ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት በሚያዘጋጀው አደገኛ የገንዘብ ማጠብ ያለባቸው ሃገራት ዝርዝር ውስጥ በድጋሚ ልትገባ ትችላለች ተባለ

Views: 527

የአውሮፓ ኅብረት በመጋቢት 2011 ኢትዮጵያን ጨምሮ 23 ሃገራት የሚገኙበትን የገንዘብ እጥበት እና የሽብር ወንጀልን የመርዳት ከፍተኛ ክፍተት ያለባቸው ሃገራትን መሰረዙን ተከትሎ አዲስ በሚዘጋጀው ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ በድጋሚ ልትገባ እንደምትችል ተገለጸ።

በመጋቢት ስብሰባው የአውሮፓ ኅብረት ይህ የጥቁር ዝርዝር በሚዘጋጅበት ወቅት የሚወሰዱ እርምጃዎች ግልፅነት የጎደላቸው በመሆናቸው ምክንያት ዝርዝሩ እንዲሰረዝ መወሰኑ ይታወሳል። የሚመለከታቸው የኅብረቱ ተወካዮችም 23ቱንም ሃገራት ማነጋገራቸውን እና የተሻለ ግልጽነት ያለውን ዝርዝር በፍጥነት እንዲዘጋጅ በማዘዝ ኅብረቱ የቀደመውን ዝርዝር ሰርዟል።

ይህንን ዝርዝር በማዘጋጀት ሒደት ውስጥ በመሰረታዊነት ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት ሃገራት ያላቸው የፖሊሲ እና የሕግ ቁርጠኝነት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል የሚሉት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ጌታቸው ተክለማርያም፣ኢትዮጵያ ውስጥ የተወሰኑ መሻሻሎች እንዳሉ ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ የለውጥ ጅማሮ በቂ በሆነ ቁርጠኝነት ያልተደገፈ እና በመሬት ላይም ለውጥ ከማምጣት ይልቅ በተወሰነ መልኩ የሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውሩ ባስ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ሲሉ ይናገራሉ።

‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በኢኮኖሚው ላይ ያለው ጫና ቀላል የማይባል ሲሆን በተለይም ይህንን የፖሊሲ ሃሳብ ለውጥ ተከትሎም አዳዲስ ፈጻሚ ተቋማት አልተቋቋሙም፣ ያሉት ተቋማትም አዳዲስ የለውጥ መተግበሪያ መንገዶች ይዘው ስላልመጡ ኢትዮጵያ ከአዲሱ ዝርዝር መግባቷ ላይቀር ይችላል።›› ብለዋል።

እንደ ባለሞያው ገለፃ ከሆነም የፋይናንስ ደኅንነት ተቋሙም ዓለማቀፍ ጫናን ለመቋቋም ሲባል የተመሰረተ እንጂ በተግባር በጥናት ላይ ተመስርቶ መልስ የሚሰጥ አይደለም ሲሉ ጌታቸው ይናገራሉ። አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ የሕገወጥ ደረሰኝ ሥራ ተንሰራፍቶ የሚገኝ ሲሆን በየሰፈሩ ያሉ የመኪና ሱቆች እንኳን በኢኮኖሚው ውስጥ ምን እየተካሔደ እንዳለ የሚያስተላልፉትን መልዕክት ተረድቶ እርምጃ መውሰድ የማይችል ተቋም ነው ይላሉ።

የፋይናንስ ደኀንነት መረጃ ማዕከል ለገንዘብ እጥበት እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመርዳት ወንጀል ተጋለጭ የሆኑ ዘርፎችን በጥናት የመለየት ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ የገንዘብ እና የሂሳብ ተቋማት፤ ጠበቆች እና የሕግ አካላት ለትርፍ ያልተቋቋሙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ሪል ስቴቶች ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በወንጀል የመደገፍ ድርጊት ሰለባ እንዳይሆኑ ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በዚህ በኅብረቱ የጥቁር ዝርዝር ውስጥ ገብታ በነበረችበት ወቅት ከአውሮፓ ሃገራት የገንዘብ ተቋማት ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች ላይ የራሱ ጫና እንደነበረው ኃላፊው ይናገራሉ። አክለውም በወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ ተፅዕኖው ቀላል የማይባል እንደነበር እና በ2012ም አዲስ በሚሰናዳው የግራጫ ዝርዝር ውስጥ ላለመግባት ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ መሆኑን የፋይናንስ ደኀንነት ማዕከል የሕዝብ ግኑኙነት ኃላፊ እንዳለ አሰፋ ገልፀዋል።

