የሸማቹ ኅብረተሰብ ፈተና እና የመፍትሔ አቅጣጫ

Views: 181

የሸማች ማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት በመተግበር ላይ ያሉት የተለያዩ መላዎች እምብዛም የታለመላቸውን ግብ አልመቱም የሚሉት ካሳዬ አማረ፣ ጊዜውን የዋጀ ነው የሚሉትን ነፃ የሸማቾች ማኅበር መመስረት እንደ መፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል።

የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች ተብለው የሚጠቀሱት ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስ እና መጠለያ ሲሆኑ አንዳንድ አገሮች ተጨማሪ ፍላጎቶችን ያካትታሉ። የምግብ፣ የመጠጥ፣ የልብስ እና የመጠለያ ፍላጎት ካለ ምርት፣ ሥርጭት፣ ልውውጥ እና ፍጆታ የሚያያዙ ኢኮኖሚያዊ ሰንሰለቶች ናቸው። ለገበያ የቀረበ ምርት ወይም ሸቀጥ ሸማች ይፈልጋል። የሰው ልጅ ፍላጎት እስካለ ድረስ ሸማችነት የቀን ተቀን እውነታ ነው።

እስከ አሁን ባለው ታሪክ ውስጥ ከአምራቹ እስከ ተጠቃሚው ድረስ ባለ ሰንሰለት የመጨረሻው ክፍል ሸማቹ ከእሱ በፊት ከነበሩት ተዋናዮች ሁሉንም ሸክም የሚሸከም ክፍል መሆኑ በግልፅ የሚታይ እውነታ ነው። ይህንን ሸክም ሸማቹ ለብዙ ዓመታት ተሸክሞ ኖሯል፣ እየኖረው ካለው የመከራ ሕይወት የሚያወጣው ኹነኛ እና አስተማማኝ አካል አለን ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል።

በየደረጃው ያሉ የንግድ ቢሮዎች፣ ጽሕፈት ቤቶች ሸማቹን ኅብረተሰብ ለመታደግ ዋጋ እንዲረጋጋ ቁጥጥር እያደረግን ነው ቢሉም መሬት ላይ የወረደ ዘላቂ መፍትሔ ሸማቹ ኅብረተሰብ ሊያገኝ አልቻለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በሸማቾች ማኅበራት በኩል ችግሩን ለመፍታት ቢሞከርም ማኅበራቱ የራሳቸው ውስንነቶች አሏቸው። ያሉባቸው ውስንነቶች ጥቂቶቹ፡- የኅብረተሰቡን ፍላጎት የሚያረካ በቂ አቅርቦት አለመኖር፣ ለኅብረተሰቡ በየቀኑ ከሚያስፈልጉ ሸቀጦች ይልቅ አላስፈላጊ ምርቶች መከማቸት፣ ለሕገወጥ አሠራር እና ለብክነት የተጋለጡ መሆን ተጠቃሽ ናቸው።

የሸማቾችን ችግር ለመፍታት የተዘየዱ መላዎች
በሌላ ጎኑ ደግሞ መንግሥት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተጨማሪ የሸማቹን ኅብረተሰብ ችግር ለመፍታት በሚል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣንን በአዋጅ ማቋቋሙ ይታወቃል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እስከ አሁን ድረስ የአቅሙን ጥረት አድርጓል፣ ሆኖም ሸማቹ ኅብረተሰብ ያለበትን ችግር የሚቀንስ ሆኖ አልተገኘም። በመገናኛ ብዙኀን የተወራ ሁሉ በተግባር እየታየ ነው ማለት አይቻልም። እስከአሁን ባለው የሥራ ታሪክ መሥሪያ ቤቱ እንቅስቃሴ አድርጎ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሸማቹን የሚታደግ ሆኖ አይስተዋልም። እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሸማቹ ላይ ያለው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ጫና መቋቋም በማይቻልበት ደረጃ መድረሱ እና ደካማ አገልግሎቶች መበራከት በየጊዜው የምንኖረው ሕይወት ነው።

