“አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስተኛ ውስጥ 18 ክፍሎች ጨለማ ቤቶች አሁንም አሉ።”

Views: 1003

ስንታየሁ ቸኮል የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት መስራች አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ናቸው። ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩ የሚናገሩት ስንታየሁ፥ በተለይ ከ1993 ጀምሮ በቀጥታ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ እንደነበራቸውም ይናገራሉ። ከተሳተፉባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ቅንጀት ለአንድነትና ዴሞክራሲ (ቅንጅት)፣ አንድነት እንዲሁም ሰማያዊ ፓርቲ ናቸው። አሁን ቀጥታ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ባይኖራቸውም ስንታየሁ ራሳቸውን የመብት ተሟጋች እንደሆኑ ይገልፃሉ።

ስንታየሁ ሰኔ 15/2011 በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ላይ ተካሔደ በተባለው መፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከተያዙት ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው። ክስ ሳይመሰረትባቸው ለወራት በእስር ላይ የቆዩት ስንታየሁ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18 በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመታወቂያ ዋስትና ከእስር ተፈትተዋል።

የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከስንታየሁ ቸኮል ጋር በእስር ቤት የነበራቸውን ቆይታ፣ አያያዝና ከምርመራ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን እንዲሁም ስለአፈታታቸው ሁኔታ አጭር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ በእስር ላይ ምን ያህል ጊዜ ቆዩ?
ስንታየሁ ቸኮል፡ አራት ወር ከስድስት ቀናት ነው የታሰርኩት። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ወር በላይ ጨለማ ቤት ውስጥ ነበርን። ጨለማ ቤት ሲባል አንዳንድ ሰው ብዥታ አለው፤ ጭልም ጭልም ያለ ነገር የሚመስለው አለ። [ጨለማ ቤት] ሥነ ልቦናዊ ሆኖ ሰዎች የማይንቀሳቀሱበት የተዘጋ ቤት ነው። በ24 ሰዓት ውስጥ 15 ደቂቃ ብቻ ለእረፍትና ለመጸዳዳት የሚሰጥበት ስፍራ ማለት ነው። ከዛ ውጪ ጨለማ ቤት ጤንነትን ለመጠበቅም ምቹ ያልሆነ ፍጹም ኢ-ሰብአዊ የሆነ ተግባር የሚፈጸምበት ቤት ነው።

ይህ ጨለማ ቤት ትላንትም ነበር አሁንም አለ። ትላንት የነበረው ጨለማ ቤት ምን አልባት ዛሬ ቀለም ተቀብቶ ሊሆን ይችላል፤ አሁን ደግሞ ነጭ ቀለም የተቀባ ጨለማ ቤት አለ። ይሔ ሊሰመርበት ይገባል። ብዙ ሰዎች ጨለማ ቤት የሚባል ነገር አብቅቷል፣ የለም የሚሉት ነገር አለ። ሔዶ ማየት ይቻላል፤ አለ።
አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሦስተኛ ውስጥ 18 ክፍሎች ጨለማ ቤቶች አሁንም አሉ። የምርመራ ጊዜ ተብሎ ከአንድ ወር በላይ እዛ ነው ያሳለፍኩት።

ከምርመራ ጋር በተያያዘ የደረሰቦት የሰብኣዊ መብት ጥሰት ነበር?
ከፍተኛ የሆነ ሥነ ልቦናዊ የመብት ጥሰት ተፈጽሞብናል። በተለይ በእንቅልፍ ሰዓት ሌሊት 5 እና 6 ሰዓት እየተጠራን ሰዎች ኹለትና ሦስት ቀን የሚቆሙበት አጋጣሚ አለ። ለምሳሌ አየለ አስማረ የሚባል 72 ሰዓት የቆመ አንድ ወጣት አለ። እንዲሁም በተመሳሳይ አስጠራው ከበደ የሚባል ወደ 68 ሰዓት ቆሞ የቆየ ሰው አለ። ይህ ግፍ ትላንት ነበር፤ ዛሬም እየተፈጸመ ነው። በፊት የምርመራ ሒደት ጥፍር ይነቀላል፣ ከፍተኛ አካላዊ ጥቃት [በእስረኞች ላይ] ይፈጸምባቸው ነበር። አሁን ደግሞ አዕምሮ ነው የሚነቀለው፤ ከጥፍርም በላይ ሆኗል። ሰዎችን አደንዝዞ የሚያወጣ የምርመራ ሒደት ነው ያለው። ሌሊት በእንቅልፍ ሰዓት ጠርተው ቁም እየተባለ ቆሞ የሚመረመር፤ ምርመራው ደግሞ ከገባቡት ጉዳይ ጋር ፍጹም የማይገናኝ ፖለቲካዊ ጥያቄ የሚጠየቅበት ነው። ፖሊሳዊ ሳይንስ የተደበላለቀ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

