የ60 ዓመቷን አዛውንት የደፈረው ግለሰብ ተቀጣ

Views: 1572

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ፖሊስ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የ60 ዓመቷን አዛውንት አስገድዶ የደፈረው የ 18 ዓመት ወጣት በ18 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ።

መኪና በመጠበቅ ሥራ ላይ የተሰማራው ግለሰቡ ድርጊቱን በፈጸመበት እለት ሐምሌ 8 ቀን 2009 ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ፤ ማደሪያ የሌላቸው፣ ሸራ ወጥረው ጎዳና ላይ የሚኖሩና በዛም ላይ ሳንባ በሽታ ያለባቸውን አዛውንት ከሚጠብቀው መኪና በአንዱ ውስጥ በተኙበት ድብደባ በመፈፀም እና ራሳቸውን መካላከል እንዳይችሉ በማድረግ ጥቃቱን አድርሷል።

የግል ተበዳይም አንድ የሚያውቁት የመኪና ባለቤት ብርድ በሚሆን ጊዜ በመኪና ውስጥ እንዲያድሩ በነገራቸው መሰረት ለመኪኖቹ ጠባቂ በማሳወቅ በሰጣቸው ፈቃድ መሰረት ወደ መኪናው ያመራሉ። ብርድ ልብሳቸውን ይዞ እንዲሔድ ቀድመው ሰጥተውት የቀረ ልብሳቸውን ይዘው የተከተሉት አዛውንት መኪና ውስጥ ገብተውም የያዙትን ልብስ ደራርበው ለብሰው ይተኛሉ።

ተከሳሽ አዛውንቷን ከመኪናው ፊተኛ ወንበር አስቀምጦ ለአፍታ ከቦታው በመራቅ እንቅልፍ እስኪጥላቸው ይጠብቃል። ጥቂት ቆይቶም በሩን ከፍቶ አፋቸውን እንዳፈናቸው፣ በተደጋጋሚም በቡጢ መትቶ ፊታቸውን በማድማት ካዳከማቸው በኋላ አስገድዶ እንደደፈራቸው የፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት የሰማው የምስክርነት ቃል ያስረዳል። ለችሎቱ የቀረቡ የፎቶ እና የህክምና የሰነድ ማስረጃዎችም አዛውንቷ የፊት ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና የመደፈር ጥቃት እንደደረሰባቸውም ማረጋገጫ ሰጥቷል።

በእለቱ ከአዛውንቷ ጋር የነበሩት የቅርብ ጓደኛቸው ሌላ ማደሪያ በማግኘታቸው መለያየታቸውንና በስፍራው እርሳቸው ብቻ እንደነበሩም እና ሊደርስላቸው የሚችል ሰው ባለመኖሩ ከአንድጊዜ በላይ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

‹‹እኔ ለባብሼ ትንሽ እንደተኛሁኝ ተመልሶ መጣና በሩን ከፍቶ አፌን አፈነኝ። ስጮኽ በቦክስ ፊቴን ደጋግሞ መታኝና የለበስኩትን አውልቆ ኹለት ጊዜ ነው የተገናኘኝ/ የደፈረኝ›› ሲሉ አዛውንቷ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል። የመኪናውን ቁልፍ ከየት እንዳገኘ እንደማያውቁም ቃላቸውን በሰጡ ጊዜ አስረድተዋል።

ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ ለማንም እንዳይነግሩ በተከሳሽ ማስፈራሪያ የደረሰባቸው አዛውንት፣ ነገሩን ለቅርብ ጓደኛቸውም በግልጽ አልተናገሩም። የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በሰጡት ቃል ‹‹የግል ተበዳይ ወደ እኛ ቤት መጥተው በር ሲያንኳኩ እኔ በሩን ከፍቼ ስመለከት ፊታቸው ተመትቶ ደምተው ነበር። ምነው ስላቸው ደበደበኝ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ውሰዱኝ አሉ›› ብለዋል። ይህንንም ተከትሎ ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ አምርተው የደረሰባቸው ጥቃት ድብደባ ብቻ ሳይሆን መደፈርም እንደሆነ ለፖሊስ መግለጻቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።

ተከሳሽ በአዛውንቷ ላይ በፈጸመው ድርጊት ግንቦት 9 ቀን 2010 በዋለው ችሎት፤ የ1996 የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 620(2)(ሐ) ስር የተመለከተውን በመተላፍ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የ18 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com