ውዝግብ ያልተለየው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ ሕግ

Views: 375

አዲሱ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ነሃሴ 18/2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ ከ50 የማያንሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በተለይ የፓርቲዎች መመስረቻ ሕጉን ክፉኛ ሲቃወሙት ይደመጣል። “ሰሚ አላገኘንም እንጂ ፓርላማው እንዳያፀድቀው ቀድመን አቤት ብለን ነበር” ሲሉም በተደጋጋሚ ወቀሳ አቅርበዋል። የምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ በረቂቅ ሕጉ ላይ ከፓርቲዎች ጋር በቂ ውይይት መደረጉንና ያቀረቡት የማሻሻያ ሐሳቦች ሁሉም ባይሆኑም መካተታቸውን ይገልጻል። “ብዙ ፓርቲዎች እንደገና ስለተከለሰው የሕግ ክፍሉ አይናገሩም፤ ሁሉም አቤቱታቸው በፓርቲዎች ምዝገባ ጉዳይ ላይ ነው” የሚሉት የምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ፤ ክርክሩ ግን ለዲሞክራሲ ሒደቱ ጠቃሚ ነው ባይ ናቸው።

ቦርዱ ገና ብዙ ፈታኝ ሥራዎችና ውዝግቦች ይጠብቁታል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኞች፣ ከመጪው አገራዊ ምርጫ በፊት የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸምና የ2012ቱን አገራዊ ምርጫ ማስፈጸም ይጠበቅበታል። የፓርቲዎች የእርስበርስ ውዝግቦችንና ንትርኮችን መፍታት ሌላው የቦርዱ የቤት ሥራ ነው።

ሕጉ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሙሳ አደም፣ አዋጁ 50 ከመቶ ችግር ያለበት መሆኑን ይናገራሉ። አሁን ክርክር ከሚነሳባቸው የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ በእጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ፣ የምርጫ ሒደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደሞዝና ጥቅማ ጥቅማቸውም እንደማይከበር በሚዘረዝረው ረቂቅ ሕግ አንቀጽ 33፣ እንዲሁም አገር ዐቀፍ ፓርቲ ለመመስረት 10 ሺሕ፣ የክልል ደግሞ 4 ሺሕ መመስረቻ ፊርማ ያስፈልጋል ከሚለው በተጨማሪ የአካል ጉዳተኞችን፣ የሴቶች፣ የአርብቶ አደሩን በሚመለከት ዝርዝር ጉዳይ የሌለው ከመሆኑም ባለፈ የበጀት አበጃጀቱም ላይ መሰረታዊ ችግሮች ይስተዋሉበታል ብለዋል።

ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ሕግ ሊያስማማ አይችልም ያሉት ሶልያና፣ “ ከ130 በላይ ፓርቲዎች ናቸው ያሉት። ከእነዚህ ምን ያህሉ ሕጉን አንብበዋል የሚለው በራሱ መታየት አለበት። የትኞቹ ፓርቲዎችስ ናቸው አንቀጾቹን በትክክል አንብበው ጠቃሚ የሆኑትን የለዩት፤ የሚለውም ሌላው ጉዳይ” ሲሉ ያስረዳሉ። በድፍኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ስለሰጡ፣ ሕጉ ተቀባይነት አላገኘም፤ የሚል ድምዳሜ ላይ እንዳንደርስ መጠንቀቅ አለብን ሲሉም ያሳስባሉ።

እንደ ሶሊያና ገለጻ፣ አጨቃጫቂ የሚባሉት 10 ሺሕ የምስረታ ደጋፊ ፊርማና የመንግሥት ሠራተኛን አስመልክቶ የወጡት የሕግ አንቀጾች ናቸው። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በቂ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል። 10 ሺሕ ፊርማ የማሰባሰብ ዋና ዓላማው፣ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ነው። መራጩ ሕዝብ፣ በግልጽ የሚታይ፣ ጠንካራ የፖለቲካ አማራጭ እንዲኖረው ለማድረግ ነው።

የመላው ኢትዮጵያ አንድንት ድርጅት (መኢአድ) ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሙሉጌታ ጌታቸው በሶልያና ሐሳብ አይስማሙም። ለምሳሌ መኢአድ 10 ሺሕ ፊርማ በሚለው ላይ ተቃውሞ የለውም የሚሉት ሙሉጌታ፣ የአዋጁ 20 አንቀፆች እንዲሠረዙና 15 ያህሉ ደግሞ እንዲሻሻሉ 33 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠይቀን፣ ረቂቅ አዋጁ ላይ ምክክር በተደረገበት ወቅት ማሻሻያ ሐሳቦችን በጽሑፍ አቅርቡ ተብሎ አቅርበናል፤ ነገር ግን ቦርዱ የማሻሻያ ሐሳባችንን ሳያካትት እንዲፀድቅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመላኩ ፓርቲዎቹ ያቀረብናቸው የማሻሻያ ሐሳቦች ባለመካተታቸው አዋጁ የእኛን ሐሳብ ያገለለ በመሆኑ መጽደቅ የለበትም ነው ያልነው ብለዋል።

