“እናት እውነት…” ለልደት ካርድ አይሠራም?

Views: 234

ቤተልሔም ነጋሽ በተለያየ ወቅት የኹለት ልጆቻቸውን የልደት ምስክር ወረቀት ለማውጣት ያጋጠማቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ልዩነት መነሻ በማድርግ፥ የወሳኝ ኹነት፣ ምዝገባና ምስክር ወረቀት አሠጣጥ አስቸጋሪነትን አሳይተዋል። የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባና ምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሕጉ ማሻሻል፤ አገልግሎቱም ፈጣን ማድረግ ይገባል ሲሉ ተችተዋል።

 

 

“እናት እውነት፣ አባት እምነት” የሚል የተለመደ አባባል አለ። እናት ዘጠኝ ወር አርግዛ፣ ቀን ቆጥራ፣ ሠፈር ወዳጅ ዘመድ እያየ ስለምትወልድ ስለመውለዷ ጥርጣሬ የሚገባው የለም፣ ፈጣሪ ጠብቆ ትክክለኛ ልጇን ተረክባለች ብለን ብናስብ እናት ስለወለደችው ልጅ ጥያቄ አይመጣባትም ለማለት ነው። አባት እምነት ደግሞ እንደዛሬ ዲ ኤን ኤ ምርመራ ቁርጣችንን ሳያሳውቀን በፊት አባት ነህ የተባለ አባትነቱን መቀበሉ የግድ ነው። የቤተሰብ ህጉም አባትነትን ሲተረጉም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ አለመሆኑን በሳይንሳዊ መንገድ ማረጋገጥ እስካልቻለ ድረስ በጋብቻ ውስጥ እያሉ ባል በተለምዶ (by Default) የሚወለዱት ልጆች አባት ነው ይላል። ከዚህም ሌላ እናት ከልጆችዋ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያና ዋነኛ ተአማኒ ለመሆኗ የሚያጠነክር ሌላ አባባል “የልጅዋን አባት የምታውቀው እናት ናት” የሚል ነው። ይህን ጉዳይ ለጊዜው እናቆየውና ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ የግሌን ገጠመኝ ላጋራ።

የዛሬ አምስት ዓመት ልጄ ትምህርት ቤት ለመግባት ሲደርስ ለማስመዝገብ የመረጥኩት ትምህርት ቤት ከጠየቀኝ ማስረጃዎች መካከል አንዱ የልደት ምስክር ወረቀት ነበር። በወቅቱ ከሆስፒታል የሚገኘው ካርድ ብቁ ነው ስለተባልኩ የውልና ማስረጃ ቢሮ መሔድ ሳይጠበቅብኝ ከሆስፒታሉ ሔጄ የወለድኩበትን ጊዜና ስሜን ጠቅሼ በሞላሁት ፎርም ወዲያውኑ ካርዱን ማግኘት ችያለሁ። የማስታውሰው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋራሁት አባት ይቅረብ ብቻ ሳይሆን ማንነቱ እኔው በሞላሁት መረጃ ተወስኖ ታምኜ ተሰጠኝ ብዬ ምናለ ሴቶችን ለሌላውም ብታምኑን የሚል ቀልድ አዘል ጽሑፍ መጻፌን አስታውሳለሁ።

ገጠመኜን በአራት ዓመት ከምናምን አሳልፉትና በዚህ ዓመት መጀመሪያ ሌላኛዋ ትንሽዋ ልጄ ትምህርት ቤት መመዝገብ ሲኖርባት በተመሳሳይ የልደት ካርድ ስንጠየቅ ከቀበሌ የሚገኘው የወሳኝ ኹነቶች ምዝገባ የልደት ካርድ ብቻ ተቀባይነት እንዳለውና መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ በመጀመሩ ያለሱ ማስመዝገብ እንደማንችል ስለተነገረን ቀበሌ መሔድ የግድ ነበር። በነገራችን ላይ ልጆችን በሚመለከት የልደት ምስክር ወረቀትን ጨምሮ ሌላም አገልግሎት ለማግኘት ኹለቱም ወላጅ ቀርቦ መፈረም የግድ ነው። ከመኖሪያ አድራሻችን የራቀ በነበረው ቀበሌ ጽሕፈት ቤት አገልግሎቱን ፍለጋ በሔድንበት ወቅት አንዴ ሲስተም የለም፣ ሌላ ጊዜ አባታቸው ሥሙ ተመዝግቦ ያለበት ቤት ቁጥር ቢሆንም የታደሰ አይደለም፣ ኮፒ አምጣ በሚል በሥራ ሰዓት መመላለስ የግድ ሆኖብን ነበር።

