“የፍትሕ ስርዓቱ ከአስፈጻሚው አካል ነጻና ገለልተኛ አለመሆኑን አረጋግጬ ነው ከእስር የወጣሁት።”

Views: 567

ኤሊያስ ገብሩ የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ፀሐፊ ናቸው። ላለፉት 12 ወራት ከ12 በላይ በሆኑ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ላይ ከዘጋቢነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ማገልገላቸውን የሚናገሩት ኤሊያስ፥ መሰናዘሪያ፣ አውራምባ ታይምስ፣ ፍትሕ፣ ዕንቁ፣ አዲስ ገጽ ከተሳተፍባቸው ጋዜጦችና መጽሔቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። የአባይ ሚዲያ የኢትዮጵያ ወኪልም ሆነው አገልግለዋል። ኤሊያስ በሙያቸው ጋዜጠኛ ይሁኑ እንጂ ራሳቸውን የመብት ተሟጋች አድርገውም ይገልጻሉ።

ኤሊያስ ገብሩ ሰኔ 15/2011 በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ላይ ተካሔደ በተባለው መፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከተያዙት ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው። ክስ ሳይመሰረትባቸው ለወራት በእስር ላይ የቆዩት ኤሊያስ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18 በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመታወቂያ ዋስትና ከእስር ተፈትተዋል።

የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከኤሊያስ ገብሩ ጋር እስር የነበራቸውን ቆይታ፣ አያያዝና ከምርመራ ጋር በተያያዘ ያጋጠማቸውን እንዲሁም ስለአፈታታቸው ሁኔታ አጭር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ ምን ያህል ጊዜ በእስር ቆዩ?
ኤልያስ ገብሩ፡ በእስር አራት ወር ነው የቆየሁት። እነ ስንታየሁ [ቸኮል] በ10 ቀን አካባቢ ይቀድሙኛል።

ከዚህ ቀደም ከነበረውን የእስረኛ አያያዝ አንጻር ይኼኛውን እንዴት አገኙት?
ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር በተገናኘ ሦስት ጊዜ ታስሬ ነበር፤ ይህ አራተኛ እስሬ ነበር። ከዚህ ቀደም በሕወሓት ኢሕአዴግ ጊዜ የነበረው የእስር ሁኔታ ይታወቃል። የእስር ቤቱን ሁኔታ በአጠቃላይ በኹለት መንገድ ነው የማየው ከትላንቱ የተሻሉ የምላቸው ነገሮች አሉ፤ ያልተለወጡም እንዲሁ አሉ።

በፊት ድብደባ ይፈጸም ነበር፤ እኛ በታሰርንበት ወቅት ግን ድብደባ አላየንም፤ ድብደባ የተፈጸመባቸው ሰዎችም አልነገሩኝም። ይሁንና ግን ሦስት ቀን ሙሉ አስቁመው የሚመረምሯቸው ነበሩ፤ ረጅም ሰዓት እስረኛን የማቆም ነገር ነበር። ምግብ በሳህን እያመጡላቸው እዛው ይበላሉ፣ ሦስት ቀን ሙሉ ቀንና ሌሊቱን አንድ ቦታ ላይ እንዲቆሙ አድርገው የመረመሯቸው ሰዎች ነበሩ። በዚህም ሽንታቸውን መቆጣጠር ያቃታቸው ሰዎች ፍርድ ቤት ሲናገሩ ሰምቻለሁ።

ጨለማ ቤት የሚባለው በፊትም ነበር፤ አሁንም አለ። ሙሉ ለሙሉ ጭልም ያለ ማለት ግን አይደለም። መብራት አለ፤ ሙሉ በሙሉ የፀሐይ ብርሃን የለም። ኹለት በኹለት በሆነ ክፍል ውስጥ በቂ አየር እንኳን የማይገኝበት ነበር። ማዕከላዊም ጨለማ ቤት ሲባል ጠዋትና ማታ ለመጸዳዳት ነበር በሩ የሚከፈተው፤ ከዛ ውጪ በሩ ተዘግቶ ነው የሚውለው። አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥም አሁን ይህ ቀጥሏል። በዚህ ወቅት ይህን አያለሁ ብዬ [ግን] አልገመትኩም ነበር።

