የሐረር ቢራ ምርት አሽቆለቆለ

Views: 1111

በሄኒከን ኢትዮጵያ ባለቤትነት የሚተዳደረው ሐረር ቢራ ፋብሪካ ለውሃ አቅርቦት የሚጠቀምበትን በሐረሪ ክልል ፍንቅሌ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን የውሃ መሳቢያ መስመሮቹን እና ጄነሬተሮቹን እንዳይጠቀም ላላፉት ሁለት ዓመታት በአርሶ አደሮችና በወጣቶች በመከልከሉ ምክንያት ምርቱ ማሽቆልቆሉ ታወቀ።

ድርጅቱ 200 ሚሊየን ብር አውጥቶ የገዛቸው ጀነሬተሮችና ሌሎች መሳሪያዎችም አገልግሎት መስጠት አቁመው በፈሳሽ ማመላለሻ መኪና ውሃ ከሌሎች አካባቢዎች በማምጣት የቢራ ምርቱን መቀጠሉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።

የተቋሙ አንድ ከፍተኛ አመራርም ይህንኑ በማረጋገጥ ሐረር ቢራ ከ1970ዎቹ ጀምሮ የሚጠቀመው የውሃ መስመር ከዚሁ ከፍንቅሌ ወረዳ እንደነበር ተናግረው ሄኒከን ፋብሪካውን ገዝቶ ወደስራ ከገባ በኋላ በሃገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ በአካባቢው በተነሳው ችግር ወጣቶቹና አርሶ አደሮቹ መጠቀም አትችሉም በማለት አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

‹‹ጉዳዩን የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ለማ መገርሳን ጨምሮ ለተለያዩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ብናሳውቅም ከማህበረሰቡ ጋር ተነጋግረን እንዲፈታ እናደርጋለን ከማለት ባለፈ እስካሁን ውሳኔ ማግኘት አልቻልንም›› ሲሉ በቢራ ፋብሪካው ውስጥ በሃላፊነት ላይ ያሉት እኚህ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹በወረዳው ከሚገኙ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ጋር ለበርካታ ጊዜያት ውይይት ብናደርግም ፍላጎታቸውን መረዳት አልቻልንም›› ያሉት ኀላፊው፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት ዘመናዊ የመስኖ እርሻ ስርአት ለመዘርጋት ሃሳብ አቅርበው እንደነበርም ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሐረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኀላፊ አብዱላኪም ዮኒስ፣ የሐረር ቢራ የሚጠቀመውን ማንኛውንም የውሃ መስመር በመንግስት በኩል ምንም አይነት ክልከላ አልተደረገበትም ይላሉ። ነገር ግን ጉዳዩ ከገበሬዎች የመሬት ባለቤትነት ጋር የተያያዘ ከሆነ ግን ከአርሶ አደሩ ጋር በመምከር የሚፈታ ነው በማለት ፋብሪካው ግን ለሃረሪ ክልል አንድም አቤቱታ አላቀረበም ሲሉም አክለዋል።
‹‹ችግሩ ተፈጠረ ቢባል እንኳን የውሃ መስመሩን የዘጋው የአካባቢው አርሶ አደር ሳይሆን፣ ግርግሩን ተጠቅመው የሚንቀሳቀሱ አካላት ናቸው›› ሲሉ ይጠቅሳሉ። አልፎ አልፎ ገንዘብ ካልተሰጠን በማለት የውሃ መስመር የሚዘጉና ቆሻሻ መድፊያ ቦታዎችን አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚከለክሉ ወጣቶች በክልሉ መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ለሐረር ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚቀርበው ከድሬዳዋ 75 ኪሎ ሜትር አቆራርጦ እና አዶሌ፣ አዎዳይንና ሃረማያን አቋርጦና አዳርሶ የተረፈውን ውሃ በመሆኑ በክልሉ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንዳለ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። ይሄንን የውሃ መስመር ሃረማያ ላይ በመዝጋት ‹‹10 ሚሊዮን ብር ወደ አካውንታችን ካላስገባችሁ ውሃውን አንለቅም›› የሚሉ ግለሰቦች ውዝግብ ፈጥረው እንደነበር አዲስ ማለዳ በቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011 ዕትሟ መዘገቧ ይታወቃል።

የክልሉን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ኤረር በሚባል አካባቢ አዲስ የውሃ ፕሮጀክት ተቋቁሞ፣ ተመርቆ ሥራውን በጀመረ በአምስተኛው ወር፣ በእርሻ ቦታቸው ላይ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ ሲወጣ ድርቀት አምጥቶብናል፣ እርሻችንን በመስኖ ውሃ ማጠጣት አልቻልንም፣ ካሳ አልተከፈለንም በሚሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ ውሃው እንዲቋረጥ መደረጉንም ጋዜጣዋ ዘግባለች፡፡

የሀረር ቢራ ውሃ የሚጠቀምበትን የውሃ መሳቢያ በተመሳሳይ መቆረጡን የሚናገሩት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሐረሪ ከተማ ነዋሪዎች፣ የክልሉ መንግሥት ከእነዚህ ግለሰቦች ሰዎች ጋር ተደራድሮ 20 ሚሊዮን ብር መክፈሉ ተዘግቧል።

መሰረቱን በኔዘርላንድ ያደረገው ሄንከን ቢራ ፋብሪካ በ400 ሚሊዮን ዩሮ ተቋቁሞ ምርት ከመጀመሩ በፊት በደሌና ሃረር ቢራ ፋብሪካዎችን ከመንግስት የገዛ ሲሆን፣ በእነዚህ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት ዋሊያ፣ በደሌ፣ በደሌ ስፔሻል፣ ሐረር፣ ሐረር ሶፊና በክለር ቢራዎችን እያመረተ ለተጠቃሚ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ሄኒከን ቢራ ላለፉት 150 ዓመታት በዓለም የቢራ ገበያ የዘለቀ ሲሆን በዓለማችን በ70 አገራት ውስጥ የተቋቋሙት ከ160 በላይ የሄኒከን ቢራ አምራች ፋብሪካዎች ለ8 ሺ ያህል ሰራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com