ይህንን ገጠመኝ በምን አስታወስኩ፣ ይህን ጽሑፍም ለመፃፍ እንዴት ተነሳሳሁ አንድ የሬዲዮ ዘገባ ሰምቼ። ሸገር ሬዲዮ ጥቅምት 14/2012 “የሕፃናት የልደት ምዝገባ የኹለቱንም ወላጆች ፊርማ የሚጠይቅ መሆኑ ብዙዎች ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ እክል መፍጠሩን ይናገራሉ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ። ጣቢያው በዘገባው እንዳለው አዋጁ የአንድን ሕፃን ውልደት በማስመዝገብ ሁለቱም ወላጆች ተገኝተው በክብር መዝገብ ላይ ፊርማ ማኖራቸው ልደት ምዝገባ ለማከናወን አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ነው። አንደኛው ወላጅ ብቻ የልደት ምስክር ወረቀቱን ማግኘት ቢፈልግ ግን ከፍርድ ቤት ሞግዚትነቱን አረጋግጦ ወረቀት ማቅረብ ይጠበቅበታል። አልያም በቦታው ካልቀረበው ወላጅ የውክልና ማስረጃ ይዞ መቅረብን የግድ ይላል። ዘገባው ጨምሮ እንዳተተው ፤ ይሁንና የአንድን ሕፃን በወቅቱ የመመዝገብ መብት በማስጠበቅ በኩል የአዋጁ ይህ ክፍል ክፍተት ያለበት እንደሆነ ይነገራል። ከኹለቱ ወላጆች አንደኛው ብቻውን ልጁን የማስመዝገብ መብትም የሚጋፋ ነው ይባላል። አልፎ ተርፎም የወሳኝ ኹነቶች አዋጅ ሲወጣ መንግሥት ክስተቶቹን በመመዝገብ መረጃ የማግኘት ዕቅዱ በዚህ ምክንያት መስተጓጎል እየገጠመው መሆኑ ይነገራል።

የውልደት ማረጋገጫ ማግኘት ዜጎች ከመንግሥት የሚያገኙት አንድ በ2004 የወጣው የወሳኝ ምዝገባና ሁነት አዋጅ ማንኛውም ሕፃን በተለወለደ በ90 ቀን ውስጥ መመዝገብ እንዳለበት ይደነግጋል። አልፎም ተርፎም በተሰጠው ጊዜ ያላስመዘገበ ወላጅ እስከ ስድስት ወር እስራትና የአምስት ሺሕ ብር ቅጣት እንደሚጣልበት ይደነግጋል። አዋጁ መተግበር ከጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም ቅጣቱ ተግባራዊ መሆን እንዳልጀመረ ተመልክቷል። አዋጁ ተግባር ላይ እየዋለ እንዳልሆነ ግን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። በተወሰነው ጊዜ የልደት ማረጋገጫ እየወሰዱ ያሉ ወላጆች ቁጥር ከሚፈለገው እጅግ አነስተኛ ነው።

በበኩሌ ለአዋጁ ተግባራዊነት ማነስ ኹለቱም ወላጆች ይምጡ የሚለው አስገዳጅ ሁኔታ አንድ እንቅፋት ነው ብዬ አምናለሁ። ኹለቱም በሥራ ላይ ለተሰማሩና አንዳቸው ሥራ ላላቸው ወላጆች ጭምር ቀበሌ በትክክል በሚሠራበት ወቅት ተገጣጥሞ ከሥራ አስፈቅዶ ሔዶ አገልግሎቱን ማግኘት ገና ሲታሰብ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ይሁን ቢባል እንኳል ብቻቸውን ልጅ ለሚያሳድጉ ወላጆች አስቸጋሪ ነው። የፍርድ ቤት ሒደት የሚስከትለውን ጣጣና የቀጠሮ ጋጋታ ለሚያውቅ በፍርድ ቤት ሞግዚትነትን ወይም አሳዳጊነትን አረጋግጦ መምጣት ሌላ ጣጣ ነው። ሌላው እዚህ ጋር መታየት ያለበት በተለይ በፈረሰ ትዳር ወይም ከጋብቻ ውጪ ልጆች ለሚወልዱ ሴቶች የህጉ ክፍተት የሚሳድረው የተለየ ጫናም ሊታይ ይገባል። የሴቶች የመደራደር አቅም አናሳ በሆነበት ከጋብቻ ውጪ ለተወለዱ ልጆች ወይም በሚታወቀው ከፍቺ በኋላ ያለ ግንኙነት አሳምኖ አባቶች መጥተው እንዲፈርሙ ማድረግ አዳጋች ነው።