በጣም ጠባብ ክፍል ውስጥ ብዙ እስረኛ ነው የነበርነው፤ ለስልሳ እስረኛ አንድ መጸዳጃ ቤት ነበር የምንጋራው፤ እጅ መታጠቢያም ባለመኖሩ ኮሪደር ላይ ነበር የምንታጠበው። ሰውነት ለመታጠብ የሚያስችል ቦታ አልነበረም፤ በብዙ ውትወታ ነው ወደ ሌላኛው ክፍል ሲወስዱን ሰውነታችንን መታጠብ (‘ሻወር’) መጠቀም የቻልነው።

አንድ ሰው ተጠርጥሮ ሲያዝ ጠርጥሮ የያዘው አካል ማን እንደሆነ መግለጽ ነበረባቸው። እኔ ሰኔ 29 [2011] ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ ስያዝ ከየት እንደመጡ እንኳን አልነገሩኝም። ማታውኑ የሕይወት ታሪክ ስጠን ብለውኝ ሰጥቻው ነበር፤ ያኔ እንኳን በምን ጉዳይ ተጠርጥሬ እንደተያዝኩ አልነገሩኝም። ይህ አንድ የመብት ጥሰት ነው ማለት ነው።

በምርመራ ላይ ያጋጠሞት የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች አሉ?
ቃልህን ስጥ አልሰጥም፥ በሚል ስንከራከር ነበር። ሦስትና አራት ሆነው በማስጨነቅም ቃል ለመቀበል ግፊት አድርገዋል። አልሰጥም ስትላቸው እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ በወረቀት ላይ ጽፈው ፈርም ይላሉ፤ እኔ ምንም የምፈርመው ነገር የለም ብያቸዋለሁ። ከጉዳዩ ጋር የማይያያዝ ጥያቄም ነበር ሲጠይቁ የነበረው። የባላደራው ምክር ቤትን እንቅስቃሴ ነበር ሲጠይቁ የነበረው። ከተጠረጠርኩበት ጉዳይ ጋር የሚገናኝም አልነበረም።
ሌላው የጄኔራል አሳምነው ባለቤት ደስታ አሰፋ አራት ቀን ሙሉ ለሙሉ ጨለማ ክፍል ውስጥ ታስራ እንደነበር ፍርድ ቤት ስትናገር ሰምቻለሁ። ጨለማ ቤት የለም ለሚባለው፤ አለ ብለን እንናገራለን።

ሌሎች እስረኞች አያያዝም ችግሮች ነበረበት እያሉኝ ነው?
አዎ! 110 ሰዎች ነን ተይዘን የነበርነው። ሁሉም የሰብኣዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመበት ሲገልጽ ነበር፤ ሁሉም በየራሱ የደረሰበትን ሲናገር ነበር።

ሰብኣዊ መብት ጥሰት በሌሎች እስረኞች ላይ ሲፈጸም ተመልክተዋል?
አንድ ቻለ የሚባል ከአሶሳ የመጣ ልጅ ረጅም ሰዓት አቁመው መርምረውት ሽንቱን እንዳይሸና አድርገውትና መቆጣጠር ሳይችል ሕክምና ሔዷል። አሁንም ድረስ ሕመምተኛ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ፍርድ ቤት ተናግሯል። ሌላም አየለ አስማረ የሚባሉ ሦስት ቀን ሙሉ በማስጨነቅ ሲመረምሯቸው እንደነበር በዐይኔ አይቻለሁ።
በፊት እንደሚባለው ጥፍር ነቀላ ነበር፤ አሁን ደግሞ የአእምሮ ነቀላ ነው፤ ሥነ ልቦናዊ ሥቅየት (ሳኮሎጂካል ቶርቸር) አለ።

