ቃና ቴሌቭዥን ላይ ተጥሎ የነበረው ቅጣት ተነሳ

Views: 536

ቃና ቴሌቪዥን አሳሳች ነው በተባለው እና በአየር ሰዓቱ ባስታላለፈው የጥርስ ሳሙና ማስተወቂያ ምክንያት ከዓመታዊ ገቢው ላይ አምስት በመቶ እንዲከፍል ተላልፎበት የነበረውን ቅጣት በመቃወም ለሸማቾች ጥበቃ እና ንግድ ውድድር ባለሥልጣን ባስገባው የይግባኝ አቤቱታ መሰረት ውሳኔው ተሻረለት።

‹‹ሌሎች የጥርስ ሳሙናዎች በቂ አይደሉም፣ ለዚህም ነው ምርጫዬ ዳቦር ኸርባል የሆነው›› በሚል ዓረፍተ ነገር እናት እና ልጅ የሚነጋገሩበት ማስታወቂያ በማስተላለፉ፣ ሌሎች የጥርስ ሰሙና አምራቾች እና አስመጪዎች ላይ ፍትኀዊ ያልሆነ የንግድ ውድደር ፈጽመዋል በሚል ነበር ቃናን ጨምሮ ሦስት ድርጅቶች ላይ የባላሥልጣኑ አቃቤአን ሕግ ክስ የመሠረቱት።

ከ2011 ካልተጣራ ዓመታዊ ገቢያቸው ላይ አምሰት በመቶ እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የነበረ ሲሆን፣ ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ ጥቅምት 18 ቀን 2012 በዋለው ችሎት ጥፋተኛ አይደሉም በሚል ውሳኔው መሻሩን የሸማቾች ጥበቃ እና ንግድ ውድድር ባለሥልጣን አስታውቋል።

የሸማቾች ጥበቃ እና ንግድ ውድድር ባለሥልጣን ማስታወቂያው በጥናት ያልተረጋገጠ እና ለሌሎቹ ተወዳዳሪዎችም ፍትኀዊ ያልሆነ ነው በማለት ግንቦት 12/2011 በባለሥልጣኑ የእርምት እርምጃ ይወሰደልኝ ሲል አመልክቶ ነበር።

ቅጣቱን ተከትሎ በወቅቱም ተከሳሾቹ ጳጉሜ 4/2011 በዋለው ችሎት ‹‹እኛ የማስታወቂያ አዘጋጅ እና አሰራጮች ነን እንጂ ተወዳዳሪዎች አይደለንም፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የጥርስ ሳሙና የሚያመርቱ፣ የሚያቀርቡ እና የሚያከፋፍሉ ነጋዴዎችን ነው እናም ልንከሰስ አይገባም›› ሲሉ ተከራክረዋል።

የዳቦር ኸርባል የጥርስ ሳሙና አስመጪ ድርጅት ባለቤትም በተመሳሳይ ‹‹ድርጅታችን ማስታወቂያ እንዲሠራለት ለባለሞያዎች ክፍያ ፈፀምን እንጂ ስለማስታወቂያው ይዘት እኛ ሳንሆን አዘጋጆቹ የሚያወቁት ነገር በመሆኑ እኛ ልንጠየቅ አይገባም›› ሲሉ ክሱን ተቃውመው ነበር።

ይህንንም ምክንያት በማድረግ የሸማቾች ጥበቃ እና ንግድ ውድድር ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ችሎት ቃና ቴሌቪዥንን ጨምሮ በዳቦር ኸርባል የጥርስ ሳሙና አስመጪው አብዱርአህዛቅ ተኮላ ማስታወቂያውን በማሰራት እንዲሁም ቢ ማስታወቅያ ዝግጅት ፍትኀዊ ያልሆነ ማስታወቂያን በማዘጋጀት ተገቢ ያልሆነ እና ሌሎች የጥርስ ሳሙናዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው በሚል ነው ቅጣት የጣለባቸው። ተከሳሾቹ ከ2011 ዓመታዊ ያልተጣራ ገቢያቸው ላይ አምስት በመቶውን ለመንግሥት እንዲከፍሉም ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

ድርጅቶቹ ለባለሥልጣኑ የይግባኝ ሰሚ ችሎት ነሐሴ 13 ቀን 2011 አቤቱታቸውን ያስገቡ ሲሆን ማስታወቂያው በቴሌቪዥን የተላለፈው አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን እና ማስታወቂያው እንዳይተላለፍ የብሮድካስት ባለሥልጣን ባዘዘው መሰረት እንደይተላለፍ አድርገናል በማለት ተከራክረው በዚህም ስለደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አብራርተዋል።

አሳሳች ነው የተባለውን የጥርስ ማስታወቂያ ያዘጋጀው ቢ ሚዲያ እና አሰራጩ ቃና ‹‹ይህንን ጉዳይ የመመልከት ሥልጣንም የብሮድካስት ባለሥልጣን በመሆኑ የተወሰነው ውሳኔ አግባብነት የለውም፤ በአንድ ጉዳይ ኹለቴ ልንቀጣ አይገባም፣ ብሮድካስትም ቀጥቶናል›› ሲሉ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅረበዋል ።
ይግባኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 18 ቀን 2012 በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ ጳጉሜ 4/2011 እኛ የማስታወቂያ አዘጋጅ እና አሰራጮች ነን እንጂ ተወዳዳሪዎች አይደለንም፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የጥርስ ሳሙና የሚያመርቱ፣ የሚያቀርቡ እና የሚያከፋፍሉ ነጋዴዎችን ነው፤ እናም ልንከሰስ አይገባም›› በሚል ያቀረቡትን አቤቱታ ‹‹ማንኛውም ማስታወቂያ አሠሪ የሚያሠራውን ማስታወቂያ ይዘት ማወቅ ይገበዋል በሚል ውድቅ አድርጎታል።

ማስታወቂያው ከአንድ ጊዜ በላይ አለመተላለፉን እና በወቅቱ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት ማስታወቂያው እንዳይተላለፍ በማድረጋቸው ድጋሚ ቅጣት ሊተላለፍባቸው አይገባም፤ በሚል በሦስቱም ድርጅቶች ላይ የተጣለውን ቅጣት በማንሳት ጥፋተኛ አይደሉም ሲል ውሳኔ አስተላለፏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com