በቀጥታ ከታሰሩበት ጉዳይ ጋር የተደረገው ምርመራስ ላይ ምን አጋጠሞት?
የታሰርነው መፈንቅለ መንግሥት ከተባለው ጋር በተያያዘ ነበር፤ ስንጠየቅ የነበረው ግን አዲስ አበባን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ መንቀሳቀስ አትችሉም፤ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አናውቅም የሚለው ነው። ይህንን ነው እኔን ፖሊስ አንድ ጊዜ የጠየቀኝ። አንድ ጊዜ ብቻዬን ጠይቆኝ ነው የተፈታሁት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በአደባባይ ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጋር በተያያዘ መታሰራችንን ነበር የተናገሩት። ፖሊስ እየጠየቀኝ የነበረው ግን ስለአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ነበር። ምን አልባት ፖሊስ ኮሚሽኑ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልተናበቡ ይሆናል።

እኛ ላይ የተፈጸመው ፖለቲካዊ እስር ነው። ያለምክንያት በፖለቲካ አመራር ውሳኔ የታሰርን የሕሊና እስረኞች ነበር። ሆነ ተብሎና ታልሞ ሕዝብ ባልደራስ ላይ የሰጠንን አደራ በአግባቡ እንዳንወጣ እንቅፋት ለመፍጠር፤ ምናልባትም ይንቀሳቀሳሉ የተባልነውን ሰዎች ከሰብሳቢያችን በመነጠል ብቻውን ለማስቀረት የተደረገበት ሸፍጥ ነው ብለን ነው የምንገመግመው።

ከእስሩ ጋር ተያይዞ ቤተሰብና ጠያቂ እንዲሁም የሕግ አማካሪ እንድታገኙ ተፈቅዶሎታል?
የሕግ አማካሪዎቻችን መጥተው አስጠርተውን በቢሮ በኩል እናገኛቸው ነበር። ከቤተሰብም ጋር እንገናኝ ነበር። በዚህ በኩል ችግር አልነበረም። በዋነኛነት ግን ራሳችንን ለመጠበቅ የማንችልበት ቦታ ላይ አሳልፈናል። ሰው በማግኘት በኩል መብታችን ቢከበርልንም በምርመራው ሒደት ግን ከፍተኛ የሆነ ሰብኣዊና ሥነ ልቦናዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል።

የሌሎች እስረኞች አያያዝ እንዴት ነበር?
ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ፖሊስንም ማዕከላዊን አውቀዋለሁ። ትላንት ምናልባት 150 ሰዎች ታስረው ይሆናል። አሁን ወደ 340 እና 400 ሰው ታስሮ ነው ያለው፤ ማረጋገጥ ይቻላል። ይህ ፊት ለፊት የሚታይ እውነት ነው፤ መቀበል መቻልም አለብን። ሁሉም ሰው ደግሞ በአግባቡ መኝታና ምግብ አያገኝም። ስለዚህ [እስረኛው] በከፍተኛ ደረጃ ለበሽታ እየተጠቃ ነው ያለው። የፖለቲካ እስረኞች የሥነ ልቦና ጥቃት ነው የሚፈጸምባቸው።

ትላንትም እስር አለ፤ ዛሬም እስር አለ። ትላንትም ጭካኔና የሰብኣዊ መብት ጥሰት ነበር፤ ዛሬም አለ። ሕዝብ መታለል የለበትም። በዋናነት የምንታሰርነው ልንጀግን ብለን አይደለም፤ አስገድደው ነው ያሰሩን። ወንጀል ቢኖርብንኮ አይፈቱንም ነበር፤ ማስረጃ ስለሌላቸው ነው የፈቱን። ገዳይ፣ ሟችና ታሳሪ ተዘጋጅቶ የሚሠራ ተራና ቀሽም ድራማ ነው። ይሔንን መንግሥትም በግልጽ የሚያውቀው ጉዳይ ነው። እኛ ንጹሕ ስለሆንን እና ከተጠረጠርንበት ጉዳይ ጋር የሚያገናኝ ምንም ማስረጃ ስለሌላቸው ነው ሊከሱን ያልቻሉት።

