“ስሜ ለምን? ነው” ፤ የለምን ሲሳይ ግለ ታሪክ

Views: 391

ስሜ ለምን? ነው” – My Name Is Why በሚል ርዕስ ስመጥሩ ኢትዮ- ኢንግሊዛዊው ገጣሚ በራሱ ሕይወት ዙሪያ የጻፈውን፣ ለገበያ በዋለ በኹለተኛ ሳምንት ብዙ ቅጂዎች የተሸጡለት መጽሐፍ ሆኖ በኢንግሊዝ በሚታተመው ሰንዴይ ታይምስ ላይ የተመዘገበውን መጽሐፍ ያነበቡት ቤተልሔም ነጋሽ፣ እይታቸውን አካፍለዋል።

 

 

የመጽሐፉ ርዕስ ፡ “ስሜ ለምን? ነው” – My Name Is Why
ደራሲ ፡ ለምን ሲሳይ
የገጽ ብዛት – 208
አሳታሚ – ካኖንጌት መጽሐፍት
የህትመት ዓመት ፤ ነሐሴ 2019 እኤአ
ለንደን፤ ዩናይትድ ኪንግደም
ዋጋ – 16፡99 ፓውንድ

“በዜማ የተሞላ፣ የሚያም ግን ደግሞ በተስፋ የተሞላ ታሪክ ….. የሚሰባብር፣ ብርሃንን የሚሻ” ኦብዘርበር ጋዜጣ
“አስደናቂ ታሪክ” ሰንዴይ ታይምስ
“ከዚህ መጽሐፍ የሚያስገርመው ነገር ፈጠራ ታሪክ አለመሆኑ፣ በእርግጥ ሆኗል። የሚገርም ታሪክ ነው” ቤንጃሚን ዘፋንያህ

ሰሞኑን በሃገራችን ካለው ውዥንብርና ሥጋት፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ምን ማለት እንዳለብኝም ባለማወቅ፣ ለዛሬ ከብዙ አታካች ጉዳዮች አረፍ እንድንል፣ መታከቱ ያልፋል በሚል እንደማሳለፊያም የመጽሐፍት ቅኝት ይዤ መጥቻለሁ። መጽሐፉን በቅርብ ላታገኙት እንደምትችሉ ቢገባኝም ራሱ ደራሲው ወገናችን ለምን ሲሳይ በመጽሐፉ መግቢያ “መጽሐፉ ለኢትዮጵያውያንም ነው” ስላለ ለእኛ የተባለውን ትንሽ ቅኝት ላደርግበት ስለወደድኩ ነው።

የኢትዮ- ኢንግሊዛዊው ስመጥር ገጣሚ ባለብዙ ስምና ክብር ለምን ሲሳይ በመንግሥት በማደጎ ልጅነት በእጓለ ማውታን ድርጅቶች፣ ማንነቱ ተደብቆት እንደልጅ መዳበስ ናፍቆት በመንግሥት እጅ ሲያድግ የደረሰበትን አሳዛኝ ግን ድንቅ ታሪክ የተረከበት መጽሐፍ ነው፤ ስሜ ለምን ነው ሲል የሰየመው መጽሐፍ።
ለምን ከስሙ ጀምሮ አስገራሚ ታሪክ ያለው ልጅ ነበር። ለአማርኛም ቢሆን ለምን ለልጅ የወጣ ስም ሰምተን የምናውቅ አይመስለንም። ኢንግሊዝኛ ሲሆን ደግሞ የበለጠ አስገራሚ ይሆናል፤ ስሙን በኢንግሊዝኛ በቀጥታ ተርጉሞ የመጽሐፉን ርዕስ My Name Is Why ያለውም ለዚህ ይመስለኛል።

በዛ ላይ ባልተንዛዛው ግለ ታሪኩ የሕይወቱን ብዙ ክንውኖችና ሲያድግ ሆድ ሆዱን የሚበሉትን በኋላ ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ የደረሰባቸውን እውነቶች የጠየቀበትም ነው። ለምን?
ለምን ከእናቱ ጋር ተለያየ፣ አሳዳጊ ወላጆቹ ለምን ጠሉት፣ መንግሥት እናቱ ስትፈልገው እንደነበር ለምን ደበቀው? ስሙን ለውጦ ከወገን ከዘሩ ለይቶ በእጓለ ማውታን እንዲድግ ለምን ፈረደበት? ለምን? ለምን?

