ሰብኣዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ!

Views: 301

ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቷም ሆነ ውል ባሰረችባቸው ዓለም ዐቀፍ ድንጋጌ መሠረት ሰብኣዊና ዴሞክሪሲያዊ መብቶች የሚከበሩበት አገር መሆን ይገባታል። ይሁንና ይህ በኢትዮጵያ በምሉዕ እየተተገበረ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ወቅታዊ አብነቶችን ነቅሳ በማሳያነት ታነሳለች።

በቅርቡ በአማራ ክልል በቅማንት እና በአማራ ማኅበረሰብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው። በጉዳዩ ላይ የተሠሩ ዘገባዎች እናዳመለከቱት ግጭቱ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ተቀጥፏል። በርግጥ ከቅማንት ማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች በቀጥታ ከሚመለከተው ሕዝብ ባሻገር የአማራና የትግራይ ክልሎች በጠላትነት እንዲተያዩ፤ የቃላት ጦርነትና ጠብ አጫሪ እንዲሁም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የፀብ መነሻ፤ ያለመተማመን ሁኔታንና እርስበርስ በጠላትነት እንዲፈራረጁ ማድረጉ የአደባባይ ሚስጢር ከሆነ ዋል አደር ብሏል።

የፌዴራል መንግሥትም ጣልቃ ገብነትና ነገሮችን የማርገብ፤ ከምንም በላይ ደግሞ የዜጎችን ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ያደረጋቸው ሙከራዎች ፍሬ ሲያፈራ አልታየም። ሌላው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ የመጡበት በአደባባይ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ሕዝባዊ በዓላትን ማክበርን በተመለከተ መንግሥት ሁኔታቸውን ሆደ ሰፊ ሆኖ ከማየት፤ የዜጎችን ደኅንነት ከማስጠበቅ ይልቅ ተንኳሽ የሆነበት ብሎም ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የጣሰበት፣ ከሕግ ውጪ ለአጭር ጊዜም ቢሆን እስር የተፈጸመበት ሁኔታ መኖሩን አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

በመስቀል ዋዜማ የፌደራል ፖሊስ ያወጣው “ተንኳሽ” የሆነ መግለጫ ዜጎች መንግሥትን በጥርጣሬ እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር የሔደበት ጥብቅ አካሔድ፤ በአብዛኛው ጥሩ ሆኖ ሳለ አንዳንድ የመብት ጥሰቶች የታዩበት ሆኖ ማለፉ ግን ሕገወጥነት ነው።

የፌዴራል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ላይ በሕገ መንግሥት እውቅና ካገኘው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራ በመሐል የሚገኘው ክብ አርማ የሌለው ባንዲራ ይዞ መገኘት እንደማይቻል ማስታወቁ ጠብ የመጫር አካሔድ ይመስላል። ለዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራ ጋር ያላት ትስስር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አርማነት በዘለለ በመንፈሳዊ አንድምታ ጋር መያያዙ ከግምት ማስገባት ይገባ ነበር ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። የፌዴራል ፖሊስ ትኩረት መሆን የሚገባውና በዋዜማው ያሳየው የሕዝብን ደኅንነት ሰላም ለማረጋገጥ ጥብቅ የሆነ የፍተሻና የመከላከል ሥራ ላይ አተኩሮ ለመሥራት በቂ ነበር።

የፖሊስ አካሔድ ግን ግራ የገባውና ወጥነት የጎደለው እንደነበር ማየት ይቻላል። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የሆኑ የእጅ፣ የአንገት ጌጦችን፣ ቲሸርቶችን፣ ባንዲራዎች በመቀማት ተጠምዶ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞም ብዙ ሰዎች ለሰዓታት ታስረዋል፤ ተንገላትተዋል። ይሁንና በተመሳሳይ ቀለም ያላቸው የባሕል አልባሳት የለበሱትን፤ ትኩረት ለማሳያነት ያገለገሉ ቁሳቁሶችን አሳልፎ በሰፊው ሲታዩ ነበር። ይህ ወጥነት የጎደለው አሰራር ፖሊስን ትዝብት ላይ ጥሏል። የፖሊስ የሥራ ትኩረት ኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ማስከበር ላይ ብቻ ትኩረት ቢያደርግ ተመራጭ ይሆን ነበር ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በተመሳሳይም ዛሬ በአዲስ አበባ እንዲሁም ነገ ደግሞ በቢሾፍቱ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ ወጣቶች የፈለጉትን ባንዲራ በአደባባይ እንዲይዙ በይፋ የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር ጥብቅ ቁጥጥር መኖሩ የሚደገፍ ሆኖ የሰዎችን ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በመሆኑም ፖሊስ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሕግንና ስርዓትን የተከተሉ ከቆመለት ተቋማዊ ተልዕኮ እና መርህ ጋር የማይጻረሩ መሆን ይገባቸዋል ስትል ታሳስባለች።