ሕዝቡን እያታለሉና እያጭበረበሩ የሚሔዱበት ዘመን ሊያበቃ ይገባል። ብዙ ሰዎች በዚህ ሁኔታ እየተሰቃዩ ነው። ከእኛ ጋር በሰኔ 15ቱ ጋር በተያያዘ ከተለያየ ቦታ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ ተቀናሽ የሠራዊቱ አባላትና እና ሌሎች ሰዎች ጨምሮ በአጠቃለይ 108 ሰዎች ነበርን፤ 22ቱ ግን አሁንም አልተፈቱም።

ያለ ክስ በእስር ላይ መቆየትን እንዴት ይገልጹታል? ሲፈቱስ ምን ተሰማዎት?
እኔ አዝናለሁ፤ መጀመሪያም ንጹሐን ዜጎች ስለሆንን መታሰር አልነበረብንም። እንደማንኛውም ዜጋ ሐሳባችንን በነጻነት የምንገልጽ፤ በአገራችን ዴሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ላለፉት 20 ዓመታት የታገልን ሰዎች ነን፤ መንግሥትም ያውቃል። ዞሮ ዞሮ አሁንም እየታገልንና እየጠየቅን ያለነው ፍትሐዊ ጥያቄ፤ መንግሥት በራሱ መመለስ ስለማይችልና ጥያቄው ስለሚከብደው፤ ምናልባትም ሥልጣኑ ላይ ከፍተኛ አደጋ ይፈጥርብኛል ብሎ ስላመነ ለማጨናገፍ ሆነ ብሎ ወንጀል ፈልጎ አሰረን። ትላንትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው አደባባይ ወጥተው አውግዤዋለሁ ብለው ንስሐ ገብተው በኮነኑት በዛው መልሶ አዋጅ መክሰስ አሳፋሪና ቀሽም ነገር ነው።

እናም ንጹሐን በሚጠቁበት አዋጅ ዛሬም እየተጠቃን፣ እየተበደልን ነው። ከዛም በላይ አራት ወር ገደማ ታስረን ነጻ ተብለን ስንለቀቅ ደግሞ በጣም ያሳምማል። በእስር በቆየንበት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች አዲሰ አበባ ውስጥ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት። መንግሥት እነርሱን ለማሰር ሞራል የለውም፤ እነሱን ለመናገር አቅም የለውም። ንጹሐንን ግን ቤት ለቤት እየሔዱ ያስራሉ። ይሔ ነገር ሊበቃ ይገባል።

ከዚህስ በኋላ በድጋሜ የመታሰር ስጋት የለቦትም?
እኔ ምንም አያስፈራኝም። ይህን አገዛዝ እናውቀዋለን፣ አጭበርባሪ አገዛዝ ነው። ባለፉት 30 ዓመታት ሕዝቡን በሐሰት እየከሰሰ፣ በሐሰት እየወነጀለ፣ በሐሰት ደግሞ ፊልም እያሠራ ሰዎችን ሲያስር የነበረ ነው። በጣም ቀሽም የሆነ ከራሱ ጋር የተጣላ ስርዓት ነው።

ይህ ስርዓት ሊበቃው ይገባል ብለን እየተጋልን ያለን ሰዎች ነን። እኛ ከሕዝባችን ጋር ነው የምንነጋገረው እንጂ ከአገዛዙም ሆነ ከስርዓቱ ጋር አይደለም።
ስርዓቱ በፈለገ ጊዜ እኛን ሊያጠቃን የተለያየ መሣሪያ ሊያነሳብን ይችላል፤ እኛን ሊከላከል የሚችል ግን ሕዝብ አለ። እኔ የምተማመነውና ተስፋ የምጥለው ሰፊው ሕዝብ ላይ ነው። አደራ የተቀበልኩት ከሕዝብ ነው። ዛሬም ከእስር ያስፈታኝ ይህ ሕዝብ ነው፤ ነገም እስር ካለ ከእስር የሚያስፈታኝ ይህ ሕዝብ ነው። ስለዚህ ለሕዝብ የምንከፍለው መስዋዕትነት ይቀጥላል። እኛ መንገዶች ነን እንቀጥላን፤ ፍርዱን የሚሰጠን ግን ሕዝቡ ነው።

ስለዚህ በዚህ ሒደት ውስጥ ነገን የምናየው፤ በእኔ በኩል ግን [ማስረጃ] ካላቸው በማንኛውም ጊዜ መጥተው ክስ ሊመሠርቱ ወይም ሊያስፈራሩኝ ይችላሉ። እሱን ግን እኔ ቦታ የምሰጠው [ጉዳይ] አይደለም።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com