ሴቶችን ከጥቃት የመጠበቅ ቸልተኝነት

Views: 493

ሥልጣናቸውን ምሽግ አድርገው በሴቶች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙና የፈጸሙ መኖራቸውን በመጥቀስ የሚጀምሩት ቤተልሔም ነጋሽ፤ በተለያዩ ማስፈራሪያዎች ምክንያት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችም ሪፖርት ሳያደርጉ በዝምታ እንደሚቀሩ ያነሳሉ። መንግሥትም የሴቶችን ጉዳይ በተለያዩ ዘርፎች አደረግሁ የሚለው ከምልክትነት አላለፈም፤ ሴቶችን ከጥቃት በመጠበቅም እርምጃ እየወሰደ አይደለም ይላሉ።

 

 

በትግራይ ክልል አዲ ዳዕሮ ወረዳ የደኅንነት አባል ነው የተባለ አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ግለሰብ ስልጣኑን ተጠቅሞ በወረዳው የሚገኙ 50 ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር ሪፖርት እንዳያደርጉ በማስፈራራት፣ መላ ወረዳውን ካሸበረ በኋላ በሕዝብ እሮሮ በቁጥጥር ሥር ቢውልም በ6000 ብር ዋስ መለቀቁ ሌላ ቁጣን ፈጥሮ የወረዳዋ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጡ አስገድዷል። ይሄ ነውር የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አልሳበም፤ አንድም ሚዲያ ዝርዝር ጉዳዩን ለማየትና ተጨማሪ ዘገባ ለመሥራት ጥረት አድርጎ አላየሁም።

ስለመልካም አስተዳደር ብዙ በሚባልበት እንዲህ አይነቱ ሥልጣንን ተጠቅሞ የሚደረግ ጥቃት በዝምታ መታለፉ ሁልጊዜም እንደምንለው መንግሥት ለሴቶች ጉዳይ ግድ የለውም፣ ሴቶችን በሚመለከት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን አደረገ ለመባል ወይም ተራማጅ መንግሥት ተብሎ ለመጠቀስ ወይም ለእርዳታ ድርጅቶች ፍጆታ ብቻ ነው በሚለው ጥርጣሬያችን እንድንፀና ያደርገናል።

ምናልባት ከላይ የተጠቀሰው ኹነት እስከዛሬ ከምንሰማው የተለየ ቢሆንም እነኝህ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉ በክልሉ የሴቶች ጥቃት እየተስፋፋ መምጣቱን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። ምሳሌ ብንጠቅስ ጣዕሞ የተባለች አንዲት ሴት እንዲሁ በፍቺ ተለይታው ሌላ ትዳር በመሠረተ የቀድሞ ባሏ ልጆችዋ ፊት በደረሰባት የጥይት ጥቃት መንቀሳቀስ የማትችል ሙሉ አካሏ የማይታዘዝ ሆኖ አልጋ ላይ መዋሏ በመገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ እንዲሁ ሌላ ሴት የአሲድ ጥቃት ደርሶባት የዓይን ብርሃኗን አጥታ ልጇን ለማሳደግ የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር።

የሕዝብና የጤና ጥናት 2016 ሪፖርት እንደሚለው ትግራይ ክልል ፆታን መሠረት አድርገው ከሚፈፀሙ ጥቃቶች በኢትዮጵያ ኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ እንግዲህ በተለይ ወሲባዊ ጥቃቶች ሪፖርት የመደረግ አጋጣሚያቸው ዝቅተኛ መሆኑን ላየ ትክክለኛ ስዕሉን የማያሳይ መሆኑን ይረዳል። እንደሪፖርቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ለቤተሰብ፣ ለባሎቻቸው፣ ለህክምና ባለሙያዎች፣ ለጓደኛ ወይም ለፖሊስ ጥቃት እንደደረሰባቸው የሚናገሩት ከጥቃት ሰለባዎች 7 በመቶው ብቻ ናቸው።
በክልሉ እየተስፋፋ የመጣውን በሴቶች ላይ የሚፈጸም የኃይል ጥቃት በመቃወም ጥቅምት 9 ቀን 2012 የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሐየድ አራት ወንዶችና ስምንት ሴቶች በድምሩ አስራ ኹለት አባላት ያሉት የሰልፉ አስተባባሪ ኮሜቴ ለመቐለ ከተማ አስተዳደር ጥቅምት 3 ቀን 2012 በተጻፈ ደብዳቤ ቢጠይቅም ሰልፉ መከልከሉ እየተነገረ ነው።