ከኹለቱ ወላጆች በአካል መገኘት በተጨማሪ የልደት ምስክር ወረቀት ለመውሰድ የሚጠየቁ ነገሮች የእናትና አባት የልደት ካርድ፣ የልጁ ሥም የውልደት ቀን፣ ክብደት፣ የተወለደበት ቦታ፣ የውልደት ሁኔታ (ሆስፒታል ወይስ ቤት ውስጥ)፣ የአዋለደው ሰው፣ ውልደተ የተመዘገበበት ቀን ይጠየቃል። ወላጆቹን በሚመለከት ከልደት ካርዳቸው በተጨማሪ ለእናት የተወለደችበት ቀን፣ በወሊድ ወቅት ያገኘችው ርዳታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ብሔር፣ የመኖሪያ ቦታ፣ የትውልድ ቦታ፣ የሥራ ሁኔታ፣ የትምህር ደረጃ፣ ዜግነት፣ የመታውቂያ ቁጥር ይጠየቃሉ። ለአባትም ከወሊድ ሁኔታ በስተቀር ሁሉም ተመሳሳይ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። በዚህ አጋጣሚ ከላይ በገለጽኩላችሁ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ለትንሽዋ ልጄ ካርድ ልናወጣ በሔድንበት የብሔር ማንነት ጥያቄ ለምን አስፈለገ ይቅርልን ብለን ከሠራተኛው ጋር ብንከራከርም አልሆንም። “የምሠራው በሲስተም ነው ሲስተሙ ሁሉንም መረጃ ካላስገባሁለት የልደት ካርዱን አያትምልኝም” ብሎ ተቃወመ። እኛም ማስጨነቅ ወይም ግርግር መፍጠር አልፈለግንም ተውነው።

የወሳኝ ሁነቶች ምዝገባ ሲጀመር የተወሰነ የቅስቀሳ ሥራ የተሠራ ሲሆን የአዋጁ መውጣት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። የአዋጁ ተግባራዊነት በወቅቱ ፕሬዚዳንት በነበሩት ሙላቱ ተሾመና በዩኒሴፍ ኀላፊ ይፋ ሲደረግ ይህ አገር ዐቀፍና አስገዳጅ ሕግ የልደት የሞት፣ የጋብቻና ፍቺ ኹነቶችን በመመዝገብ የዜጎችን መብት ያረጋግጣል፣ ለመንግሥትና ለፖሊሲ አውጪዎች ትክክለኛውን መረጃ ስለ ዜጎች እንዲያገኙ በማሳለጥ በተለይ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሕግና እነሱን የሚያካትት አሠራር አለመኖር ምክንያት የተቸገሩ በኢትዮጲያ የሚገኙ ስደተኞችን ችግር በማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል በሚል በከፍተኛ አዎንታዊ ስሜት ነበር የተቀበልነው።
በሚገባ የተደራጀና የተቀላጠፈ የወሳኝ ኹነቶች ምዝገባና ምስክር ወረቀት አሰጣጥ የመንግሥትን ዕቅድ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመረኮዘ በማድረግ የሀብት አጠቃቀምንና ቁጥጥርን ያግዛል በዚህም የልማት ግቦች እንዲሳኩ የራሱ ድርሻ አለው። ይህ ድርሻው በአግባቡ እውን እንዲሆን ደግሞ በተቻለ መጠን ከዚህ በፊት ሰዎች የማያከናውኑትን ልጆችን በተወለዱ በ90 ቀን የማስመዝገብ ነገር ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ የግድ ይላል።

ከላይ በጠቀስኩት ዘገባ ሸገር ያነጋገራቸው የዜግነትና ኢሚግሬሽን ጉዳዮች መምሪያ የሥራ ኀላፊ የኹለቱም ወላጆች በመዝገቡ ላይ መፈረም ያስፈለገው የልጁን ሁለቱንም ወላጆች የማወቅ መብት ለመጠበቅ መሆኑን መናገራቸውን ዘገባው አትቷል። በውክልና አንደኛው ሌላኛውን ወክሎ እንዲሠራ አስቀምጠናል ቢሉም ቅሬታ የቀረበ በመሆኑ ለሕዝብ ቅሬታ ለመመለስ ጥናት ተጠንቶ ለማሻሻል እንደሚሠራ ተናግረዋል። የሌላ አገር ልምድ ታይቶ ለእናት ቅድሚያ የሚሰጡ አገሮች በመሆናቸው ያንን ለማየትም ጥናት ተደርጎ ማሻሻያ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ይህ ተግባራዊ ሆኖ በአገሪቱ የልደት ምዝገባ አገልግሎቱ እንደሚሻሻል ተስፋ እናደርጋለን።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com