የለምን መጽሐፍ በኢንግሊዝ በሚታተመው ሰንዴይ ታይምስ በጣም ብዙ ቅጂዎች የተሸጡለት መጽሐፍ ሆኖ ለመመዝገብ የበቃው ነሐሴ 29 ሽያጭ ላይ ውሎ ኹለተኛውን ሳምንት ሳይጨርስ ነበር። የመጽሐፉ ማስተዋወቂያ ላይ በግልጽ እንደሚለው “መንግሥት ህፃን ልጅ ሰርቆ እንዴት ያስራል? ይህንንስ ምስጢር አድርጎ መቆየት እንዴት ይቻለዋል? ይህ መጽሐፍ ይህንን ያብራራል”
ለምን 17 ዓመት ሆኖት፣ ሲወለድ የተሰጠውን የልደት ሰርቲፊኬት እስኪያገኝ እናቱ ያወጣችለትን ትክክለኛ ስሙን እንኳን አያውቅም ነበር። ይጠራ የነበረው በማደጎ ሂደት ሲያልፍ ጉዳዩን ይከታተል የነበረው ሰው ባወጣለት ስም ኖርማን (የራሱን ስም ነበር ሰውየው የሰጠው) እና ከፋም ለማም ቤተሰብ ብሎ በሚያውቃቸው ሰዎች የቤተሰብ መጠሪያ ኖርማን ግሪንውድ ተብሎ ይጠራ ነበር። በ17 ዓመቱ እናቱ ለምን ብላ እንደሰየመችው፣ በዘርና በምንጭም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ተረዳ።

መጽሐፉ ‹‹ስሜ ለምን ነው›› ይህንን ማንነቱንና ፍቅር፣ የኔ የሚለውን ወገን ፍለጋ ለዓመታት የተራበ የተጠማ በብዙ መልስ ያልነበራቸው ጥያቄዎች ራሱን ሲያስጨንቅ ያደገ ልጅ ታሪክ ነው። ካለፈበትና ከሆነው በተቃራኒ በ21 ዓመቱ የግጥም መጽሐፍ ለማሳተም የበቃ፣ ግጥሞቹ በለንደንና ሌሎች የኢንግሊዝ ከተሞች አደባባዮች የቆሙለት ድንቅ ገጣሚና ጸሐፊ ለመሆን የበቃ ነው። ታሪኩ በአብዛኛው ስለተጨማለቀው አሳፋሪ ስለሚለው የኢንግሊዝ የእጓለማውታን ሲስተምና አሠራር ሲሆን የዚህ ዘመን ስኬቱ ዓለምም ሚዲያም በሚያውቀው መልኩ በመጽሐፉ አልተካተተም።

መጽሐፉ የተፃፈበት ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ምዕራፍ መግቢያ ጣል የሚያደረገው ግጥም በቋንቋና በአገላለጽ ላይ ያለውን ጌትነትና ምጥቀት የሚያሳይ ነው።
ምሳሌ ብናይ – በግርድፉ ለመተርጎም ከሞከርኩት ጋር ኢንግሊዝኛውም እነሆ
(Chapter 2)
I will build an Embassy
In your heart over time
There is a plot of land inside me
Build one in mine
ኤምባሲዬን እገነባለሁ
በልብሽ – በጊዜ ሒደት
በልቤ ባዶ መሬት አለ
አንቺም የራስሽን ገንቢበት።
የለምን ልጅነት ያልተረጋጋ የማይጨበጥ ትዝታ የነበረው ነበር። ከህፃንነቱ ወራት እስከ 12 ዓመቱ በቆየበትና እስከ 17 ዓመቱ መጠሪያው ከነበረው ግሪንውድ ቤተሰብ የነበረውን የልጅነቱን ትዝታ፣ ያደገበትን ግቢ ውብ ዛፍና አበቦች፣ በልጅነቱ የነበረውን የተጫዋችነትና በሁሉም የሚወደድ ባህሪ ድምቀት በልጅነት ዓይን ይተርካል። በዚያው መጠን በሌላ ጽንፍ በትምህርት ቤቱ በቆዳው ቀለም ከሌሎች የተለየ ስለነበር የሚደርስበትን ትንኮሳና መገለል ይዘረዝራል።