በንግድ ልውውጥ ሒደት ውስጥ በሸማቹ ላይ አስከፊ ጫና እንዲደርስ ከሚያደርጉ መንገዶች መካከል አንድ ኹለቱን ልጠቁም። አንደኛው ለሸማቹ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን የሚያቀርበው የነጋዴው ክፍል የራሱ ችግሮች ቢኖሩበትም የገፈቱ ቀማሽ ግን ሸማቹ ነው። ነገር ግን ተመሣሣይ ምርቶችን ለሸማቾች የሚያቀርቡ ነጋዴዎች በመመሳጠር ተፈላጊው ምርት አንድም ከገበያ እንዲጠፋና ሰው ሠራሽ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋሉ፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ የመሸጫ ዋጋ ተመን በመወሰን የትርፍ ህዳጋቸውን ከ100 ፐርሰንት በላይ (የመጨረሻው ጣሪያ የማይታወቅ) ያደርጉታል። የዚህ ሴራ ተጠቂ ሸማቹ ኅብረተሰብ ነው። ይህ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሸማቹን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከድህነት ወደ ባሰ ድህነት ደረጃ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

ሌላው መንገድ ደግሞ ከአምራቹ ገበሬ እስከ ሸማቹ ድረስ ያለው ሰንሰለት እንዲረዝም በማድረግ በመሀል ያለው የደላላው ክፍል በገበሬው እና በሸማቹ ትከሻ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምር የግል ጥቅሙን ያሳድዳል። ይህ ሁሉ ኮንትሮባንድ ከመቀነስ ይልቅ እየባሰበት እና ሕጋዊ ነጋዴዎችም ከገበያ ላለመውጣት ወደ ሕገወጥ ንግድ መግባታቸውን ከተለያዩ ምንጮች መረዳት ተችሏል። ለአገር ውስጥ ፍጆታ መዋል የሚገባቸው የግብርና ምርቶች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ጎረቤት አገር በኮንትሮባንድ መወጣቱ አቅርቦት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደር ባሻገር አገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በየጊዜው እያሳጣ ነው። የምርት እጥረት ሲፈጠር ለደላላውና ለስግብግብ ነጋዴዎች ሠርግ እና ምላሽ ይሆንላቸዋል። ሀብት ለማጋበስ ተግተው ይሠራሉ፣ ሚሊዮኖችን ወደ ድህነት ይገፈትራሉ፣ በድህነት ውስጥ የነበሩት ከድህነት ወለል በታች ይወርዳሉ። የዚህ ድምር የተዛባ የሀብት ክፍፍል ሊያሰፍን ችሏል።

በኢንዱስትሪ በበለፀጉት እና ዴሞክራሲ እያደገባቸው በሚገኙ አገራት የሸማቾች ጉዳይ ለመንግሥት ዐቢይ አጀንዳ ሆኖ በታሪክ የዘለቀ ነው። መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላት ለሸማቾች ጥበቃ ተግተው በመሥራት በኑሮ ውድነት የሚመጣውን ጫና እንዲቋቋሙት ያደርጋሉ። ለሻጭ እና ለገዢ አመቺ የገበያ ስርዓት እንዲኖር አስቀድመው በመሥራታቸው የምርት እጥረት ወይም ሌላ ሰው ሠራሽ ሆነ ተፈጥሮአዊ ችግሮች ሲፈጠሩ ሸማቹ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጫናዎችን ለመቀነስ ይሞክራሉ። በተለይ ዴሞክራሲ እያደገባቸው በሚገኙ አገራት የሸማቹን ኑሮ ለማቃለል አጋዥ መሣሪያ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት በሸማቹ ኅብረሰተብ ተነሳሽነት እና ነፃነት በየአገሩ የተመሠረቱ ነፃ የሸማቾች ማኅበራት (Independent Consumers Societies) ናቸው።

የአገራችንን ኹነት ስንዳስስ በንጉሡ ዘመን የሕዝብ ቁጥርም አነስተኛ እና ምርትም በቂ ስለነበር በተጨማሪ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች የበረቱ ባለመሆናቸው በዜጋው ላይ የኑሮ ጫና የለም ማለት ያስችላል። የደርግ አስተዳደር ሲመጣ በተከተለው የኅብረተሰባዊነት ርዕዮት መሠረት ከግሉ ይልቅ የመንግሥት ይዞታ (ፐብሊክ ሴክተር) የበላይነት ስለነበረው መሠረታዊ ሸቀጦች በቀበሌ ኅብረት ሱቅ በኩል ከተተበተቡባቸው ችግሮች ጋር በአንጻራዊነት ምርቶችን ያቀርቡ ነበር። በዚህ ወቅት የአየር ባየር ንግድ፣ ተፈላጊ ሸቀጦችን መሰወር፣ ማከማቸት በብዛት ይከናወን ነበር።

