ዳሰሳ ዘ ማለዳ ማክሰኞ መስከረም 27/2012

Views: 330

1-የአፍሪካ ልማት ባንክ ፣የኮሪያ ኢግዚም ባንክ፣የአውሮፓ ህብረት፣የተባበሩት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) እና ቢግ ዊን የተባሉ ድርጅቶች ለተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚውል የ84ነጥብ 22ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………

2-በማዕድናት ላይ ዕሴት ባለመጨመር በቀጥታ ከመላክ እና በቂ የሆነ የዓለም አቀፍ ገበያ ትስስር ካለመኖር ጋር ተያይዞ የሚታየውን የገቢ ማነስ ለመቅረፍ እና ተጨማሪ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው። የተጠቀሱትን ተግባራት የሚከታተልና የሚያስተባብር  በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) የሚመራ ኮሚቴም ተዋቅሯል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………

3-በኢትዮጵያ በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች በአገልግሎትና በመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት በአቅርቦት ችግር ሳይሆን የህገወጥ ደላሎች ጣላቃ ግብነት መሆኑን  የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር  ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥም  በሕገ- ወጥ ደላሎች አማካኝነት አየር በአየር በመኪና ላይ ሕገወጥ ግብይት ሲያካሂዱ የተገኙ 59 መኪኖች አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም 52 መኪኖች ጤፍና ሌሎች እህሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል።(አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………

4–የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ መስከረም 27/2012 ባካሄደው 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ  የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚያደረገው የድጎማ በጀት የማከፋፈያ ቀመርን ለሁለት ዓመት አራዝሟል።ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት የነበረውን ቀመር ከ2010 በጀት ዓመት ጀምሮ ለሶሰት ዓመታት እስከ 2012 በስራ ላይ እንዲወል መወሰኑ ይታወሳል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

………………………………………………………………

5 ከኬሚካልና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምርቶች በ2011 በጀት ዓመት 38ነጥብ2 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ  ማሳካት የተቻለው ግን 18ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ወይም የእቅዱን 48 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገልጿል።ለተገኘው የውጭ ምንዛሪ ዝቅተኛ መሆን የኃይል መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት ውስንነት የፀጥታ ችግሮች በዋናነት ተጠቅሰዋል።(ኢቢሲ)

 

………………………………………………………………

6-  በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ በመካሄድ ላይ በሚገኘዉ አገራዊ ምርጫና የምርጫ ባለድርሻ አካላት ሚና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ የተገኙት የቀድሞዉ የናይጀሪያ የምርጫ ኮሚሽን ሊቀ መንበር አታሂሩ ጄጋ (ፕሮፌሰር) ታአማኒ የሆነ የምርጫ አስተዳደር መገንባት በሚቸልበት ሁኔታ ላይ የአገራቸዉን መልካም ተሞክሮ አካፍለዋል።የአንድ አገር ምርጫ ስኬታማነት የሚወሰነዉ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ በሚከናወኑ ተግባራት መሆኑን በመገንዘብ፣ ከምርጫ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ፍፃሜ የሚከናወኑ ተግባራት በአግባቡና በጥንቃቄ መከናወን እንዳለባቸዉ ገልጸዋል።(አብመድ)

………………………………………………………………

7- በሐገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዉ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር  ከ9ኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ከተዉጣጡ የካቢኔ አባላት ጋር ዉይይት አድርጓል፡፡በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዉ ላይ ያተኮረ ሲሆን አላማዉም ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ያስመዘገበችዉ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አሁን ላይ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በመለየት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማምጣትና የኢኮኖሚ እድገትን ማስቀጠል እንደሆን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።(ዋልታ)

………………………………………………………………

8- ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለታዳሽ ኃይል ትኩረት እንዲሰጥ አሳስባለች።የአየር ብክለት በዓለማችን የአየር ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑንና ለአካባቢ የአየር ለውጥ መነሻ የሆኑ ጉዳዮችንና የችግሩ አባባሽ ሁኔታዎችን በመለየት በጋራ መከላከል አስፈላጊ መሆኑን    የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንግራ አንደርሰን ተናግረዋል።(ኢቢሲ)

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com