ሌላው ሰሞኑን ከተስተዋሉና ከሰብኣዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ሴቶችን የሚመለከት ይገኝበታል። አንዳንድ ፖለቲካ እናራምዳለን ብሎም የመብት ተሟጋች ነን በሚሉ አካላት በጅምላ አልያም በተናጠል ሴት ግለሰቦች ላይ ያነጣጠሩ የመብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ተስተውለዋል። የሴቶች ክብር ዝቅ የሚያደርጉ መረን የለቀቁ እንኳን በአደባባይ በጓዳም ልንጠቀማቸው የማይገቡ ጸያፍ አገላለጾች በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ተለቀው እንካ ሰላንቲያ ሲያስከተሉ ተስተውሏል። ጸያፍ ስድቦቹ ሴትነት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሰብኣዊ ክብርን የሚያሳንሱ በመሆናቸው ሊወገዙ ይገባል፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አካልም ናቸው።

በእርግጥ ሥነ ጾታን በተመለከተ የኅብረተሰባችን ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። ይሁንና የሥነ ፆታን ጉዳይ በተመለከተ ኅብረተሰቡ ትኩረት እንዲሰጠው በተለይ ከሴት መብቶች ጋር የሚሠሩ ሲቪክ ማኅበራት እንዲሁም የኅብረተሰብን ሰላምና ደኅንነት የሚያስጠብቁ አካላት ንቃትን ከመስጠት፣ ግንዛቤን ከመፍጠር አንጻር ትኩረት ሰጥተው ሲሠሩ ወንጀል የሆኑትም ተለይተው ክስ የሚመሰረትባቸው አካሔድ መዘርጋት ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ድምጿን ከፍ አድርጋ ታሰማለች።

በመጨረሻ ከዚህ ቀደም በእስረኞች ላይ በሰፊው ይታዩ የነበሩ ሰብኣዊ ክብርን የሚነኩ፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች መቅረታቸው አንዱ መጠቀስ ያለበት አስመስጋኝ ለውጥ እንደሆነ ምስክርነት መስጠት ተገቢ ነው። ይሁንና አሁንም ቢሆን በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ እስረኞች ዘርፈ ብዙ ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ማረፊያ ቤት ሆነው የፍርድ ሒደታቸውን እያካሔዱ ያሉ ተጠርጣሪዎች አሁንም ቢሆን አፋጣኝ መፍትሔ የማግኘት መብቶች እምብዛም ሲከበር አይታይም። አሁንም የጊዜ ቀጠሮ በሚል ሰበብ እስረኞች ሲጉላ ማየት የተለመደ ነው። ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ለፍርድ ቤት ባላቀረቡበት ሁኔታ የተራዘመ የጊዜ ቀጠሮ በመሰጠቱ ብዙ እስረኞች እየተጉላሉ መሆኑ ይታወቃል።

በሕግ ሙያ እንደ መርህ ከሚጠቀሱት ወርቃማ አባባሎች መካከል በስፋት የሚጠቀሰው ‘የዘገየ ፍትሕ እንዳልተፈጸመ ይቆጠራል’ የሚለው ጎልቶ ይታወቃል።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20 የተከሰሱ ሰዎች መብት እንዲሁም አንቀጽ 21 በጥበቃ ሥር ያሉ በፍርድ ቤት የታሠሩ ሰዎች መብቶችን የሚዘረዝር ሲሆን፤ እንዲሁም ያለምንም መሸራረፍ ሥራ ላይ መዋል ይገባዋል ስትል አዲስ ማለዳ ታስባለች።

በአጠቃላይ ከላይ ለተዘረዘሩት ማሳያዎች የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ላይ መንግሥት ትኩረት በመስጠት መቀነስ ብሎም ማስቀረት ይገባዋል። በተለይ የጸረ ሽብርተኝነት ሕጉ አቧራው ተራግፎ በሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ እንደ ማጥቂያ መሣሪያ መጠቀም ተገቢ አይደለም ስትል አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። ሳይውል ሳያድርም ሕጉ ይሻሻል ወይም ይሰረዝ።

