የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤት ውሎ አንድምታዎች

Views: 288

ፕሬዝዳት ሳሕለወርቅ ዘውዴ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የ2012 የመክፈቻ ጉባኤ ላይ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ በተወካዮች ምክር ቤቱ በጥቅምት 11/2012 የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአባላቱ የተነሱ ጥያቄዎች ላይ መልስ ሰጥተዋል።

ይጀመራል ተብሎ ከተያዘለት ቀጠሮ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ዘግይቶ የተጀመረው ጉባኤው፣ 375 የምክር ቤቱ አባላት የተገኙበት ነበር። ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተወሰነ ቀደም ብለው ወደ አዳራሹ ከገቡት መካከል የሆኑት የሰላም ሚኒስተሯ ሙፈሪያት ከሚል በምክር ቤቱ የግራ ረድፍ ቀዳሚውን ወንበር ይዘዋል። ወደ አዳራሹ የሚገቡትን ባልደረቦቻቸውን ያለመታከት ሰላምታ የሚሰጡት ሚኒስትሯ ከመቀመጫቸው ብድግ በማለት በፈገግታ ሲነጋገሩ ይታያሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ አዳራሹ ተከታትለው መግባታቸውን ተከትሎም በአዳራሹ ውስጥ የነበረው ጫጫታ እንዲሁም በሙዚቃ ማጫወቻው ሲሰሙ የነበሩት የፍቅር ዘፈኖች ተቋረጡ።

የምክር ቤቱ ሠራተኞች ለጋዜጠኞች እና ለምክር ቤቱ አባላት በቀይ ወረቀት ላይ የሰፈረ እና ከጉባኤው 10 ቀን በፊት የታተመ የጥያቄ ቀደም ብሎ በመበተናቸው የሚነበቡትን ጥያቄዎች መከታተል እንብዛም ከባድ አይደለም።

ቀደም ብለው ከተነሱ ጥያቄዎች መካከልም የመጪው አገራ ዐቀፍ ምርጫ አንዱ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው የምክር ቤቱን መቀመጫ መቶ በመቶ የያዘው ፓርቲአቸው ካቀደው የውህድት ጉዳይ ጋር አያይዘው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ማቴዎስ ገለቦ የተባሉት የምክር ቤቱ አባል ያቀረቡት ጥያቄ በተለይም በአገሪቱ ያለው የሰላም እና የመረጋጋት ችግር እንዴት ተፈትቶ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ለማካሔድ ይቻላል ሲሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

‹‹ችግር አልባ ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ማድረግ አይቻልም፣ ዴሞክራሲም ባህል ነው፤ ይህንን ባህልም በመለማመድ እንጂ በመሸሽ አይሻሻልም›› በማለት ምርጫው በጊዜው ለማካሔድ ያስችላሉ ስላሏቸው ምክንያቶች ይዘረዝራሉ።

በምርጫው ማካሄጃ የጊዜ ገደብ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸውን ጨምሮ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ሲሰጡ ከነበሩት አስተያየቶች ይልቅ ረገጥ ባለ መልኩ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ገደብ መካሔዱ ላይ ያላቸውን አቋም ያስረዳሉ።

ምርጫውን ምን አልባት ማካሔድ ባይቻል ምክር ቤቱ እድሜውን ከክልሎች ጋር በመነጋገር ማራዘም ቢችልም ከሕዘብ ይሁንታ አግኝቶ የመጣ ተመራጭ ምክር ቤት ያለውን አቅም ያህል ስለማይኖረው ባይሆን ይመረጣል ብለዋል። መቶ በመቶ ተመርጦ ምክር ቤት መግባት እንደ ኢትዮጵያ ህብር በሆነ ህብረሰተብ ውስጥ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