አስገድዶ መድፈርና የወሲብ ጥቃት በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ሁሉ አስከፊው ነው። ሴቶች በመደፈር ምክንያት አካላዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ ሥነልቦናዊ እና ስሜታዊ ጉዳት ይገጥማቸዋል። በመደፈር ላይ የሚሠሩ ጥናቶች እንደሚሉት መድፈር ወንዶች በሴቶች ላይ ያላቸውን የበላይነት በኃይል ለማስረገጥ የሚጠቀሙበት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው። የሴትን ሰውነት የመቆጣጠር፣ የማዋረድ፣ ዝቅ የማድረግ አስከፊ ድርጊትም ነው። ለዚህም ነው ሰውነትን ብቻ ሳይሆን ስብእናንም መድፈር ነው የሚባለው።

በአብዛኛው ማህበረሰቡ ለሴቶች በሚሰጠው ዝቅተኛ ግምትና ቦታ ምክንያት እንዲሁም በተለይ በልጆች ላይ የሚያደርሰውን ከባድ የሥነልቦና ጫና እና በወሲብ ሕይወታቸው በአጠቃላይ በስብእናቸው ላይ ጥሎ የሚያልፈውን ከባድ ጠባሳ ባለመረዳት ነገሩን በሽምግልና ለመጨረስ፣ ገመናችን ይወጣና ሰው ምን ይለናል (በተለይ ለልጆቹ ዘመድ የሆኑ ወይም ቅርበት ያላቸው ሰዎች ወንጀሉን በሚፈጽሙበት ወቅት) በሚል ሪፖርት ከማድረግ ይቆጠባሉ። በዚህም ወንጀለኞቹ ሳይቀጡ ይቀራሉ፤ ያም ብቻ ሳይሆን የሕዝብና የጤና ጥናት ከጠየቃቸው ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መካከል ለምሳሌ 59 በመቶው አጠገባቸው ባለ በሚያምኑትና በሚወዱት ሰው የወሲብ ጥቃት ገጥሟቸው እንደሚያውቅ ሲጠቅስ 49 በመቶው አካላዊ ጥቃት እንደገጠማቸው 29 በመቶው ደግሞ ጥናቱ ከተደረገበት ወቅት በፊት በነበረው አንድ ዓመት ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ሪፖርት ማድረጋቸውን ይጠቅሳል።

በማህበረሰባችን አተያይ ግን ጥቃት አድራሾች ወይም ደፋሪዎች የማይታወቁ ሰዎች፣ አውሬዎች፣ ከስንት አንድ አይነት የሚባሉ ሆነው ሲቀረፁ ይታያል። ሰዎች በአብዛኛው ስለ አስገድዶ መድፈር ሲያስቡ አንዲት ሴት በጨለማ ስትጓዝ ወይም ጭር ባለ አካባቢ ብቻዋን ስትሔድ አልያም በጣም አጭር ቀሚስ ለብሳ መንገድ ላይ ስትሔድ ወንዱ ድንገት ስሜቱ ተነሳስቶ የደፈራት አድርጎ ያስቡታል። ይሄ ግን ብዙ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች የሚፈፀሙበት እውነታ አይደለም። ይህ አስተሳሰብ ወንዱን እንደ እንሰሳ የሚያስቆጥር ብቻ ሳይሆን ያደግንበትን ባህል፣ ሃይማኖትና ሞራል ወሲብ በሃገራችን የተለጠፈበትን ውስብስብ አተያይ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው።

ከላይ የጠቀስኩትን የአዲ ዳዕሮን ጉዳይ ብናይ ጉዳዩን በማህበራዊ መገናኛዎች ያወጡት ሰዎች በሚያጋሯቸው ጽሑፎች ሥር የሚሰጡ አስተያየቶች የሚሳዩት ይህንኑ ነው። አብዛኛው ሰው ‹‹የደኅንነት መኮንኑ አውሬ ነው፤ ሰው አይደለም›› ሲል ተበዳዮቹ ባሎች፣ ወንድሞች፣ አባቶች የሏቸውም ወይ ብሎ የሚጠይቅም ነበር። መንግሥት ምነው ዜጎቹን መጠበቅ ተሳነው ያለ ግን አላየሁም።