የሕግ አማካሪ የማግኘት እና በቤተሰብ የመጠየቅ መብታችሁ ተከብሮላችኋል?
አልተከበረም! ቤተሰብም መታሰሬን ያወቀው ቅዳሜ ታስሬ ሰኞ ፍርድ ቤት ስቆም ነው። ለቤተሰብ ስልክ እንኳን እንድደውል አልፈለጉም። እስከ ሰኞ ፍርድ ቤት እስክቀርብ ድረስም የለበስኩትን አልቀየርኩም። ከአምስት ቀን በኋላ ነው ጠበቃም ማግኘት የቻልኩት። ቤተሰብም በግፊት ነው በመርማሪ በኩል ወደ ማግኘት የመጣነው።

መጀመሪያ ከነበርንበት ክፍል ወደ ሌላ ክፍል ከተዘዋወርን በኋላ ግን ጋዜጣም ይገባ ነበር። የፊት ገጹን አይተው የፖለቲካ ጉዳይ ከሆነና በእነርሱ ግምገማ ድንገት ካስደገጣቸው አይገባም የሚሉትበት ጊዜ ነበር። እኛም በተደጋጋሚ ጠይቀን መጽሐፍና ጋዜጦች ይገባሉ። የሕዝብ ስልክም ስለነበር መደወል እንችል ነበር። ይሔ በአንጻራዊነት በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ነው።

ከሥነ ምግባር የወጡ የፖሊስ አባላት እንዳሉ ሁሉ፥ ለእስረኛ ጥሩ የሆኑ ፖሊሶች አይቻለሁ፤ ምንም እንኳን ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም።

ያለ ክስ በእስር ላይ መቆየትን እንዴት ይገልጹታል? ሲፈቱስ ምን ተሰማዎት?
በተፈጠረው ነገር በጣም አዝኛለሁ። ከመጀመሪያው ጀምሮ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ነበር። የያዘኝና ፍርድ ቤትም ያቀረበኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ነው። በጸረ ሽብር አዋጁ ደግሞ የመጠየቅ መብት ያለው የፌዴራል ፖሊስ እንጂ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አይደለም። ይሔ ጉዳይ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስሩ ሕገወጥ መሆኑን ያሳያል።

በጠበቃ በኩል ከስሼ ፍርድ ቤቱ የሕግ ጥሰት እንዳለ እያወቀ እንኳን አስፈጻሚውን አካል ስለፈሩ ብቻ ለእነርሱ የወሰኑበት ሁኔታ ነበር። ይግባኝም ጠይቀን የሕግ ጥሰት መኖሩን እያወቁ፣ “ኤልያስን ብንፈታውም ገና ሳይወጣ በር ጋር ይይዙታል” ብለው ነው ለጠበቃዬ የነገሩት። ችግር የለም እናንተ ፍቱት፣ እነርሱ ደግሞ በር ላይ ይያዙት ብሏቸው፤ አሁንም ‹‹በሌላ ችሎት ጉዳዩ እየታየ ስለሆነ›› ብለው በፍርሃት ውሳኔውን ቀልብሰዋል።

አሁንም የፀረ ሽብር አዋጁ ማጥቂያ ነው የሆነው። በተወገዘና ይሻሻላል በተባለበት አዋጅ ላይ ሰዎች ተጠርጥረው እስር ቤት መግባት አልነበረባቸውም። አሁንም የፀረ ሽብር አዋጁ ከገዢው ኀይል የተለየ ሐሳብ የሚያቀነቅኑትን ማጥቂያ መሣሪያ ሆኖ መቀጠሉን ነው ያየነው።

መርማሪዎቹም ለእኔ ባይሆንም ለሌሎች ተጠርጣሪዎች “ፍርድ ቤት አይፈታችሁም፤ እኛ ነን የምንፈታችሁ፤ ፍርድ ቤት ዝም ብላችሁ ትሔዳላችሁ እንጂ ውሳኔ ያለው እኛ ጋር ነው” ይላሉ። ይሔ ትልቅ የማይባል አገላለጽ ነው። ፖሊስ ፍርድ ቤት ያቀርባል፤ መፍታትም ሆነ ማሰር የሚችለው ፍርድ ቤት ነው። መርማሪ ፖሊስ አይቶ ያስፈታዋል ብሎ ካሰበ ግን በመታወቂያ ዋስ ሊፈታ ይችላል።