ከዚያም በ12 ዓመቱ በልጅነት ዓለሙ የሚያውቃቸው ቤተሰቤ ያላቸው አንፈልግህም ሲሉት ዓለሙ ሲጨልም፣ ለመቆየት ሲጣጣር አቅም አጥቶ ህፃናት ማሳደጊያ ሲገባ፣ በዚህ ሁሉ በልጅ አዕምሮ ያጠፋው ጥፋት እንዳለ ሲጠይቅ፣ የሃዘን የደስታና የጥንካሬ ታሪኩ መጽሐፉን እንዳናስቀምጠው ያደርገናል።
የልጅነቱን ብቸኝነት፣ የሁኔታውን አሳዛኝነት የገለጠበትን አንድ ግጥም ብናይ
He lost touch at night
Their fingertips withdrew
Nobody touched him, light,
Except you
በማታ ማንነቱን ረሳ
ጣቶቻቸው ተሰበሰቡ
ማንም አልነካውም፤ ብርሃን
ካንቺ በቀር
ለምን ታሪኩ በመጨረሻ ተገጣጥሞ በመጽሐፍ እንደቀረበው ቅርፅ እንዲይዝ ያስቻለው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ለ34 ዓመታት ታግሎ በመጨረሻ ሙሉ ፋይሉን መንግሥት ለዓመታት በሱ ላይ የሰነደውን ሰነድ ማግኘት ሲችል ነበር። ከዚሁ ዶኩመንት ያገኛቸውን ደብዳቤዎች (የእናቱን የልጄን መልሱልኝ ተማጽኖ ጨምሮ) ኦፊሻል ውሳኔዎች፣ አስተያየቶች፣ ግምቶች፣ ትንተናዎች አለፍ አለፍ እያለ ዋና ዋናዎቹን በመጽሐፉ ገጾች አትሟቸዋል። በነገራችን ላይ መንግሥት ልጅነቱን ስለነጠቀው፣ እንዳይጠገን አድርጎ ስለሰበረው፣ መልሶ የማያገኘውን ከእናቱና ከወገኖቹ ጋር የማደግ ዕድል ስለወሰደበት መንግሥትን ፍርድ ቤት ገትሮ ከፍርድ ቤት ውጪ በተደረገ ድርድር መጠኑ ያልተገለፀ ካሳ እንዲከፈለው ተደርጓል።

ለምን በሥራዎቹ፣ በዓለም እየዞረ በሚያቀርባቸው አነቃቂ ንግግሮች በሚያገኘው ገቢ እሱ ባደገበት የእጓለማውታን ሥር ለሚያድጉ ልጆች ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም አቋቁሞ ይሠራል። በተቋማት የሚገኙ ልጆች በተለይ በገና ወቅት ታዋቂ ሰዎችና ሌሎችም አብረዋቸው እንዲያሳልፉ የገና እራት የሚባል ፕሮግራም በየዓመቱ በመላው ኢንግሊዝ እንዲካሔድ ያስተባብራል፤ ይመራል።

ለምን የተወለደው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1967 ዊጋን በተሰኘች የሰሜን ምዕራብ ኢንግላንድ ከተማ ሲሆን ኢትዮጵያዊት እናቱ ለትምህርት ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የነፃ ትምህርት ዕድል አግኝታ በመጣችበት ከጋብቻ ውጪ ፀንሳ ነበር። በወቅቱ ኢንግሊዝ ይደረግ እንደነበረው መውለጃዋ ሲደርስ በተቋም ገብታ ወልዳ ወደ ትምህርት ስትመለስ ‹‹ስጨርስ ልጂን ትመልሱልኛላችሁ›› ብላ እሺ ሲሏት እውነት መስሏት አምና የሰጠች ናት። ከዛ ምን ሆነ የሚለውን ከመጽሐፉ እንድትረዱ ስጋብዝ፤ በብዙ መከራ ውስጥ አልፎና ወላጅ አልባ ሆኖ አድጎ ለከፍተኛ ስኬትና ለዓለም አቀፍ እውቅና መብቃት ይቻላል የሚለውን በማስመር በራሱ በለምን ሲሳይ ግጥም ልሰናበት።
Look what was sown by the stars
At night across the fields
I am not defined by my scars
But by the incredible ability to heal
እዩ በኮከቦች የተዘራውን
ሌሊቱን በመስኩ ሁሉ ላይ
በጠባሳዬ አልገመትም
ለመዳን ባለኝ ድንቅ ችሎታ እንጂ
(ምዕራፍ ዘጠኝ መጀመሪያ)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com