ዳሰሳ ዘ ማለዳ ጥቅምት 26/2012

Views: 467

1- የጸረ ተባይ መርጫ አውሮፕላን ተደጋጋሚ ብልሽት እያጋጠመው መሆኑ አንበጣን ለመከላከል እንቅፋት እንደሆነበት የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የእድገት ደረጃውን ጨርሶ እንቁላል ለመጣል በሚያስችለው ደረጃ የደረሰውን አንበጣ ለመከላከል የሚከናወነውን ሥራ ፈታኝ ካደረጉት መካከል አንበጣው ያረፈባቸው አካባቢዎች በአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ አመቺ አለመሆናቸውም ጭምር እንደሆነ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። (ዋልታ)
…………………………………………………………….
2-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሱማሌ ላንድ እና በሳዑዲ አረቢያ ቅርንጫፉን ለመክፈት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት አባጫ ጊና አስታወቁ። ከዚህ ቀደም ባንኩ በጁቡቲና በደቡብ ሱዳን ቅርንጫፎች መክፈቱን ያስታወሱት ፕሬዘዳንቱ፣ አሁን ላይ ደግሞ ኹለት ቅርንጫፎች በመክፈት በውጭ የሚገኙ የባንኩን ቅርንጫፎች ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። በቀጣይም ባንኩ ጥናት እያደረገ የውጭ አገር ቅርንጫፎቹን እንደሚያሳድግ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
……………………………………………………………..
3-በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሦስት ወራት በተከሰቱ አደጋዎች የ28 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የከተማዋ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። በ2012 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የወደመው ንብረት 143 ሚሊዮን 797 ሺሕ 310 ብር ሲሆን አምና በተመሳሳይ ወቅት የወደመው ንብረት 18 ሚሊዮን 831 ሺሕ 500 እንደነበርም አስታውሰዋል። በሌላ መልኩ 2 ቢሊዮን 802 ሺሕ 350 ብር ማዳን የተቻለ ሲሆን አምና በተመሳሳይ ጊዜ ማዳን የተቻለው ደግሞ 697 ሚሊዮን 505 ሺሕ የሚገመት ንብረት መሆኑን ገልጸዋል። ባለፉት ሦስት ወራት ለ6 ሺሕ 95 ነዋሪዎች የቅድመ ሆስፒታልና አምቡላንስ አገልግሎት መስጠቱ ታዉቋል። (ኢቢሲ)
……………………………………………………………..
4-በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱትን ኹለት ኢትዮጵያውያን ፍርደኞች ጎበኘ። በሳዑዲ አረቢያ ማረሚያ ቤት ኹለት ኢትዮጵያውያን ዜጎች በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰው ሰሞኑን የሞት ፍርድ የተላለፈባቸው መሆኑ ይታወቃል። ኤምባሲው የፍርድ ውሳኔውን ኮፒ ያገኘ ሲሆን፣ በቀጣይ ሚሲዮኑ ዜጎችን የፍርድ ውሳኔ መቃወም የሚያስችላቸውን ሁኔታ እንደሚያመቻች፣ የይግባኝ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ድጋፍ እንደሚያደርግ እንዲሁም ጠበቃም ቀጥሮ የኢትዮጵያውያኑን ጉዳይ እንዲታይ የሚቻለውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጿል። (ኤፍ ኤም 107.8)
……………………………………………………………..
5-በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ ላይ በሚገኙ የመዝናኛ ፓርኮች በተያዘው በጀት ዓመት ለ9 ሺሕ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑ የአዲስ አባባ የተፋሰስ እና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማት ኤጀንሲ አስታውቋል። በአስሩም ክፍለ ከተሞች በሚገኙት 24 የመዝናኛ ፓርኮች የሥራ እድሉን ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል። (ፋና ብሮድካስቲንግ)
……………………………………………………………..
6- የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ነገ ጥቅምት 27/2012 እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። ቦርዱ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ለማከናወን ባለፉት ቀናት ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል። በተካሔደው ዝግጅትም ከ6 ሺሕ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎችን አሰልጥኖ በትላንትናው እለት ማሰማራት የተጀመረ ሲሆን፣ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ ስርጭትም ሲካሔድ መቆየቱ ታውቋል። (ፋና ብሮድካስቲንግ)
………………………………………………………
7 -የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር “የዕድሜ ባለፀጎችን በመደገፍ እንመረቅ” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀንን በማስመልከት ከመስከረም 8 – 2ዐ/2012 ድረስ ከአገር ውስጥ ለጋሾች ያሰባሰበውን ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አልባሳትና ቁሳቁስ ለአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዛሬ ጥቅምት 26/2012 አስረክቧል። (ኢቢሲ)
………………………………………………………
8-የአውሮፕላን ነዳጅ በጥቅምት ወር ሲሸጥበት ከነበረው በሊትር ብር 26 ነጥብ 63 በዓለም ወቅታዊ ዋጋ መሰረት ተሰልቶ በተገኘው ልዩነት 1 ብር ከ 76 ሳንቲም በመቀነስ በሊትር ብር 24 ነጥብ 87 እንዲሸጥ መወሰኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል። የኅዳር ወር የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባለበት እንደሚቀጥልም ታውቋል። (አዲስ ማለዳ)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com