የአዲስ ማለዳ አንድ ዓመት

Views: 237

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ የኢትዮጵያ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ዘርፍን በኅዳር 8/2011 አሐዱ ብላ ትጀምር እንጂ ተረግዛ እስክትወለድ በቅድመ ዝግጅት ደረጃ ከስድስት ወራት ያላነሰ ጊዜ ፈጅቶባታል። በአገራችን የተከሰተውን የፖለቲካ ምኅዳር መስፋት ተከትላ የቁጥር ጭማሪ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ልዩነት ለማምጣት እንዲሁም የዴሞክራሲ ልሳን ለመሆን የተነሳች ጋዜጣ ነች።

በራዕይዋ በኢትዮጵያ የአራተኛነት መንግሥት ሚናዋን ለመወጣት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል ነጻ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ መገናኛ ብዙኀን መሆንን የሰነቀችው አዲስ ማለዳ፥ በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆንን ዒላማ አድርጋ እየሠራች ትገኛለች።

አዲስ ማለዳ ዕሴቶቼ ናቸው ብላ ያነገበቻቸው ሐቀኝነት፣ ምክንያታዊነት፣ ብዝኀነት፣ ሥልጡንነት፣ ጨዋነት እና ሙያተኝነት ጋር የማይፃረሩ ሐሳቦችን እና አስተያየቶችን ሁሉ እያስተናገደች ከርማለች፤ ወደፊትም ታስተናግዳለች። ከዚህም ባሻገር ዝርዝር ዓላማዬ ብላ የለየቻቸው ለተደራሲያን ወቅታዊ መረጃዎችን ማቅረብ፤ ትምህርት አዘል ሥልጡን ውይይት ማስተናገድ፤ ዴሞክራሲያዊነት እንዲያብብ፣ የመብት ጠያቂነት እንዲጎለብት ብሎም ኀላፊነትና ተጠያቂነት እንዲዳብር መታገል እንዲሁም የዜጎች፣ በተለይም ደግሞ ድምፅ አልባ ለሆኑት ልሳን መሆንን ያካትታል። እነዚህን ዓላማዎችን እያሳካች መሆን አለመሆኑን መፍረድ የተደራሲያን ቢሆንም፥ ለማስታወስ ያህል አንዳንዶቹን በመጠቃቀስ ለአንባብያን እናስታውሳለን።

በኢትዮጵያ አዲስ የኅትመት ሚዲያ በሚገፋ ምኅዳር ውስጥ፣ አዲስ ማለዳ ከመጀመሪያ ዕትሟ ጀምሮ ሳትቆራረጥ የዛሬውን ጨምሮ ለ52 ሣምንታት መሰራጨት መቻሏ በራሱ ትልቁ ስኬቷ ነው። በርግጥም በዓመት ጉዞዋ በንፅፅር አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ዕውቅና እና የነጻ እና ገለልተኝነት ክብር ማግኘቷ ድርብ ስኬት ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና ጉዞዋ እንደው ዝም ብሎ በተደላደለ መስክ ላይ አልነበረም፤ አቀበትም ቁልቁለትም የፈተኑት ጉዞ ነበር።
የአዲስ ማለዳ መለያዎች

አዲስ ማለዳ በ‘አቦል’ እና ‘ወፍ በረር’ የዜና አምዶቿ በር አንኳኩተው የመጡትን ብቻ ሳይሆን፥ በራሷ ፈልጋ ያገኘቻቸውን ዜናዎች ለመሥራት ታትራለች። ከነድክመቷ እንዲሁም ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም ተደራሲዎቿ ከሚሰጡት ግብረ መልስ በመነሳት ዜናዎቿ የተሻሉ ገላጮቿና በአብዛኛው የትም ያልተሰሙ መሆን የጥንካሬዋ መለኪያዎች ሆነዋል ብንል አላጋነንም። በወቅታዊና ትንታኔ ዓምዶቿ ወቅቱን ይመጥናሉ ያለቻቸውን አጀንዳዎች ትኩረት በመስጠት በመጠኑ ሰፋ ብለው እንዲቀርቡ አድርጋለች።