በያዝነው ዓመት ኢትዮጵያን ከዚህ ስም ዝርዝር ውስጥ ለማስወጣት እና በአዲሱ ግራጫ ሊስት ስም ዝርዝር ውስጥ እንዳትመደብ ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የኅብረቱ አካላት ጋር እየሠራን ነው ብለዋል።

በሕገ ወጥ መንገድ የተገኝ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅርብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን መከላከል ዓለማቀፋዊ ግዴታዎች ናቸው ያሉት እንዳለ አሰፋ፣ ተቋሙ የማቀናጀት እና የማስተባበር ሥራ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በ 2011 ከ80 በላይ በሕገወጥ መንገድ የተገኝ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅርብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን በመያዝ ለሕግ አካላት ማስተላለፋቸውንም ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ ተንታኙ ‹‹ቁጥጥር የሌለው›› የሚሉት ይህ የፋይናንስ ደኅንነት ተቋም ጠንካራ እና ከተለዋዋጩ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ቁመና ኖሮት ሊቋቋም ይገባል ሲሉ ይናገራሉ። በተጨማሪም ሌሎች የጸጥታ ተቋማት ላይም የሚታየው የሕግ የበላይነትን የማስከበር ክፍተቶች ካልተፈቱ ወደ ዝርዝሩ ተመልሶ የማይገባበት ምክንያት የለም ሲሉ ይሞግታሉ።

ከምንም በላይ ግን የፖለቲካ አለመረጋጋቱን መስመር ማስያዝ እና የተጀመሩ የፖሊሲ ለውጦች ተቋማዊ ካልተደረጉ በዓለማቀፍ የጥቁር መዝገብ መግባት ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የራሱ ጫና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ከመጠን በላይ የከረረው የሃገሪቱ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ ክንድ እና የማይገመተው የፋይናንስ ፖሊሲ፣ ዜጎች ምን ሊመጣ እንደሚችል ባለማወቃቸው ምክንያት ያላቸውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ከመደበኛው የኢኮኖሚ ዝውውር ያስወጣሉ፤ እንደ ጌታቸው ገለፃ። ይህም ዜጎች ተገደው ወደ ሕገወጡ የገንዘብ ዝውውር መስመር እንዲገቡ እንደሚያደርጋቸው እና በዚህ ረገድም መንግሥት የተወሰነ መሻሻል እንዳሳየ ተናግረዋል። በባንክ እና በኢንሹራንስ መስክ የተደረጉ የሕግ ማሻሻያዎችም የበለጠ ተጠናክረው መካሔድ እና በተለይም አገልግሎት ማቀላጠፍ ላይ ካልተሠራ የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ከመሰረቱ መፍታት የሚቻል አይደለም ሲሉ ገልፀዋል።

አውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያን በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚረዱ መንገዶችን ከማዘጋጀት አንፃር ክፍትት ከታየባቸው 23 ሀገራት ተርታ የመደባት ሲሆን እነዚህን ክፍተቶች መቅረፍ ካልተቻለ ኅብረቱ በሚያዘጋጀው አዲስ ግሬይ ሊስት (Gray list) በተሰኘ የሀገራት ስም ዝርዝር ውስጥ የምትገባ ይሆናል።

መቀመጫውን በኔዘርላንድ ያደረገው እና በ28 ኅብረቱ ሃገራት ሽብር፣ የመረጃ መረብ ደኀንነት እና ሌሎች የተቀናጁ ወንጀሎችን በሚከታተለው ኢውሮፖል (Europol) መረጃ መሰረት ከኅብረቱ ዓመታዊ ጥቅል ሀገራዊ ምርት ውስጥ ከ0.7-1.28 በመቶ የሚሆነው በሙስና፣ በጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፤ በአደንዛዥ እፅ ንግድ፣ ታክስ በማጭበርበር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ባሉ ሕገወጥ ድርጊቶች የተመዘገበ ስለመሆኑ ጥርጣሬ መኖሩን አሳውቋል።

በመሆኑም ድርጊቱ በኅብረቱ ሃገራት ዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ አደጋ የሚደቅን እና በኅብረቱ ሃገራት የገንዘብ ስርዓት ላይ አደጋን የሚፈጥር በመሆኑ እነዚህን ሕገ ወጥ ድርጊቶች ለመከላከል የሚያስችል የገንዘብ ዝውውር ሕግ እና መሰል ክፍተት ያለባቸውን ሀገራት በአዲሱ ግራጫ ሊስት ውስጥ እንደሚያካትት አሳወቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com