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወሲባዊ ጥቃት በራሱ መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን የሚያስከትላቸው ሌሎች ጎጂ ውጤቶችም አሉት። ከሚጠቀሱትም መካከል አካላዊ ጉዳት፣ ሥነ-ልቦናዊ መንቋሸሽ፣ በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች፣ ተስፋ መቁረጥና መረበሽ፣ ያሳለፉትን ስቃይ በማስታወስ የሚፈጠሩ ሌሎች ጉዳቶች የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል።

ሥነ-ልቦናዊ እና ሥነ-አዕምሯዊ ህክምና፣ የምክርና ችግራቸውን በመረዳት ልባዊ ተቆርቋሪነት፣ ርህራሄ በማሳየት ድጋፍ መስጠት ባልተለመደበት እንደኛ ባለ ሃገር፣ ተጠቂዎቹ ሕይወታቸውን እንደገና ለማቋቋምና በማህበራዊ ሙሉነት ለመንቀሳቀስ እንዲሁም አዕምሯዊና አካላዊ ብቃት ያላቸው ዜጎች ለመሆን በእጅጉ ይቸገራሉ።
አስገድዶ መድፈር የከፋ ወንጀልና ጉዳት መሆኑን ማሳያው አንድ መንገድ በጦርነትና በሕዝቦች መካከል በሚኖር ጠብ አንደኛው በሌላው ላይ የሚፈጽመው ከፍተኛ ንቀትና ክህደት ማሳያ መሆኑንም ታሪክ ያስረዳናል። በቦስኒያ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ተደፍረው የጠላት ወታደሮችን ልጆች እንዲወልዱ ተደርገዋል። በኢራቅ ተነስቶ ተስፋፍቶ ለሶርያ ጦርት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል አንድ ሚና የተጫወተው አይ ኤስ አይ ኤስ የተሰኘው ጽንፈኛ ሚሊሻ አንድ ግፍና ወንጀል የጠላት ወገን ያለውን አካል ልጆችና ሚስቶች መድፈር፣ በወሲብ ባርያነት መጠቀም፣ በግድ ልጆች እንዲወልዱ ማድረግ ይጠቀሳል።
በእኛው አገርም በቡራዩ ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘም በሐዋሳና በአካባቢዋ አስገድዶ መድፈር ተፈጽሞባቸው ለእርግዝና የተዳረጉ ሴቶች መኖራቸውን በመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ሰምተናል።

በዚህ ዓምድ እንኳን በተለያዩ ዘርፎች መንግሥት የሴቶችን ጉዳይ ከምልክትነትና አደረግሁ ከማለት ባለፈ ግድ እንደማይሰጠው በተደጋጋሚ ስለገለጽኩ ዛሬም ከጥቃት መጠበቅ ለምን አቃተው የሚለውን ሳነሳ ለማስታወስ በሕገ መንግስቱ የተደነገጉትን በተግባር ግን የተረሱ የሚመስሉትን መብቶች በመዘርዘር ነው።

አንቀጽ 35 – የሴቶች መብት
ሴቶች ይህ ሕገ መንግሥት በአረጋገጣቸው መብቶችና ጥበቃዎች በመጠቀም ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው።
ሴቶች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው።
ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው። በዚህ በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማኀበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግሥት እና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው።
ሴቶች ከጎጂ ባሕል ተጽዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር አለበት። ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶች የተከለከሉ ናቸው።

ሀ) ሴቶች የወሊድ ፈቃድ ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የማግኘት መብት አላቸው። የወሊድ ፈቃድ ርዝመት ሴቷ የምትሠራውን ሥራ ሁኔታ፣ የሴቷን ጤንነት፣ የሕፃኑንና የቤተሰቡን ደኅንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕግ ይወሰናል።

ለ) የወሊድ ፈቃድ በሕግ በሚወሰነው መሠረት ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የሚሰጥ የእርግዝና ፈቃድን ሊጨምር ይችላል።
ሴቶች በብሔራዊ የልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በኘሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም፣ በተለይ የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ኘሮጀክቶች ሀሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው።

ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት አላቸው። በተለይ መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው። እንዲሁም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት አላቸው።
ሴቶች የቅጥር፣ የሥራ እድገት የእኩል ክፍያና ጡረታን የማስተላለፍ እኩል መብት አላቸው።

ሴቶች በእርግዝና እና በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከልና ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት መረጃ እና አቅም የማግኘት መብት አላቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com