በ‘ሐተታ ዘ ማለዳ’ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎበትና ወቅቱንና ጊዜውን ይመጥናል ባለቻቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ባለድርሻዎችን ሐሳብ አነጋግራ፣ የባለሙያዎች ሐሳብን አካትታና ዋቢ መጽሐፍትን አጣቅሳ፣ አንፃራዊ ጥልቀት ያለው ትንታኔ የሚቀርብበት ልዩ የጋዜጣዋ መለያ መልክ ማድረግ ችላለች። ከበርካታ ተደራሲዎቿም በተለየ ሁኔታ ግብረ መልሶችን የምታስተናግድበት ዕድል ነው።

‘አንደበት’ እንግዶች የሚቀርቡበት አምድ ሲሆን ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮችን የሚመጥኑ እንዲሆኑ ጥረት አድርጋለች። በአብዛኛው የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች፣ በከፍተኛ ኀላፊነት ላይ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በሙያቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች፣ በማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ ጉልሕ አስተዋፅዖ ማድረግ የቻሉ ወይም ድምፃቸው መሰማት አለባቸው ብላ አዲስ ማለዳ ያመነችባቸውን ግለሰቦች የአገሪቱን ብዝኀነት በአንፃራዊነት በሚያሳይ መልኩ እንግዳ ሆነው እንዲቀርቡ አድርጋለች። ይህ አካሔዷ ወደፊትም ይቀጥላል። በ‘ሕይወትና ጥበብ’ አምድም ጥበባዊ ጉዳዮች በየፈርጃቸው ተዳስሰዋል፤ የጥበብ ሰዎች እንግዳ ሆነው ተስተናግደዋል።

ከላይ የጠቀስናቸው ዋና ዋናዎቹን ዓምዶች ሲሆን ‘ማረፊያ’ ዓምድም ቁጥሮችን፣ ንግግሮችን እንዲሁም ሰሞነኛ መነጋገሪያ የሆኑ ጉዳዮችን የምታቀርብበት ምጥን ነገር ግን ብዙ ቁም ነገሮችን የያዘው ገጿ ነው።

በተለይ ከዜና ክፍል ውጪ የሚጻፉት ዓምዶቿ፥ የተለያዩ ሐሳቦች የሚንጸባረቁበት እንዲሆኑ ጥረት አድርጋለች። ወቅታዊነትን፣ መሠረታዊነትን አንዳንዴም አጨቃጫቂ የሆኑ ጉዳዮች እንዲዳሰሰበት ሆኗል።

የስርዓተ ፆታን ምጣኔ በመጠበቅ ረገድም በተለይ የሴቶችን ድምፅ ለማሰማት አዲስ ማለዳ አንድ ቋሚ ሴቶች ስለ ስርዓተ ፆታ ብቻ የሚጽፉባት ‘ሲቄ’ የተሰኘች ምጥን ዓምድ ሲኖራት፥ በቋሚነት ደግሞ አንድ ሴት ዓምደኛም አላት። ብዙም ባይሆኑ ሔድ መጣ እያሉ ጽሑፍ ያበረከቱ ሴት ጸሐፍትም አሉ። አዲስ ማለዳ በዜና ክፍል አባልነት፣ በአምደኝነት፣ በዜና እና ትንታኔ ምንጭነት ሴቶችን ከወንዶች እኩል ለማካተት ጥረቷን በንቃት ትቀጥላለች።

አዲስ ማለዳ ከስርዓተ ፆታ ጋር በተያያዘ በተለይ የሴቶች ተሳትፎን ለማበረታታት እና ለመደገፍ፥ በዓለም ዐቀፍ የሴቶች ወር (መጋቢትን) ታሳቢ አድርጋ “ሴታዊት” ከተሰኘ ድርጅት ጋር በትብብር ሙሉ በሙሉ በሴት ጸሐፊያን የተዘጋጀችና የሴቶችን ጉዳይ ብቻ የያዘች ልዩ መጽሔትም አሳትማ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አድርሳለች።

የአዲስ ማለዳ ጥንካሬ
ዘመኑ ፈጣን፣ ሁኔታዎች በፍጥነት ተለዋዋጭ በሆኑበት ዓለም በተለይ ትውፊታዊ (‘ትራዲሽናል’) ከሚባሉት መገናኛ ብዙኀን መካከል ጋዜጣን መጠቀም ምን ያህል ፈታኝ እየሆነ እንደመጣ ይታወቃል። አንዳንድ አጥኚዎች የኅትመት መገናኛ ብዙኀንን በመሞት አፋፍ ላይ የሚገኝ ሚዲያ ነው ሲሉት፤ ዕድሜው አጭር እንደሚሆን ሲናገሩ ይደመጣል።