እና እስሩም ፍቺውም ፖለቲካዊ ነው እንጂ የፍትሕ ስርዓቱን ተከትሎ የተካሔደ አይደለም። የፍትሕ ስርዓቱ፣ ደኅነትም፣ ፖሊስም፣ ዐቃቤ ሕግም፣ ፍርድ ቤትም ከአስፈጻሚው አካል ነጻና ገለልተኛ አለመሆኑን አረጋግጬ ነው ከእስር የወጣሁት። በፊት ግን ለውጥ አለ ብዬ አምን ነበር፤ ገብቼ በማየቴ ነው ይህን የተናገርኩት።

ከዚህስ በኋላ በድጋሜ የመታሰር ስጋት የለቦትም?
እኔ ትላንት አደርገው ከነበረው ምንም ወደ ኋላ የምልበት ነገር የለም። ፍርድ ቤትም መርማሪዎች ሲናገሩ የነበረው፤ እኔ የታሰርኩት በጋዜጠኝነት ሙያ ነው ስል ነበር፤ አላመኑኝም ነበር። በኋላ ግን መርማሪ ፖሊሱ ጋዜጠኝነት ሙያን መሠረት አድርገው ሰኔ 15 ባሕር ዳር ላይ የተደረገውን ያቀነባበረው መንግሥት ነው፤ ዶክተር ዐቢይም እጁ አለበት ብሎ በስልክም አውርቷል፤ ማኅበራዊ ሚድያ ላይም ጽፏል ብለዋል።

እኔ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ እንደዛም ብዬ አልጻፍኩም። ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት ለአንድ ወር ያክል ፌስቡክ ላይም ጽፌ አላውቅም። በስልክ ስለማውራቴም መረጃ አቅርቡ ተብለው ነበር፤ መረጃ ማቅረብም [ግን] አልቻሉም። ስለዚህ የታሰርኩት ከሙያዬ ጋር በተገናኘ ነገር። ይህ ደግሞ አሁንም ጋዜጠኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀልና ሽብር መሆኑን ነው የሚያሳየው። እኔ ነጻ ሐሳቤን ትላንትም ሳራምድ ነበር፤ ዛሬም እቀጥልበታለሁ።

ነገር ግን ሌሎች ንጹሐን ዜጎች ነገ ላይ በግፍ መታሰር አለባቸው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም የአሁኑ እስር ለአሳሪውም ለታሳሪም የማይመጥን እስር ነው። ማሰር አሻናፊነትና ጀግንነት አይደለም፤ መታሰርም እንደዛው። ከዚህ አዙሪት ውስጥ መውጣት መቻል አለብን። በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ፣ ሐሳባቸውን በነጻነት በማራመዳቸው፣ መንግሥት ያላስደሰተውን ያደረጉ ዜጎች አሁንም በቂም በቀል የሚቀጡበት አዙሪት መቆም አለበት፤ ለዚህ ነው ትግል የሚያስፈልገው። ማንም አራት ወር ይቅርና አራት ሰዓት በሐሰት መታሰር አልነበረበትም። ወንጀል የሠራ ሰው አይጠየቅ እያልኩኝ አይደለም፤ በቂ መረጃ ከተገኘበት በሕግ አግባብ መጠየቅ አለበት። ወደ ፍርድ ቤት የሚያመራ ከሆነም ተከስሶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት አለበት፤ ይህን አምናለሁ። ነገር ግን ሰዎች ባላጠፉት ድርጊት ትላንት እንደነበረው በፖለቲካ ቂም በቀል መወጣጫ መታሰራቸው መቆም አለበት። ይሔም ሌላ ትግል ይጠይቃል። ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስኪሰፍን ድረስ ትግል ይጠይቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com