‹‹እኛን ምክር ቤት ያስገባን ምርጫ ትክክል ስለሆነ እና አሁን ከዛ ያነሰ ሁኔታ ስላለ ምርጫ አይደረግ የሚለው አሳማኝ ስላልሆነ ምርጫ መደረግ አለበት ብዬ አምናለሁ›› ብለዋል። ‹‹እስካሁን የተደረጉ ምርጫዎች የወሰዱትን በጀት ተደምረው ለየሚበልጥ በጀት ተመድቧል፣ እስከ አሁን ከነበሩ አባላት በተሻላ ከእኛ ራቅ ያሉ ሰዎች ያሉበት ቦርድ ተዋቅሯል›› ሲሉ ክርክራቸውን አስረድተዋል።

የጠቅላዩ ንግግር ‹‹አናራዝመውም ግን ሊራዘም ይችላል›› የሚል አንድምታ ያለው ይመስላል። በዚህም በቀጥታ ይራዘማል ባይሉም የማራዘም አማራጭ መኖሩን ያመለከተ እንደሆነ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ እንዲሁም የሕግ ተመራማሪው አደም ካሴ (ዶ/ር) ይናገራሉ። ለዓመታት የኢትዮጵያ የምርጫ ሕጎች ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን ያዘጋጁት አደም እንደሚሉት፣ ሕገ መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይካሔዳል ከማለት ባለፈ ዝርዝሮች እንደሌሉት ይጠቅሳሉ።

‹‹በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ ትልቁ ችግር የምርጫ መራዘምን በተመለከተ ዝርዝር ሁኔታዎችን የሚጠቁም እና ምርጫ መቼ፣ በማን እና እንዴት ይራዘማል የሚለው ላይ ዝርዝር ሕግ ያለመኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተረዱት ይመስላል›› ይላሉ። ‹‹ከሕግ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከቅቡልነት አንፃርም ምርጫውን ማራዘም አግባብ አለመሆኑን ቢገልፁም ከክልሎች ጋር በመነጋገር እናራዝማላን በማለት ጉድለቱን ለመሙላት ትርጓሜ የሚሰጥ የሚመስል ግልጽ ያልሆነ አስተያየት ሰጥተዋል›› ሲሉ ያክላሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተያየት ከፖለቲካ አንጻር ትክክለኛ አካሔድ ነው፣ ቢሆንም ከሕግ አንፃር ግን ውስብስብ ነው የሚሉት ባለሞያው ምርጫውን የማራዘም እርምጃ የሚጀመር ከሆነ የሕግ ጥያቄዎች ሊነሱ እንደሚችሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹የዴሞክራሲ ተቋማት ብዙ ጊዜ በጡንቻ ይመሰላሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሲጀመሩ አወዛጋቢ ቢሆኑም ምርጫን ጨምሮ ሌሎች የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎች በመለማመድ እንጂ በሽሽት አይሻሻሉም›› ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ ይደግፋሉ። አክለውም ምርጫ ቢካሔድ ችግር ይፈጥራሉ ተብለው የሚፈሩት አካላት አብዛኞቹ ምርጫ እንዲካሔድ የሚፈለጉ ከመሆናቸው ጋር ሲነፃፀር የችግሩን መፈጠር የበለጠ እርግጠኛ ያደርገዋል ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሻለ ሰላም የሰፈነበት፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሚካሔድ ማስተማመኛ ብለው ካቀረቡት ጉዳዮች መካከል መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መልኩ ተፎካካሪዎች ምርጫውን ካሸነፉ ሥልጣኔን በሰላማዊ መንገድ አስተላልፋለሁ የሚል ቃል በእርሳቸው በኩል መሰጠቱ አንዱ ነበር።

የምርጫ ሕጉ የተረቀቀበት እና የጸደቀበትን መንገድም ለምርጫው መሳካት የራሱ ሚና ይኖረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ሕጉ ከሌሎች ሕጎች በተለየ መልኩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሳይቀርብ በቀጥታ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን አንስተዋል። ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በሕጉ ላይ የተነሱ ጥቄዎች ዙሪያም በሚሊዮኖች ለመመረጥ የሚዘጋጅ ፓርቲ የቀረበው የድጋፍ ፊርማ ጥያቄ አግባብ አይደለም የሚል አስተያየትም ሰጥተዋል።

