ለተፈናቀሉ ዜጎች ኹለት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ግዢ ሊፈጸም ነው

Views: 457

የመንግሥት ንብረት ግዢ እና ማስወገድ አገልግሎት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ እና ችግረኛ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የሚውል የኹለት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴን ግዢ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ የነበረ ሲሆን በመጪው ህዳር 13/2012 ጨረታው ተከፍቶ ግዢው እንደሚፈፀም ተገለፀ።

በብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንዲገዛ የተጠየቀው ይህን ስንዴ ለመግዛት ጨረታ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም በጨረታው ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶች በጨረታው ሰነድ ላይ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በመጠየቃቸው የስንዴው ግዢ ጨረታ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን አገልግሎቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የጨረታ ሰነዱን ከገዙ 52 ዓለም ዐቀፍ እና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች መካከል አራቱ በጨረታው ላይ ግልፅ ያልሆኑልን ነጥቦች አሉ በማለት ማብራሪያ በመጠየቃቸው ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ ለመስጠት እና ሌሎች ተጫራቾች መሰል ጥያቄዎች ካሏቸው ማቅረብ እንዲችሉ ጨረታው ላልታወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገልጿ ነበር። አብዛኛዎቹ የማብራሪያ ጥያቄዎች በማጓዝ ሂደቱ ላይ እንደሆኑ የመንግሥት ንብረት ግዢ እና ማስወገድ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ መልካሙ ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ማብራሪያ የተጠየቀባቸውን ነጥቦች ግልፅ በማድረግ በአጭር ጊዜ የስንዴ ግዢውን ለመፈፀም እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።

የጨረታው ሰነድ ከመስከረም 10/ 2012 ጀምሮ ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ጥቅምት 18/ 2012 ጨረታው ክፍት እንደሚሆን የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ገልጾ ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com