በኅብረተሰቡ የሚፈለጉ ሸቀጦች ከገበያ ሲጠፉ በውድ ዋጋ ለሕዝቡ በመሸጥ ራሳቸውን ያበለፅጋሉ። ከ1983 በኋላ ግን የግል ይዞታ ይበረታታ ስለነበር ስርዓት ያልተበጀለት ነፃ ገበያ ባናቱ ደግሞ የሌብነት መንሰራፋት የሕዝቡን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲገባ አድርጎታል። ላለፉት ኹለት ዐሥርተ ዓመታት መሠረት ልማት ተስፋፍቷል። ነገር ግን የመሠረተ ልማት መስፋፋት ለኢኮኖሚ ዕድገት መሣሪያ ሆኖ ያገልግል እንጂ በራሱ በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ ቀጥተኛ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። በመሆኑም የዋጋ ግሽበቱ እና ኑሮ ውድነቱ ሲያሻቅብ መንግሥት በደርግ ጊዜ የነበረውን የሸቀጥ አቅርቦት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል በማድረግ ገበያውን እያረጋጋሁ ነው ቢልም የኑሮ ውድነቱ ጫና ሲቀነስ አይስተዋልም።

መስከረም 26/2012 የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በኹለቱ ምክር ቤቶች የአዲስ ዓመት የጋራ ስብሰባ ላይ ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር ውስጥ “በ2012 ከውጭ አገራት በብዛት ሸቀጦችን በማስገባት የዋጋ ንረትን መንግሥት ለመቆጣጠር እንደሚሠራ” ገልፀዋል። ይህ እርምጃ መልካም ሆኖ በገፍ ምርት ስለገባ ብቻ መፍትሔ ሊሆን ግን አይችልም፤ ተጨማሪ ድጋፍ ይፈልጋል።

ስለዚህ መፍትሔው ምን ይሁን?
(1) ነፃ የሸማቾች ማኅበር (Independent Consumers Society) መመሥረት በአሁኑ ወቅት ለሸማቹ በተግባር የሚሟገትለት አካል የለም። ስለዚህ ገለልተኛ እና ከመንግሥት ተጽዕኖ ነፃ የሆነ የሸማቾች ማኅበር መመሥረት ያስፈልጋል። በአንድ ወቅት የንግድ ውድድር የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አገር ዐቀፍ የሸማቾች ማኅበር ለማቋቋም እየሠራ መሆኑን ከመገናኛ ብዙኀን ማድመጤ ትዝ ይለኛል። ስለዚህ በመመሥረት ሒደት ውስጥ የማስተባበሩን ሥራ አጠናክሮ ቢቀጥል፣ አገር ዐቀፍ ነፃ የሸማቾች ማኅበር ከተመሠረተ ብዙ የመቆጣጠሪያ፣ ግፊት ማሳደሪያ እና ሕገወጦችን ማቆም የሚያስችል ርምጃዎችን በመውሰድ ሸማቹ ኅብረተሰብ ለምዝበራ አይጋለጥም፤

(2) አሁን በወረዳ ደረጃ ያሉትን የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለኅብረተሰቡ መሠረታዊ ሸቀጦችን ለማቅረብ አቅም እንዲኖራቸው ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤

(3) የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በብቁ ባለሙያዎች እንዲመሩ በማደረግ አሠራራቸውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና አገልግሎታቸውን የዘመነ እንዲያደርጉ እና ሀብታቸው ለብክነት እንዳይጋለጥ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ በአዲስ መልክ ማደራጀት፤

(4) የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ከገበሬ ማኅበራት ጋር የማስተሳሰር ሥራ በመሥራት ከአምራቹ ወደ ሸማቹ ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር የንግድ ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራቹ እንዲጠቀም በማድረግ የሸማቹን ኅብረተሰብ ኑሮ ማሻሻል ያስችላል።

በመቀጠል ከተናጠል እርምጃ ይልቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት (የንግድ ሚኒስቴር፣ የንግድ ቢሮዎች፣ የንግድ ጽሕፈት ቤቶች፣ የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ነፃ የሸማቾች ማኅበር፣ የሥነ ልኬት እና ደረጃዎች መዳቢ መሥሪያ ቤት፣ ሌሎች የሚመለከታቸው መንግሥታዊ፣ የግሉ ሴክተር እና ሲቪል ማኅበራት እና የሸማቹ ኅብረተሰብ) በጋራ እና በተናጠል ሲንቀሳቀሱ በሸማቹ ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት በደረጃ በመቀነስ ጎን ጥራት ያለው እና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ማቅረብ ያስችላል።

ካሳዬ አማረ በአድማስ ዩኒቭርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። በኢሜል አድራሻቸው amarek334@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com