አደም በሌላውም ዓለም በምርጫ ለመወዳደር ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ የተለመደ እንደሆነ ጠቅሰው ይህም ቁጥራቸው በበዛ ፓርቲዎች ምክንያት መራጩ ህብረተሰብ እንዳይደናገር እንዲሁም ጠንካራ ፓርቲዎችን ለመለየት ገደቦቹ ያስፈልጋሉ ሲሉ ይሞግታሉ። በተለይ በሰለጠነው ዓለም ከፍተኛ የገንዘብ ማስያዣ የሚጠየቅ ሲሆን በእኛ ሃገር ግን የህንን ከመጠየቅ ይልቅ የተወሰነ ሺሕ የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ መጠየቁ አግባብ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከትግራይ ክልል ውጪ ይህንን ፊርማ ማሰባሰብ ያስቸግራል ብለው እንደማያምኑ እና አሁን ችግር ያለባቸው የሚባሉ አካባቢዎች ያለው ሁኔታም የሚረግብ ነው፣ እንደ አደም ገለጻ። ነገር ግን በትግራይ ክልል ፓርቲዎቹ ለመንቀሳቀስ የሚያስቸግር ሁኔታው ባሻገር ሕዝቡ ለገዢው ፓርቲ ካለው ድጋፍ አንፃር ሁኔታው በቶሎ መሻሻሉ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ያስረዳሉ።

‹‹ቅድመ ሁኔታዎች ማለት ከ 77 ጂንስ ሱሪ ማምረት እና ቀድመው ከተመረቱ አስር መካከል መምረጥ ማለት ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‹‹ሕዝቡ ቢያንስ በ1997ቱ ምርጫ ከምርጫ በኋላ በምርጫ ኮሮጆ ምክንያት የሚከሰቱ ግጭቶች የሰው ሕይወት ከመቅጠፍ ባሻገር ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ጠንቅቆ አውቋል፣ እንደ ኬንያ ካሉ የጎረቤት አገራት ወይም ከራሱ መማር ይችላል›› በማለት በሕዝቡ ዘንድ ይኖራል ስላሉት የፀጥታ ሁኔታ ተንብየዋል።

ይህንን በኹለት መልኩ የሚያዩት አደም ‹‹አንድ ሰው ሊታሰር ነበር በሚል መነሾ የተፈጠረውን ችግር በማየት ምርጫ ተሸንፌአለሁ የሚል አካል ቢመጣ የሚያመጣውን መልስ መመልከት ይቻላል›› የሚለውን ‹‹ምርጫው ወራት ይቀረዋል፣ ነገሮችን ማሻሻል ይቻላል እንዲሁም አሸንፋለሁ ብሎ ቀድሞ እርግጠኛ የሆኑት አካላት ችግር መፍጠራቸው አይቀርም›› ከሚል ሃሳባቸው ጋር በማጣመር ‹‹በኹለቱም አንፃር ከባድ የፖለቲካ አደጋ ቢሆንም አንዱን መምረጣቸው ግን ግድ ነው›› ይላሉ።

ሰልፍ የማይወጣ ሰው ምርጫ ይመርጣል የሚሉት አደም አሁን በአደባባይ የምናየው የሰው ብዛት እንደ ድጋፍ የሚቆጥሩ አካላት በኋላ ምርጫው ይዞት በሚመጣው ውጤት ላይ የራሱ ጫና መኖሩ አይቀርም ሲሉ ይናገራሉ።

ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የኢሕአዴግ ውህድትን በማስመልከት ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የመጀመሪያው ነጥባቸውም የፓርቲው ውህደት ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር መያያዙ አግባብ አይደለም ሲሉ የፓርቲ ፖለቲካን እድሜ ከሃገሪቱ እድሜ ጋር በማነፃፀር ‹‹ኢትዮጵያ የኢሕአዴግ አባት እንጂ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይሆንም›› ሲሉ ያብራራሉ።

