ከሰባት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ‹‹የሰው ዘር መገኛ›› የተሰኘ አዲስ ሙዚየም ሊገነባ ነው

Views: 430

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የሰው ዘር ቅሪት አካሎች ለእይታ የሚቀርቡበት አዲስ ሙዚየም በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ኪሎ አካባቢ ሊያስገነባ ነው፡፡ በአውሮፓ ህብረት ሙሉ ድጋፍ ከ3 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የዲዛይን እና ተያያዥ ስራዎችን ማካሄድ የተጀመረ ሲሆን ጠቅላላ ወጪውም ከ7 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡

ሙዚየሙ ከ1 ዓመት በኋላ ግንባታው የሚጀመር ሲሆን፣ በውስጡም የሰው ዘር ቅሪት አካሎችን በመያዝ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ጎብኚዎችን ለመሳብ እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግም አኳያ ከፍተኛ የሆነ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ፋንታ በየነ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ መስርያ ቤቱ በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚካሄዱበት እንደመሆኑ መጠን ይህን አዲስ ሙዚየም ለመገንባት ማሰቡ ትልቅ ነገር ነው።

አዲስ የሚገነባውም ሙዚየም የሰው ዘር ቅሪተ አካላትን ጨምሮ የተለያዩ ቅርሶች ለእይታ ከሚቀርቡበበት ብሔራዊ ሙዚየም ተለይቶ የሚወጣ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያቋርጠው የምስራቅ አፍሪካ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ በርካታ የሰው ልጅ እና የእንስሳት ቅሪት አካላት የሚገኙበት አካባቢ ነው። በአካባቢውም ጥናትና ምርምር የሚያካሄዱ ባለሞያዎችም በርካታ ግኝቶችን በማግኘት ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደሆነች ያረጋገጡበት ሲሆን ግኝቶቹን ግን ከሳይንሳዊ ፋይዳቸው ባሻገር ለቱሪስት መስህብ ለመጠቀም ግን አስፈላጊው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ፋንታ ተናግረዋል።

‹‹የሰው ዘር መገኛ›› በሚል ስያሜ ይገነባል የተባለውን ይህን ሙዚየም ለመገንባት የሚወጣውን ወጪ መንግስት እንዲሁም በውጪና በሀገር ውስጥ ለጋሽ ድርጅቶች እና ተመራማሪዎች የሚደገፍ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ፊት ለፊት በ4 ሺህ 451 ካ.ሜ ቦታ ላይ ለሚገነባው ለዚህ ሙዚየም በአካባቢ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ነዋሪዎች የሚነሱ ሲሆን 9 ሚሊየን 166 ሺህ ብር የካሳ ክፍያ ተፈፅሞ መጠናቀቁንም አዲስ ማለዳ ለመረዳት ችላለች፡፡ በ2012 የበጀት አመት መጨረሻ ድረስም አጠቃላይ ነዋሪዎችን የማንሳት ስራ እንደሚጠናቅ ፋንታ ጨምረው ተናግረዋል።

በዓለም ላይ ከተገኙ 23 የቅድመ ሰው ዝርያዎች መካከል አስራ ሦስቱ በኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው። በአፋር ክልል እና በሌሎች የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ባሉት መካነ ቅርሶች የሚገኙ እስከ 6ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያስቆጠሩ የቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካላት ኢትዮጵያ የሰው ዘር ምንጭ ስለመሆኗ ያስረዳሉ፡፡

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሰፋ (ዶ/ር) እንዳሉትም አዲስ የሚገነባው የሰው ዘር መገኛ ሙዚየም ላይ ሰፊውን ድርሻ ይዘው የሚያንቀሳቀሱት ነባር የቅሪት አካል አጥኚዎች ናቸው። ሙዚየሙም በአብዛኛው የሰው ዘር ቅሪት አካልን የሚይዝ ሲሆን ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ርብርብ በማድረግ ከመጪው ጥቅምት 29 ጀምሮ ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ስራ ይጀመራል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረውም ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን እና ለሀገር መልካም ገፅታ ግንባታም ቀላል የማይባል ሚና እንደሚኖረው ገልፀው፤ መንግሥት የቱሪዝም መዋቅሩን በማስተካከል ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ መሥራት እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም ከ75 ዓመታት በፊት በአፄ ኀይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተቋቋመ ሲሆን፤ በወቅቱ ቅርስ በማሰባሰብና ለዕይታ በማቅረብ “ቤተመዛግብት ወመዘክር” (የአሁኑ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ድርጅት) ተብሎ አገልግሎት ይሰጥ ነበር። በኋላ ቅርስ ስብስቡ እየጨመረና ጥናቶች እያደጉ ሲሔዱ በሒደት ሙዝየሙ ብቻውን ሲወጣ በዘገምተኛ ሒደት የአሁኑ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ተቋቁሟል። እስከአሁን ድረስ የሙዝየምነት እውቅና ሳይኖረው ቢቆይም፤ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ያገለግል የነበረው ብሔራዊ ሙዚየሙ ከ1985 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በነበሩ ዓመታት በ1 ሚሊዮን 933 ሺሕ 662 የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኚዎችን እንዳስተናገደ መረጃዎች ያመለክታሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com