የምክትል ከንቲባው የሥልጣን ጉዳይ

Views: 223

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እንዳለፈው ሳምንት ስማቸው ተነስቶ የሚያውቅ አይመስልም፤ በማህበራዊ ድረገጽ ባሳለፍነው ሰሞን በተደጋጋሚ ሲነሱ ቆይተዋል። መጀመሪያ 300 ሺሕ ተማሪዎችን የሚያካትተው የምገባ መርሃ ግብር መጀመሩን ተከትሎ በምስጋና ነው ሲነሱ የነበረው። በድንገት ግን ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል የሚል መረጃ ወጣ።

የአዲስ አበባ አወዛጋቢ ጉዳዮች በየእለት እየጨመሩና አዲስ እየሆኑ መምጣታቸው የታወቀ ቢሆንም የከንቲባው ከሥልጣን መነሳት ጉዳይ ለብዙዎች አዲስ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የሥልጣን ዘመናቸው አብቅቷል የሚሉት ሁሉ ‹‹ማን ቦታውን ሊረከብ ነው?›› ሲሉ ዘረዘሩ፤ የገቢዎች ሚኒስትሯ አዳነች አቤቤ እንደሚሆኑ በማሰብም ስለ አዳነች የአመራር ብቃትና ስለቀደመው ልምዳቸው እያነሱ የሚወያዩ ጥቂት አልነበሩም።

ይህን ዜና በእርግጠኝነት የተነገረ ነበሩ። ታማኝ የተባሉ የማህበራዊ ድረ ገጽ ምንጮች ከታማኝ ምንጭ ያገኘነው ነው ብለው ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከከንቲባነታቸው እንዲነሱ ተወስኗል፤ በእርሳቸው ቦታ የገቢዎች ሚኒስትር አዳነች አቤቤ መታጨታቸውም ተሰምቷል።›› ተብሎ ቀርቧል።

እንደዚህ ዜና ብዙዎች እርግጠኛ ሆነው የተቀባበሉትም ያለ አይመስልም። አንዳንዶች ላለመስማት ይመስላል የጠላት ጆሮ ይደፈን ብለው ኢንጅነሩ ለአዲስ አበባ ነዋሪ የሠሩትን መልካም ተግባራት እያነሱ ተቆጭተዋል። ለምን ይሆን የሚነሱት ሲባልም የዓድዋን ማዕከል ለማስገንባት ማቀዳቸው፣ ለተማሪዎች የደንብ ልብስ እና ደብተር እንዲሁም ምገባ ማዘጋጀታቸው፣ ኢሬቻ በዓል ላይ ያደረጉት ንግግርና አዲስ አበባ የሁላችን ናት ማለታቸው ባናደዳቸው ሰዎች ምክንያት ነው ሲባል ነበር።

ሳይውል ሳያድር ዜናው ትክክል አይደለም ተባለ። የከንቲባው ጽሕፈት ቤትም ‹‹ኢንጅነር ታከለ ኡማ አሁንም በሥራ ላይ ይገኛሉ። ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል ተብሎ የወጣው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ለመግለጽ እንፈልጋለን።›› በማለት ገለጹ። ነገሩ ግን አስቀድሞ ሀሰተኛ እንዳልነበር እርግጠኞች ብዙ ናቸው፤ ይልቁንም በአመራሮች በኩል ኢንጅነሩን ከኃላፊነት በማንሳቱ ላይ የሃሳብ ለውጥ ኖሮ ሳይሆን አልቀረም።

ከዚህ በኋላ ኢንጅነሩ ከኃላነታቸው እንደማይነሱና ሥራ ላይ እንዳሉ ተነገረ። ‹‹አሁን ላይ ሀሳቡ ተቀይሮ እና ሥራቸው ላይ እንዲቀጥሉ ሲደረግ “የወጣው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ለመግለፅ እንፈልጋለን” ተብሎ በከንቲባው ፅ/ቤት የፌስቡክ ገፅ መገለፁ አግባብ አይደለም። ፈፅሞ ልክ አይደለም።›› ሲል አስነበበ።

ይሄኔ ታድያ በዛው በማህበራዊ ድረ ገጽ አንዳንዶች በሕዝብ መወደደ ምን ያህል ዋጋ እንዳለውና በሕዝብ ተቃውሞ ምክንያት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተሰጠው ውሳኔው ተቀልብሷል ሲሉ ተናገሩ። እንግዲህ የበላዮች የአዲስ አበባ ሰው እንዳይከፋው ሰግተው ያወረዱትን ውሳኔ መልሰው አጥፈውት ይሆን ወይ ሊፈትኑ ይፋ ያደረጉት አልታወቀም፤ ለጊዜው ግን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በሥልጣን እንደሚቆዩ ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com