የፓርቲው ውህደት ያልተፈጸመ ነው፣ የውህደቱ መልክ ላይ አሁንም ውይይት አለ፤ ደግሞም ውህደቱ መቼ ይሁን የሚለው ላይ እንጂ በራሱ ውህደቱ ይኑር የሚለው ላይ ተቃውሞ የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ግንባሩ ቢዋሃድ የተመሠረተው መንግሥት ላይ የቅቡልነት ጥያቄ ያስነሳል የሚሉ ጥያቄዎች አግባብ አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የግንባሩ ፓርቲዎች ስማቸውን ሲቀይሩ ጥያቄ አልተነሳም፣ የሚነሳበት የሕግ አግባብ የለም ሲሉ ይናገራሉ።

‹‹መንግሥትን የሚያቋቁመው ይህ ምክር ቤት እንጂ ሌላ አካል አይደለም፣ የሚያፈርሰውም ይህ ምክር ቤት ነው›› ሲሉም ሞግተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ የሚስማሙት አደም፣ ውህደቱን ከሕግ እና ከቅቡልነት አንፃር ይመለከቱታል። ‹‹ከሕግ አንፃር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፣ በኢትዮጵያ ምርጫ ስርአት ሕዝቡ የሚመርጠው ግለሰብን እንጂ ፓርቲን አይደለም፣ የኢሕአዴግን ተወካይ ነው እንጂ ኢሕአዴግን አይደለም›› ሲሉ ያስረግጣሉ። ‹‹ምክር ቤቱ እንደሚለው አንድን መንግሥት የሚመሠርትው ከ 50 በመቶ በላይ መቀመጫ ያለው ሲሆን ነው። እነዚህ ፓርቲዎች ወይም ቡድኖች የምርጫው ጊዜ መኖር አለባቸው አይልም፣ ምርጫ ከተካሔደ በኋላ አብዛኛውን ድምፅ ለማግኘት መሰባሰብ የተለመደ ነው።››

አደም እንደሚሉት ቅቡልነት ከሕዝብ የሚመጣ እንጂ ከሕግ ጋር የሚገናኝ ስላልሆነ መደበላለቅ የለበትም ይላሉ። ሕዝቡ ይህንን አይቀበልም ከተባለም ምርጫው ቅርብ ስለሆነ በአደራ ጊዜ መንግሥት መሻር ይቻላል እንጂ ምርጫውን ያለጊዜው መጎተት አግባብ አይሆንም ሲሉ አደም ያብራራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት ሰጥተው መልስ ከሰጧቸው ጥያቄዎች መካከል በመገናኛ ብዙኀን የሥነ ምግባር አጠባበቅ ላይ የተነሳው ጥያቄ አንዱ ነው። ‹‹የሚዲያው ሁኔታ መገራት ይፈልጋል›› በማለት ስለ ፍትኀዊ ምርጫ ባብራሩበት ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነፃ የሆነ ውድድር ለመፍጠር ግን ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። በተለይ በውጪ ሃገር ዜጋ በሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተያዙ ሚዲያዎች ላይ የሰላ ትችት አቅርበዋል።
ፕሬዘዳት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣ በተያዘው ዓመት የክልል የፀጥታ መዋቅርን ማጠናከር እንደ አንድ ዓላማ መገለፁ እንዳሳሰባቸው የተናገሩት ሙሐመድ ሀሰን ናቸው። ‹‹ክልሎች ተቀናሽ የሠራዊት አባላትን በማደራጀት ወታደራዊ አቅማቸውን በማፈርጠም ፉክክር የተጠመዱ ይመስላሉ፣ ፍጥጫውም የአንድ ፌዴራላዊት አገር ሳይሆን የተለያዩ ሀገራት ሽኩቻ እየመሰለ ይገኛል›› ሲሉ ጥያቄአቸውን በንባብ አስቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ፖሊሶችን ጨምሮ በሃገራችን በተለይ በሕገ ወጥ ገበያው የሚዘዋወረው የጦር መሣሪያ ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ ለግማሽ ቀን ያክል እንኳን ለማዋጋት የማይሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል። የክልል የፀጥታ አካላትን ማጠናከርም በተለይ በክልሎች ውስጥ የሚነሱ የፀጥታ ችግሮችን ለመቆጣጠር እንዲያስችል እንጂ ከሌላ ክልል ጋር ለመጋጨት ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል።

የሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ንግድን አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሠለጠነው ዓለም ተራምዶ ያለፈውን እና የረባ ግልጋሎት የማይሰጥ መሣሪያ የገባ በመሆኑ አገሪቱ የኋላቀር መሣሪያዎች ማራገፊያ ሆናለች ብለዋል።

‹‹ከመጣ በኋላ የሚውለው ወንድም ለመግደል ነው፣ ጎረቤት ለመግደል ቢገዛም ልጆች ራሳቸውን ይገሉበታል፣ መሣሪያ የሚጠቅም ነገር አይደለም፤ ደግሞም ትምህርት ይፈልጋል። ዝም ብሎ ክላሽ መያዝ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ሥልጠና ይፈልጋል›› ብለዋል።

የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥም በተቋማት የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ጋር የሚደረጉ ውይይቶችንም አጠናክረው አንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። አያይዘውም የሕግ ማስከበር ሥራው ዴሞክራሲን ወደ ኋላ በማይወስድ መልኩ እንደሚሠራ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዴሞክራሲን የሚያፍን ሰላም ማስከበር ትርፉ ኪሳራ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹ከሕግ በላይ በመሆን ኢትዮጵያን እና ህልውናዋን አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ነገር ካለ ግን ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን›› ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኑሮ ውድነቱን መዋቅራዊ እና ሰው ሠራሽ በማለት ለኹለት የከፈሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጥ ይዞ መጥቷል ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል። የመኖሪያ ቤት ችግር፣ የምግብ ችግር፣ ሥራ አጥነት እንዲሁም የምርት አጥረት ለኑሮ ውድነት አንዱ ችግር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣውን የቤት ኪራይ ዋጋ ለመቆጣጠር የተለያዩ የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ እንደተጀመረ ገልፀው፣ የሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክን እና የአዲስ አበባን ምሳሌ አንስተዋል። እንደ እስከዛሬው መንግሥት ለብቻው ሳይሆን ከግል ባለሃብቱ ጋር በመጣመር እንዲሁም ለግል አልሚዎች ሁኔታዎችን በማመቻቸት የቤት እጥረቱን ለመፍታት እንደሚሠራም ተናግረዋል።

‹‹እስከ አሁን ከገነባነው የቤት ፕሮጀክት በእጥፍ የሚበልጥ ፐሮጀክት ለመጀመር ዝግጅት ተጠናቋል›› ያሉም ሲሆን፣ ‹‹በቀን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚያመርተው ፋብሪካ ከኹለት ወር በኋላ ያልቃል፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬት ንጉሥ የረዱን እና በቀን 10 ሚሊዮን ዳቦ ማምረት የሚችለው ፋብሪካም በተያዘው ዓመት ሲጠናቀቅ የዳቦ ዋጋ ይረጋጋል።›› ብለዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን ቦታ በአግባቡ በመጠቀም እና የከተማ ግብርናን ተግባራዊ በማድረግ የምርት እጥረቱን መፍታት እንድሚቻል አመላክተው፤ ትምህርት ቤቶች አጥረው ያስቀመጧቸው ሰፋፊ ቦታዎችን በማልማት መጀመር ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።

በሦስት ወር የግብርና የወጪ ንግድ እቅድ ከ 100 በመቶ በላይ መሳካቱን እና በዓመቱ ከነበረው በቂ ዝናብ ምክንያት የምርት መጠን ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ይህም የኑሮ ውድነትን እንደሚያቃልል ጠቅሰዋል። የአገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጡ የብልጽግና መሰረት በተያዘው ዓመት ይጣላል የሚል እቅድ መኖሩንም ጨምረው ተናግረዋል።

‹‹በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቁን ኢኮኖሚ ስለምትገነባ እንደዚህ ዓይነት መሰናክሎች ቦታቸውን ለአዳዲስ ችግሮች ይለቃሉ የሚል እምነት በመንግሥት በኩል አለ›› ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com