ሌላው በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴ መዳከም ከባድ የሆነ ክፍተት መፈጠሩ ግልጽ ነው። የተሻሻለውን የሲቪል ማኅበራት ሕግ በመጠቀም የነበሩ የሲቪል ማኅበራትም ሆኑ አዳዲሶቹ በተለይ ኅብረተሰቡን የማንቃት፣ መብቱን የመጠየቅ፣ የማክበር ሥራ እንዲሠራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክረው መቅረብ ይገባቸዋል። ያለ ጠንካራ ሲቪል ማኅበራት መብቱንና ኀላፊነቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ ዜጋ ለመፍጠር አዳጋች መሆኑ ይታወቃል። በሥራ ላይ ያሉ እንደዚህ ዓይነት ሕጎች በተግባር መሬት ላይ ወርደው መፈጸማቸው ዜጎች መብታቸውን እንዲያውቁ፣ ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ የማስቻል አቅም ሊገነባላቸው ይችላል።

ዴሞክራሲ ያለ ሲቪል ማኅበራት የነቃ ተሳትፎ መገንባት አዳጋች ብቻ ሳይሆን የማይቻል መሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም እነዚህ ማኅበረሰባዊ ተቋማት ጠንክረው መውጣት ይገባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች።

በመጨረሻም መገናኛ ብዙኀን ሚዛናዊ፣ በማስረጃ የተደገፈና አስተማማኝ ከሆኑ ምንጮች ያገኟቸውን ዜናዎች ሙያዊ ታማኝነቱን በተከተለ መልኩ ማቅረብ አለባቸው። ይሁንና ከዚህ በተቃራኒ በኢትዮጵያ አንዳንድ መገናኛ ብዙኀን አንድን ወገን ወግነው ሌላ ሌላውን ማጥቂያ ሆነው እየቀረቡ፣ የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ እየሆኑ ለመሆኑ በአንዳንድ ክልሎች ባለቤትነት የሚታወቁ መገናኛ ብዙኀን ጭምር ይህንን ነገር በማስፈጸም ይታወቃሉ። ይህም ሙያውን መናቅ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርን አለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን መዘዙ ከባድ ሲሆን የአገር ኅልውናንም ፈተና ላይ ሊጥል የሚችል መሆኑ መታወቅ ይገባዋል።

አዲስ ማለዳ መገናኛ ብዙኀን ኅብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት፣ ያለ አድሎና ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ማግኘት ይገባዋል ትላለች። በመረጃ የበለጸገ ማኅበረሰብ የሚወስደው እርምጃ በእውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያደርገዋልና ነው። በመሆኑ መገናኛ ብዙኀን የተቋቋሙላቸውን ዓላማ ለማሳካት፣ ግብ ለመምታት፣ ተልዕኮ ለመፈጸም መትጋት ይገባቸዋል። ከምንም በላይ መገናኛ ብዙኀን ሙያተኛነትን ማስቀደም ይገባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

መገናኛ ብዙኀን ኅብረተሰቡን በመረጃ የሚያበለጽጉ፣ ሚዛናዊና ሙያዊ ሥነ ምግባርን ያሟሉ የኅብረሰተሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ እንጂ የጥፋት ኀይል ሆነው ግጭት የሚያነሳሱ፣ የውሸት መረጃን የሚያሰራጩ መሆን አይገባቸውም። አለበለዚያ ለዜጎች ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ገፊ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

ከአገራት ተሞክሮ እንደምንረዳው መገናኛ ብዙኀንን ማኅበራዊ ትስስር አውታሮችን ጨምሮ ለበጎ በማዋል ዴሞክራሲ እንዲገነባ የሚያግዙ መሆን ይገባቸዋል። በ1994 (እ.አ.አ.) የተፈጸመው የሩዋንዳ እልቂት መገናኛ ብዙኀን ምን ያክል ለጥፋት ከዋሉ አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑ በተግባር የታየ አብነት ነውና፤ መገናኛ ብዙኀን ሕዝብን በመረጃ ማበልጸግ ሚዛናዊና ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተከተሉ መረጃዎች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ ያላትን አቋም በአጽንዖት ትገልጻለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com