እንደ ሙሉጌታ ገለጻ፣ በዋናነት ፓርቲዎቹ ቅሬታ ያቀረቡባቸው አንቀፆችም ለፓርቲዎች ምዝገባ መመዘኛነትና ለእጩ ተወዳዳሪዎች የቀረበውን መስፈርት ናቸው፤ እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ በረቂቅ ሕጉ የቀረቡ መስፈርቶች የምርጫውን አሸናፊ አስቀድሞ የሚበይን በመሆኑ አገሪቱን ወዳልተፈለገ የፖለቲካ ውዝግብ የሚወስድ ሕግ ነው ብለዋል። ፓርቲዎቹ እንዲሰረዙ አቤቱታ ካቀረቡባቸው የአዋጁ አንቀፆች መካከልም ከ5 ሺሕ ብር በላይ እርዳታ የሰጠ ደጋፊ ሥሙ እንዲገለጽ የሚያስገድደው አንቀጽ ተጠቃሽ ሲሆን፣ ይህም ደጋፊን የሚያሸማቅቅ ስለሆነ ነው የምንቃወመው ብለዋል።

የአባላት ዝርዝርና አድራሻ በግልጽ መታወቅ አለበት እንዲሁም አንድ የፓርቲ አባል የሆነ እጩ ተወዳዳሪ፣ በሚወዳደርበት አካባቢ ሦስት ሺሕ ድምጽ አስቀድሞ ማሰባሰብ አለበት የሚሉት አንቀፆችም ፓርቲዎቹ እንዲሠረዙ ከጠቀሷቸው መካከል ይገኙበታል።

የፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ሊያመጣ የሚችለው ተጽዕኖ በቀላሉ መታየት እንደሌለበት የሚያወሱት ሙሉጌታ፣ ሕጉን ባለማሻሻል ከሚመጣው ተጽዕኖ ይልቅ አሻሽሎ የሚያመጣውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማጣጣም የተሻለ ነው ብለዋል። እኛ ያልነው ብቻ ካልሆነ አላልንም የሚሉት ሙሉጌታ፣ ሁላችንንም ያስማማ ሕግ ይውጣ ነው ያልነው ብለዋል።

ሙሳ፣ የፓርቲዎቹን ጥያቄ በኹለት መንገድ መመልከት ተገቢ ነው ይላሉ። ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ረቂቅ ሕጉን ሲቃወሙ ተቃውሞውን ከሚያሰሙት መካከል አብዛኞቹ፣ የፓርቲያቸው ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የተገነዘቡት መሆናቸውን አስታውቀው፣ ሌሎቹ ደግሞ መስፈርቱን ጠብቀው የተደራጁ ሆነው እነሱ የሚወዳደሩበት ክልል ውስጥ የሚገኘው ገዢ ፓርቲ፣ አባላት ለመመልመል አይደለም በክልሉ ገብተው በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ፈተና ስለሆነባቸው የደኅንነት ሥጋት አለብን የሚለው ነው። ምርጫ ቦርድ ሁኔታዎቹን በዚህ መንገድ ማየት እንዳለበትም ያሳስባሉ። እኛ ብቻ ያልነው የሚል ሳይሆን ሁሉንም ያስማማ ሲሆን የተሻለ ይሆናል በማለት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ቅጽ 1 (40) ነሐሴ 4/ 2011 በወጣው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ላይ እንደገለጹት፣ በየትኛውም ዓለም በፖለቲካ ውስጥ ልዩነት አለ ይላሉ። በኢትዮጵያ እኛ ያልነው ካልሆነ የሚለው ብሒል ተደጋግሞ ይሰማል የሚሉት መምህሩ፣ ከሌላ አገር ተሞክሮ ተወስዶበት፣ ራሳቸው ፓርቲዎቹ መክረውበት የተወሰነውን ውሳኔ አልቀበልም ብሎ ማለት ውሃ የማያነሳ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ማንኛውም ሕግ ሲወጣ ሁሉንም ሊያስደስት እንደማይችል ያወሱት ዮናስ፣ አብላጫውን ካስማማ ተግባራዊ ይሆናል ሲሉ አክለዋል።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሊቀመንበር አብዱል ቃድር አደም (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ ከሚሆንባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው ምርጫ ነው። የምርጫ ሥርዓቱንና የአመራረጥ ሁኔታውም ቢሆን እነዚህን መብቶች ለመተግበርና በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ የራሳቸው ተፅዕኖ ሊኖራቸው መቻሉ አያጠራጥርም። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 እንደተገለጸው ሥልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ ነው። የምርጫ መርሆችን በተመለከተ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 38 ላይ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ፣ ሁሉን ዐቀፍ፣ ሚስጢራዊ መሆን፣ በየጊዜው መካሔድ እንዳለበት አስቀምጧል። የምርጫ ሥርዓቱን ደግሞ አንደኛ-አላፊ የሚባለውን ሥርዓት (First-Past-The-Post) እንዲከተል በሕገ መንግሥት ተወስኗል።