አዲስ ማለዳ ይህንን ትልቅ ተግዳሮት በመጀመሪያም ተገንዝባ ነበርና በፍጥነት በድረገጽ እና በማኅበራዊ ገጾቿ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ትገኛለች።
ድረገጿ addismaleda.net በንፅፅር አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ የተከታዮቿ ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ በመሔድ በአሁኑ በወርሓ ጥቅምት በአማካኝ በቀን ሰባት ሺሕ አምስት መቶ ሰዎች የመረጃ ምንጭ አድረዋታል፡፡ ድረገጹ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ220 ሺሕ በላይ ሰዎች ከ760 ሺሕ ጊዜ ለሚበልጥ ጊዜ መረጃ ለማግኘት አዲስ ማለዳ ድረገጽን ጎብኝተዋ፡፡ የፌስቡክ ተከታዮቿም92 ሺሕ ተቃርቧል። በትዊተር፣ በቴሌግራም እና በሊንክድኢን ገጾቿም አዲስ ማለዳ ለተደራሲዎቿ የመረጃ ምንጭነቷ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።

አይረሴ ትውስታዎች
በአንድ ዓመት ቆይታ አዲስ ማለዳ ብዙ ዘገባዎችን ያስተናገደች ሲሆን አንዳንዶቹ ዘገባዎች ወይም ጽሑፎች ተደራሲዎቿን እንዲሁም የማኅበራዊ ትስስር ገፆች አለፍም ሲል ሌሎች መደበኛ መገናኛ ብዙኀንን የሳቡ፣ ያወያዩ ጉዳዮች ናቸው። ይህም ለአዲስ ማለዳ መታወቅ የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል።

ከበርካታዎቹ ኹለቱን ለአብነት በመጥቀስ ተደራሲዎቿን እናስታውስ፤ አንደኛው መስከረም 17/2012፣ ቅጽ 1/47 በፊት ገጽ ላይ ያስነበበችው “የኢትዮጵያ ብልጽጋና ፓርቲ በሚል ስያሜ ኢሕአዴግ ውሕድ ፓርቲ ሊሆን ነው” የሚለው አቦል ዜናዋ የቅርብ ጊዜ፣ ነገር ግን በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ሰበር ዜናዋ ነበር። የዜናውን ፍንጭ ረቡዕ አግኝታ፣ ሐሙስና ዓርብን ለማረጋገጥ ላይ ታች ስትል ቆይታ ዓርብ ምሽቱን ተጽፎና ተዘጋጅቶ ወደ ኅትመት ገብቶ እስኪወጣ ድረስ በመደበኛው መገናኛ ብዙኀንም ይሁን በማኅበራዊ ገፆች ምንም ሳይባል ነው ዜናውን ለአንባብያን ያደረሰችው።

ሌላው አጋጣሚ ደግሞ አዲስ ማለዳ ግንቦት 3/2011 ቅጽ 1/27 ያስነበበችው ጉዳይ ሲሆን ዘጋቢዋን ኤርትራ – አስመራ በመላክ “የኤርትራውያን እንባ” በሚል ርዕስ የተሠራ በአንፃራዊ ጥልቅ ትንታኔ የተሠራበት ዘገባ፣ ጋዜጣዋ ወጥታ በተሰራጨችበት ዕለት በአንድ ታዋቂ በሆነ የዩቲዩብ ቻናል በድምጽና በምሥል ተቀናብሮ ለአዲስ ማለዳ ተገቢውን ዕውቅና ሰጥቶ በተሰራጨ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዐሥር ሺሕዎች ተመልካች ከማግኘቱም ባሻገር ብዙዎች በማኅበራዊ ገፆች ሲመለከቱትና ሲቀባበሉት ውለው ሰንብተዋል። የኤርትራ አክቲቪስቶችንም በከፍተኛ ሁኔታ ያነጋገረ ዘገባ ነበር።

