የመጀመሪያ ደረጃ የካፒታል ገበያ ህግ በወር ውስጥ ይፀድቃል

Views: 791

ብሔራዊ ባንክ የመጀመሪያ ደረጃ የካፒታል ገበያ ስርዓትን የሚፈቅድ እና የሚያስተዳድር መመሪያ በመጪው አንድ ወር ተኩል ውስጥ ወደ ሥራ ሊያሳገባ ነው። ለኹለተኛ ደረጃ የካፒታል ገበያ መሰረት ይሆናል የተባለለትን ይህንን ሕግ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቅም የባንኩ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ በገንዘብ ሚኒስቴር ከሚገኙ ምንጮቿ እንደሰማችው፣ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ መመሪያው ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ቢሞከርም ሳይሳካ ቀርቷል። በተለይም የመንግሥትን የግምጃ ቤት ሰነድ እና ማንኛውም ዓይነት ቦንድ በዚህ ማእቀፍ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን ሰነዶቹን ከገዙ በኋላም ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ የማስተላለፍ መብት የሚሰጥ መመሪያ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሥራ ኀላፊ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በረቂቅ መመሪያው መሰረትም የሰነድ ሽያጭ ፉክክሩን ለግሉ ዘርፍ ክፍት በማድረግ ሲተችበት የነበረውን ከሦስት በመቶ የማይበልጥ የወለድ መጠንን በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል እና ይህም ባንኮችን ጨምሮ ማንኛውም ከ 5ሺሕ ብር በላይ አውጥቶ ሰነዶቹን ለመግዛት የሚችል ሰውን በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከልም ገበያው ውስጥ የተትረፈረፈ ገንዘብ ለመሰብዘብ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የተናገሩት ኀላፊው፣ በመጪው አንድ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይተገበራል ለተባለው የኹለተኛ ደረጃ የካፒታል ገበያ ስርዓትም ብዙ ልምድ የሚወሰድበት አንደሚሆን ጠቅሰዋል። ምንም እንኳን እንደሌሎች አገራት የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ተሟልተውና የዲጂታል የግዢ ስርዓቶችን ለጊዜው የማይካተቱ ሲሆን እስከዛሬ ሰነዶቹ በሚሸጡበት መልክ በአካል በመገኘት ግብይቱ እንደሚፈጸም ለማወቅ ተችሏል።

ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ሲባል የሚዘጋጁ ቦንዶችንም የመክፈያ ጊዜአቸው እስከሚደርስ ገንዘቡን የሚፈልግ ማንኛውም ባለቦንድ በፈለገው ዋጋ ሊሸጣቸው እንደሚችል አዲሱ ሕግ እንደሚፈቅድ ለማወቅ ተችሏል።

መንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶችን ለኹለት ምክንያቶች ሲጠቀምባቸው የቆየ ሲሆን፣ በተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀለት በጀት መሰረት የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥም ከገበያው ላይ በመሰብሰብ ክፍተቱን ለመሙላት የሚጠቀምበት መንገድ አንዱ ነው። በተጨማሪም በገበያ ውስጥ የሚሰራጨው ገንዘብ ሲትረፈረፍ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ሲባል የግምጃ ቤት ሰነዶችን መሸጥም የተለመደ አሰራር ነው።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ከባለሃብቶች ጋር ውይይት ያደረጉት የብሔራዊ ባንኩ ገዢ ይናገር፣ የመጀመሪያ ደረጃ የካፒታል ገበያውን የሚያስተዳድር መመሪያ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ይፋ ባደረጉ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ይፋ ይሆናል ማለታቸውም ይታወሳል።

ገዢው ይህንን ከተናገሩ ሦስት ሳምንታት ያለፉ ሲሆን እርሳቸው ባሉት ፍጥነትም ባይሆን በጥቅምት ወር ውስጥ ግን መመሪያው ፀድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአዲስ ማለዳ ምንጭ ተናግረዋል።

የባንክ ዘርፍ ተንታኝ የሆኑት አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት፣ የግምጃ ቤት ሰነድን ጨምሮ ሰነዶችን በሕግ በመደንገግ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ካፒታል ገበያ ማሳደግ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ዘርፉ በአግባቡ አንዲሠራ የሚያስችል አሰራር መፍጠር ከተቻለ ብቻ ነው። እስከዛሬ ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ የካፒታል ገበያውን ውጤታማ እንዳይሆን ያደረገው በተለይም የግሉን ሴክተር ለመሳብ ያለመቻሉ ሲሆን የመንግሥት ተቋማት ግብይቱን ተቆጣጥረው ዝቅተኛ ወለድ እንዲኖረው እና የማያተርፍ ገበያ እንዲሆን በማድረጋቸው ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

‹‹የመጀመሪያ ደረጃ የካፒታል ገበያው የነፃ ገበያን መርህ በመከተል እንዲሠራ ካልተፈቀደ በስተቀር የኹለተኛ ደረጃ ገበያው ወይም ስቶክ ማርኬቱ ውጤታማ አይሆንም›› ሲሉ ይናገራሉ። በኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበራት አክሲዮን ከሸጡ በኋላ የገቡትን ቃል ለመፈፀም ሲቸገሩ መመልከት የተለመደ ነው የሚሉት አብዱልመናን ዘርፉን በአግባቡ አቀናጅቶ የሚመራ ስርአት መዘርጋት ከተቻለ እና የመጀመሪያ ደረጃ የካፒታል ገበያ በውጤታማነት መምራት ከተቻለ የኹለተኛ ደረጃ ገበያውን ስኬት የሚወስን ይሆናል ሲሉም ጨምረው ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com