሲሉ ሎጀስቲክ እጥረቱን ተመርኩዘው ያብራራሉ።

ከዚሁ በተጨማሪ ደኅንነት ባለሙያው ስለወቅታዊው የሰላምና ደኅንነት ችግሮች ሲያስረዱ “እየተፈጠረ ያለው ችግር እኮ በደንብ ትኩረት ከተሰጠው፥ ከከተማ ፖሊስ አቅም በላይ አይደለም” ብለዋል። ባለሙያው ምክንያታቸውንም ሲጠቅሱ፥ በከተማው እና በክልሉ ያለውን የደኅንነት መዋቅር ማጠናከር ብቻ ችግሮችን ከመፈጠራቸው በፊት ማፈን እና ባስ ሲልም በፖሊስ መቆጣጠር እንደሚቻል ያስረዳሉ።

የደኅንነት ባለሙያው መፍትሔ ያሉትን ጉዳይ ሲያስቀምጡ፤ “መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ደኅንነት መዋቅር በማጠናከር እና የሚገኘውን የትኛውንም ዓይነት መረጃ ወደ ተግባር በመለወጥ ቅድመ መከላከል ማድረግ ይቻላል” በማለት “ነገሮች ግን ከዚህ ሁሉ አፈትልከው ከተሰቱ ዝም ብሎ በገፍ ከማሰር ይልቅ ለችግሮች መንስዔ የሆኑ አካላትን ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ እንዳይደገም ማድረግ ይቻላል” ሲሉ ያስረዳሉ። “መንግሥት እጅግ ለዘብተኛት የታየበት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ነው፤ ስለዚህ ይህ አሠራሩን በአስቸኳይ በማረም ቁርጠኛ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል” ሲሉ ይመክራሉ።

የደኅነነት ባለሙያው የስርዓት አልበኝነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም የመንግሥት የሕግ ልዕልናን የማስከበር ቸልታን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፤ “ይህን ዓይነት አለመረጋጋቶች አዲስ አይደሉም፤ በየጊዜው የሚከሰቱ ናቸው። ነገር ግን በጊዜው የነበረው አስተዳደር ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ ጠንካራ ሥራ ይሠራ ነበር” የሚሉት ባለሙያው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ አካባቢ በተደጋጋሚ የታጠቁ ኀይሎች በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት ያደርሱ ነበረበትን ጊዜ በመጥቀስ መንግሥት የወሰደው እርምጃ አካባቢውን ለረጅም ዓመታት የጸጥታ እና የሰላም ቀጠና ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎት እንደነበር አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግና አስተዳደር ተመራማሪና መምህር ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ስለ መንግሥት ሕግ የማስከበር አግባብ ያስረዳሉ። “መንግሥት ቸልተኝነት ብቻ ሳይሆን አድሎም እየታየበት ነው” ሲሉ ይጀምራሉ። ቀጥለውም በሕግና በስርዓት አገርን ማስተዳደርና የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ የመንግሥት ግዴታው እንጂ ለሕዝቡ ውለታ እየዋለለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱት ጥያቄዎችን በአግባቡ እና ወቅቱን ጠብቆ አለመመለሳቸው ለችግሩ መንስዔ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚናገሩት ሲሳይ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ግን መንግሥት እንደ መንግሥት ቁመናውን አስተካክሎ ሕግን የማስከበር ኀላፊነቱን መወጣት እንዳለበትና ለነገ የማይባል ሥራው መሆኑን ያስቀምጣሉ።

ሲሳይ፤ በአሁን ወቅት እየታየው ያለው የመንግሥት መለሳለስ በየቦታው ለሚያጋጥመው ዜጎች ሞት ዋነኛ መንስዔ ከመሆኑም ባሻገር በዚሁ ከቀጠለም እንደ አገር ቀጣይ ዕጣ ፋንታው አሳሳቢ እንደሚሆንም መላ ምታቸውን ያስቀምጣሉ።

“ሕግን የሚተላለፉ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፣ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊትም ጠቋሚ ምልክቶችን በመመልከት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም የእከሌ ቡድን ነው፤ የእከሌ ጎሣ ነው ከመባባል ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑን ማስገንዘብ። ያ ካልሆነ ግን አሁንም ያለው የዜጎች መፈናቀል፣ ሞት እና ንብረት ውድመት ተባብሶ ይቀጥላል” የሚሉት ሲሳይ፤ እስከ አሁን የታየው ምናልባትም በጣም ትንሹ ሊሆን እንደሚችልና የወደፊቱን ለመገመት የሚያሰፈራ እንደሆነም ሥጋታቸውን አልደበቁም።

መንግሥት በሕግ ይገደዳል ወይ?
መንግሥት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 እና በአንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተደነገገውን ዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነትን አለበት። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ይህ እየሆነ አለመሆኑ በጉልህ ይታያል። በዚህ ጉዳይ ታዲያ ሕግ ባለሙያው ፊሊጶስ አይናለም መንግስት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ መስነፉ በሕግ የሚያስጠይቅ እና ግዴታም ጭምር መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን መንግስትን በሕግ መጠየቅ በኢትዮጵያ ውስጥ አዳጋች እንደሚሆን ይናገራሉ። አያይዘውም ለዚህ ጉዳይ በዋናነት የሚጠየቀው አቃቤ ሕግ ወይም ፖሊስ ቢሆንም ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚንስትሩ በመሆኑ ነገሮች ተድበስብሰው እንዲቀሩ ምክንያት ናቸው ይላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com