መንግሥት ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት ዋስትና ይስጥ!

Views: 507

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 11/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት፣ መስከረም 26/2012 ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ያደረጉትን የመክፈኛ ንግግርን መሠረት ላደረጉ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።

በተለይ የውጪ አገር ፓስፖርት ኖሯቸው የሚድያ ባለቤት ለሆኑ የሰጡት ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂ አዘል ማብራሪያን ተከትሎ፣ የኦሮሞ ሚድያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር እና ‘አክቲቪስት’ የሆኑት ጃዋር መሐመድ፣ በፌስቡክ ገጻቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት እኔን በተመለከተ ነው በሚያስብል አኳኋን ወዲያወኑ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህንንም ብዙዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ተቀባብለውታል፤ በመደበኛው የመገናኛ ብዙኀንም ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በእኩለ ሌሊት ጃዋር መሐመድ መንግሥት የመደበላቸው ጠባቂዎች ከእውቅናቸው ውጪ በእኩለ ሌሊት እንዲነሱ ሊደረጉ መሆኑን የሚገልጽ እንዲሁም እሳቸው ላይ ጥቃት ለማድረስ የተጠነሰሰ ሴራ መኖሩን የሚገልጽ መልዕክት በአፍን ኦሮሞ፣ በእንግሊዝኛ እና ዘግየት ብሎ ንጋት ላይ ደግሞ በአማርኛ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ፣ ብዙ ወጣቶች (‘ቄሮዎች’) ቦሌ በተለምዶ ጃፓን ኤምባሲ በሚባለው ቦታ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በቀጥታ ተምመዋል።

በማስከተልም ንጋት ላይ የአዲስ አበባ መግቢያ እና መውጫ የሆኑ አውራ ጎናዎችን በመዝጋት ወደ መዲናይቱ የሚገቡና የሚወጡ ሰዎችን እንቅስቃሴ ገድበዋል። ረፋድ ላይ በተሰሙ ዜናዎች ደግሞ በአብዛኞቹ የኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ድሬዳዋንና ሐረርን ጨምሮ በተመሳሳይ የተቃውሞ ድምፆች ተሰምተዋል፤ “የጃዋር ጥቃት ጥቃታችን ነው” በሚል ስሜት።

እነዚሁ ወጣቶች ባደረጉት እንቅስቃሴ የዜጎችን እንቅስቃሴ ከመግታት እና የየከተማውን ነዋሪዎች መረጋጋት እንዳይኖራቸው በማድረግ የሥጋት ምንጭ ከመሆን ባሻገር በተለያዩ ቦታዎች እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት በደቦ ፍርድ ቀጥፈዋል፤ በርካታ ሰዎችም ለይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል። እንዲሁም ወጣቶቹ የእርስ በርስ ግጭት ፈጥረው በራሳቸው ላይም ጉዳት አድረሰዋል።

በሰዎች ላይ ከሕይወት መጥፋት እና ከአካል መጉደል ባሻገር በአገሪቱ ላይ ትልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ እንዲደርስ አድርገዋል። ፍብሪካዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በርካታ ተሸከራካሪዎች ተቃጥለዋል፤ የግለሰብ ቤቶችም ጋይተዋል።

እንደዚህ ዓይነት ግጭቶች ሲፈጠሩ የዚህ ሳምንቱ ብቸኛ አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰላምና ደኅንነት እጦት በሰፊው ተስተውሏል፤ ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክር ቤት ማብራሪቸው ላይ ጉዳዩን አሳንሰውና አቃለው ያዩት ቢሆንም።

ለአብነት ለመጥቀስ በአማራ እና በትግራይ ክልል መንግሥታት መካከል በንጽጽር ረዘም ላለ ጊዜ የዘለቀ የቃላት ጦርነት እና ፍጥጫዎች በማካሔድ ላይ ይገኛሉ። አንዳንዴም የኹለቱ ክልሎች ፍጥጫና የቃላት ጦርነት በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ ሳይሆን ኹለት ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታት ያስመስላቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሶማሌ እና አፋር አዋሳኝ ከተሞች የድንበር ይገባኛል በየጊዜው በሚነሱ ግጭቶች ክቡሩን የሰው ልጅ ሕይወት ሲነጥቅ እና አካል ሲያጎድል መመልከት የተለመደና ተራ ድርጊት እየሆነ ለመምጣቱ እማኝ መጥቀስ አያስፈልግም። በእርግጥ የኹለቱ የክልል መንግሥታት በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሸማጋይንት ችግራቸውን በሰከነ ውይይትና ድርድር ለመፍታት መስማማታቸው ተዘግቧል። ድርድሩ ውጤት ካስመዘገበ ይበል ያሰኛል!

በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ ያሉት ግጭቶች በክልሎች መካከል ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ በክልል ውስጥ ጭምር መሆኑን ማሳያ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በአማራ ክልል በአማራ እና በቅማንት ሕዝቦች መካከል በየጊዜው የተፈጠሩ ችግሮች የሰው ሕይወት የቀጠፉ፣ የአካል ጉዳት ያደረሱና ንብረት ያወደሙ ግጭቶች ማስከተላቸው የተለመደ የዕለት ተዕለት ልምምድ ሆኗል።

በተመሳሳይ በሌሎች ክልሎች ውስጥም የሚታዩ ግጭቶች አሉ። በጋምቤላ ክልል በአኘዋክና ኑዌር፣ በአፋር ክልል በአፋርና ኢሳ በደበብ ክልል ሲዳማና ወላይታ እንዲሁም በጉራጌ ዞን መስቃንና ማረቆ ተጠቃሾች ናቸው።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አዲስ አበባ የሚወስዱ መንገዶችን እንዲሁም የፌዴራል አገር አቋራጭ የሆኑ መንገዶችን ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ የተደራጁ ወጣቶች መዝጋት በተደጋጋሚ መከሰቱ ይታወቃል። ይህም መሠረታዊ የመንቀሳቀስ መብት መገደብ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ማስከተሉ እሙን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንገድ መዝጋትና ስብሰባ ማደናቀፍን በተመለከተ “መንገድ መዝጋት ይቅርና ድንበር መዝጋት እድገት አያረጋግጥም በሚባልበት በዚህ ዘመን መንገድ መዝጋት የኋላ ቀርነት ፖለቲካ ውጤት ነው፤ የብሽሽቅ ፖለቲካ ውጤት እና አላስፈላጊ ነው። አዳራሽ ሰዎች ተሰብስበው መንግሥት ለመቃወም ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ለመስደብ በሚሰበሰቡበት ወቅት አዳራሽ [ውስጥ] ገብቶ መበጥበጥም ትክክል አይደለም። ሰው በሰላማዊ መንገድ በአዳራሹ ውስጥ ሐሳቡን እንዲገልጽ ካላለማመድን በስተቀር ወደ አመጽ መግባቱ አይቀርም” ብለዋል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝቦች መካከል ግጭት መፍጠር ማንንም አሸናፊ እንደማያደርግ በመጠቆም ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ የሰላምና ደኅንነት መታጣት ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡት መካከል ይገኝበታል።

ይሁንና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሾች ወቅታዊውን አገራዊ የሰላምና ደኅንነት ሥጋት አሳሳቢነት ከግንዛቤ ያላስገቡ የተለሳለሱና የተድበሰበሱ ምላሾች ናቸው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። መንግሥት ከቃላት በዘለለ በተግባር የሚገለጥ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እርምጃዎች በመውሰድ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን መተማመንና ከለላ መጠናከር አለበት።

በእርግጥም መንግሥት የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ሲወድቅ በቀጥታ በጉዳዩ ላይ ጥርት ያለ አቋም በመውሰድ ለሕዝብ አለኝታ መሆን ሲገባው በተደጋጋሚ ቸልተኝነት፣ “አልሰማሁም አላየሁም” በሚል ኀላፊነትን በወቅቱ ያለመወጣት ወይም አደጋ ከደረሰ በኋላ ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ይስተዋላል።
ሆኖም መንግሥት ባሉት ዓይንና ጆሮዎች ቢቻል የሰላምና ደኅንነት ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት አሊያም ከደረሰም በኋላ ተመጣጣኝ የሆኑ አፋጣኝ እርምጃዎች መውሰድ፣ የኅብረተሰብ ሰላምን ማስጠበቅ ዋነኛ ተልዕኮው መሆኑን የዘነጋው ይመስላል።

እነዚህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በየጊዜው እየተፈጠሩ ያሉ በተለይ ከማንነት ጋር የተያያዙ ግጭቶች፣ የደቦ ፍርዶችና የመንገድ መዘጋቶች በሌሎች አገራት እንደታየው ወደለየለት ስርዓት አልበኝነት እንዳያመራ ስትል አዲስ ማለዳ ሥጋቷን ትገልጻች። በሊቢያ፣ በሶሪያ እንዲሁም በየመን የታዩት የጎበዝ አለቃነት መበራከት ምን ያክል ስርዓት አልበኝነትን እንዳስከተሉ ብሎም ለአገር መፍረስ ዐቢይ ሚና መጫወታቸው ዓለም ያወቀው ጉዳይ ነው።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ተለያዩ ክፍሎች ቀስ በቀስ እየተበራከተ የመጣውን ስርዓት አልበኝነት ሳይቃጠል በቅጠል ካልተባለ አገሪቱን ልትወጣው ወደማትችለው አዘቅት ውስጥ ይከታታል። ስለዚህ መንግሥት ብቸኛ የኀይል ባለቤትንት (monopoly of violence) ስላለው ኀይሉን በሕግ አግባብ መጠቀም ይገባዋል። ምክንያቱም መንግሥት የዜጎች የሰላምና ደህነት ከለላ መሆን ስለሚገባው። በተጨማሪም ስርዓት አልበኝነት ከነገሰ አገር እንዳይፈርስ ያሰጋልና መንግሥት ኀላፊነቱን ይወጣ። በዚሁ አጋጣሚ አዲስ ማለዳ መንግሥት ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት ዋስትና ይስጥ ኃለፊነቱንም በአግባቡ ይወጣ ስትል በአጽንዖት ታሳስባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com