የጸደቀን ሕግ ማሻሻል ይቻላል?
ሙሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ምርጫ ቦርድ ፈቃደኛ ከሆነ ሕጉን ርዕሰ ብሔሯ እስካልፈረሙበትና በነጋሪት ጋዜጣ እስካልወጣ ድረስ ማሻሻል ይቻላል ባይ ናቸው። እንኳን የምርጫ አዋጅ ሕገ መንግሥትም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የማይሻሻልበት ምክንያት እንደማይኖር ያወሳሉ። እንኳን የምርጫ አዋጅ ሕገ መንግሥትም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የማይሻሻልበት ምክንያት እንደማይኖርም ይናገራሉ።

ሕጉ የተዘጋጀው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር ባለ የዴሞክራሲ ጉዳዮችን የሚመለከት የሥራ ቡድን መሆኑን ያስታወቁት ሶልያና፣ “ከዚያ ውጪ ባለድርሻ ከሆነው የምርጫ ቦርድም የዚህ ቡድን አባላት አሉ፤ በጋራ ነው የተሠራው። እኔ ለምሳሌ እዚህ ከመቀጠሬ በፊት የዚያ ቡድን አባል ነበርኩ። ያ የሥራ ቡድን ነው ሕጉን ያረቀቀው። ሕጉ ከመረቀቁ በፊት የቀድሞው ሕግ የነበሩበት ክፍተቶች ምንድን ናቸው? የሚለው ጥናት ተደርጎበታል” ሲሉ ይገልጻሉ።

እንደ አማካሪዋ ምላሽ፣ በዚያ ጥናት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕግ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ከእነሱ በተገኘው ግብዓት መሰረት፣ ውይይቶች ተደርገው፣ ከፓርቲዎችም ከሕግ ባለሙያዎችም ግብዓቶች ተወስደዋል። ከፓርቲዎች ግብዓት ይወሰዳል ማለት እነሱ ያሉት በሙሉ ይካተታል ማለት ግን አይደለም። ገዥው ፓርቲም ተቃዋሚዎችም ግብዓት ይሰጣሉ። ከዓለማቀፍ ልምዶች የሚገኙ ግብዓቶችም ተካተው ነው ሕጉ የሚዘጋጀው። ገለልተኝነት ሲባል ደግሞ ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚዎችም ገለልተኛ መሆን ያስፈልጋል። አርቃቂው ቡድን ሁሉንም ግብዓቶች መዝኖ ነው ሕጉን ያዘጋጀው።

ሶሊያና እንደሚሉት፣ የመንግሥት ሠራተኛን በተመለከተ ከፓርላማ ሪፖርት እንደተረዱት፤ በረቂቁ ተካቶ የነበረው ሙሉ ለሙሉ ከሕጉ ተወግዷል። ይኼን ሕግ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ኢሕአዴግ ስላልወደዱት፣ በሁሉም ስምምነት የቀረ ድንጋጌ ነው። ስለዚህ ሕጉን የማሻሻሉ ፋይዳው የሚታይ አይደለም።

ረቂቅ ሕጉ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከተስማሙበት ውጪ የቀረበ በመሆኑ፣ ከቦርዱ ጋር እንደገና መምከር አለብን የሚል ነው ጥያቄያችን የነበረው የሚሉት የመኢአድ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሙሉጌታ፣ የሕጉ ይዘት የዜጎችን የመደራጀት፣ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት የሚገድብ በመሆኑ ከመጽደቁ በፊት ተመልሶ ለውይይት መቅረብ አለበት ብለን ስንሞግት ነበር ብለዋል።