እነዚህ ለአብነት ጠቀስናቸው እንጂ፥ ሌሎችም ብዙዎቹ ሥራዎቿ የብዙዎችን ቀልብ የሳቡና መነጋገሪያ ሆነው ያለፉ ዘገባዎች ነበሩ።

ተግዳሮትና ድካሞች
ሌሎች መደበኛ መገናኛ ብዙኀን በተለይ የኅትመቶቹ የሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶችን ሁሉ አዲስ ማለዳም ተጋፍጣለች። ለምሳሌ በየጊዜው እያሻቀበ የሔደው የኅትመት ዋጋ በዋናነት ተጠቃሽ ነው፤ አዲስ ማለዳ ኅትመት ስትጀምር የማተሚያ ዋጋ በጋዜጣ ከስድስት ብር ከሰባ ሳንቲም የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ዋጋው ከ60 በመቶ በላይ ዋጋ ጭማሬ አሳይቶ ከዐሥር ብር ከኻያ አምስት ሳንቲም ላይ ደርሷል።

ሌላው ችግር መረጃ በተፈለገው ልክ የማግኘት ወይም ማረጋገጥ አለመቻል፣ የዘጋቢዎች የሙያ ብቃት ደረጃ፣ ተቋማዊ አቅምና የሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ እምብዛም ሳይቆዩ መልቀቅ ተጠቃሽ ተግዳሮቶች ናቸው።

በኅትመት መገናኛ ብዙኀን ዘርፍ አዲስ ተዋናይ የሆነችው አዲስ ማለዳ፣ ብዙም ባይሆኑም የዘገባ ዝንፈቶችን ፈፅማ ታውቃለች፤ ወዲያውኑ የማስተካከያ እርምጃዎች ብትወስድም። ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ የወጣው ከዘጋቢዎች የአቅም ማነስ ባሻገር ለሙያው ሥነ ምግባር ያለመገዛት፥ በተለይ ደግሞ የሰው ሐሳብ በትክክል ዕውቅና መስጠትና ምንጭን አስተካክሎ ያለመሥራት፤ ባስ ሲልም እንደራስ አድርጎ ማቅረብ ነው። እነዚህ ግድፈቶች ባጋጠሙ ጊዜ ተመጣጣኝ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ እንዳይደገሙ አድርጋለች።

አዲስ ማለዳ ወደ ፊት
አዲስ ማለዳ ዘመኑን በሚመጥን ተደራሽነት እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያጎለብት ሥልት በመንደፍ ላይ በቅርቡ አዳዲስ የይዘት ማስተካከያዎችን ታደርጋለች።
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የጋዜጣ ሥርጭት ውስንነት በመኖሩ ስርጭቷን ይበልጥ አዲስ አበባ ላይ ያደረገችውን ጋዜጣ ከአዲስ አበባ ውጪም እንደልብ የምትገኝበትን ኹኔታ ለማመቻቸት ጥናትና ዝግጅት እያደረገች ነው። እንዲሁም ከተለመደው የሥርጭት ዘዴ ውጪ ሌሎች አማራጮችን በማጤን ላይ ትገኛለች።
ሌላው በአገራችን የጋዜጣ አንባቢዎች በብዛት ጎልማሳ ወንዶች ናቸው። ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በተለይ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ሕፃናት ተደራሽ ለማድረግ የጋዜጣ ውስጥ ጋዜጣ (insertions) ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች።

በመጨረሻም ዘመን ወለዱን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አዲስ ማለዳ ይፋዊ የዩቲዩብ ቻናል በመክፈት በድምጽና ምስል ጭርም የታጀበ መረጃ ለሕዝብ የማድረሱን ሥራ ለማጠናከርና ተደራሽነቷንና ተፅዕኖዋን በዛው ልክ ለማስፋት ዝግጅቷን ጨርሳለች።

አዲስ ማለዳ ከሠራችው ያልሠራችው፣ ከተጓዘችው ገና ያልተጓዘችው፣ ከዳሰሰችው ያልዳሰሰችው ስለሚበዛ በኹለተኛ ዓመት የኅትመት ዘመኗ ጥንካሬዋን ይዛ ድክመቷን አርማ እናንተን ውድ አንባቢዎቿን ተማምና፣ በአዲስ ጉልበት ትመጣለች። የእናንተን ውድ አንባቢዎቿን ድጋፍና ገንቢ ትችት ይዛ ወደ ፊት በረጅሙ እንደምትጓዝ እምንታችን ፅኑ ነው። የዘውትር ገንቢ አስተያየታችሁ እንዳይለያትም ጥሪ ታደርጋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com