ብዙ ፓርቲዎች እንደገና ስለተከለሰው የሕጉ ክፍል እንደማይናገሩ ያወሱት ሶሊያና፣ ሁሉም አቤቱታቸው በፓርቲዎች ምዝገባ ጉዳይ ነው። ሕጉ ውስጥ የተቀየረውንና የተሻሻለውን ነገር ማየት እንደማይፈልጉ ይገልጻሉ። 10 ሺሕ ፊርማ የሚለውን ብቻ ነው የሚያነሱት። ያንንም አስመልክቶ ጥቅምት ላይ ፊርማ የማሰባሰብ መርሃ ግብር ይዘዋል፤ በዛ ጊዜያቸው ዐሥር ሺውን ፊርማ ለምን አያሰባስቡም ሲሉ ይጠይቃሉ። እኛ ይኼንን በጣም ዝቅተኛ መስፈርት ነው ብለን ነው የምናምነው። በሌላ በኩል፤ በርካታ የቀረቡ የማሻሻያ ሐሳቦች በሕጉ ተካተዋል። ይኼን ግን ፓርቲዎቹ አይጠቅሱም። ሁሉም የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። በርካታ ሐሳቦቻቸውም ተቀባይነት አግኝቶ በሕጉ ተካቷል። እነሱ የሚያነሱት ግን አንድ ኹለት ጉዳዮችን ነው በማለት አክለዋል።

የውዝግቡ ተጽዕኖ እስከምን ድረስ ነው? መፍትሄውስ?
በፓርቲዎች መካከል በሚፈጠሩ ውዝግቦችና አቤቱታዎች ብዙ ጊዜያችንን እየበሉብን ነው ያሉት ሶሊያና፣ የቦርዱን የፖለቲካ ፓርቲ ዲፓርትመንት ሥራ በእጅጉ መፈታተኑን አስታውሰው፣ በጣም በርካታ የማይታወቁ ፓርቲዎችም በአመራር ውዝግብ አቤቱታ ያቀርባሉ ብለዋል። ይኼ ደግሞ ቦርዱ ሌሎች ሥራዎችን እንዳይሠራ ማነቆ ሆኖበታል ብለዋል። ሌሎቹ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው በማለት።

ጭቅጭቁን በበጐ እንደሚወስዱት የገለጹት ሶሊያና፣ ፖለቲካ ሁሌም ክርክር እንዳለው አንስተው፣ የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ ጥረት የሚደረግበት እንደመሆኑ ጉዳዮቹ በራሳቸው አነጋጋሪ ናቸው ብለዋል። ክርክሩ መኖሩ የባለድርሻዎቹን የነቃ ተሳትፎ አመላካች መሆኑን የጠቆሙት አማካሪዋ፣ ክርክሩም ለዲሞክራሲ ሒደቱ ጠቃሚ ነው ብለን ነው የምናምነው ብለዋል። ሕዝቡ ከዚህ ክርክር የሚወስደው የራሱ ነገር እንደሚኖረው በማውሳት።

ሶሊያና እንዳስታወቁት፣ ሌላው በሕጉ የተቀመጠ የግልግል ዳኝነትን ለመጠቀም የሚያስችል ሕግ ተካትቷል። አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየጊዜው የሚቀርቡ አቤቱታዎችን የሚመለከትና የሚያስማማ ወይም የግልግል ዳኝነት የሚሰጥ ይሆናል። ሕጉ ላይ ያለውን ነገር ከፓርቲዎች ጋር ተወያይቶ፣ እንዴት ውዝግቦችን መፍታት ይቻላል ለሚለው፣ አንድ መፍትሔ ያስገኛል።

ዮናስ በየትኛውም ዓለም በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ የማይቋረጡ ጥያቄዎች አሉ። ሁሉም መልስ ያገኛሉ ማለት ግን አይደለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አድገዋል በሚባሉ አገሮች እንኳን በፓርቲዎች መካከል ውዝግቦች አሉ። አንዱ የሠራውን ሌላኛው ስህተት ፈልጎ ሲወቅስ ይስተዋላል። ያንን ግን እንደ ዴሞክራሲያዊ መገለጫ ነው የሚታየው እንጂ እንደጥቃት አይወሰድም። እኛም ጋር በዚህ መንገድ ነው መታየት ያለበት። ክርክሩን ለዲሞክራሲ ሒደቱ መገለጫ ማድረጉ ነው የተሻለ የሚሆነው ሲሉ ይመክራሉ።

ሙሳ በበኩላቸው፣ የፓርቲዎችን ጥያቄ እንደስጋት ሳይሆን እንደግብዓት መጠቀሙ ለቦርዱም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጠቃሚ መሆኑን አንስተው፣ ሁሉንም ነግር በእልህ ከማድረግ በውይይት መፍታት የተሻለ መሆኑን ይገልጻሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com