መቀመቅ ቁፋሮ በማን እና ለማን ነው?

Views: 344

ግዛቸው አበበ ሰሞኑን መተማ-ሱዳን መንገድ መዘጋቱ እና በአካባቢው (በጭልጋ) ለቀናት ጦርነት አከል ግጭት መኖሩን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን መዘገቡን በማስታወስ ከሰሊጥ ምርትና ወጪ ንግድ እንዲሁም ከቅማምት ማኅበረሰብ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ግጭት አንድምታ በመጣጥፋቸው አመላክተዋል። የፌደራል መንግሥቱ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ መግባት ይገባዋልም ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ ቪኦኤ የአማርኛው ፕሮግራም፣ በየዕለቱ ከምሽቱ ሦስት እስከ አራት ሰዓት በሚያሰራጨው ፕሮግራሙ መጠናቀቂያ ላይ የብዙዎችን ትኩረት የማይስብ፣ ነገር ግን ስለ ሰሊጥ ሰብል ስብሰባ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎችን ሊያስደነግጥ የሚችል አንድ ዜና አሰማ። ዜናው በመተማ በአካባቢው የሚገኙ ሰሊጥ አምራች ገበሬዎች በተፈለገው መጠን የጉልበት ሠራተኞች ማግኘት አለመቻላቸውን የሚያትት ሲሆን በዚህ ዜና ትኩረት የተሰጠው በተፈጠረው የሰው ኀይል እጥረት ለቀን ሠራተኞቹ የሚከፈለው የቀን ዋጋ በጣም ከፍተኛ የመሆኑ ጉዳይ ነበረ። ዜናው የቀን ሠራተኞች ወደ ቦታው ለምን እንዳልሔዱ ብዙም ትኩረት ያልሰጠ መሆኑ አስገራሚው ነገር ነበረ። የአካባቢውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያውቅና ወቅቱ ለአካባቢው ሰሊጥ አምራች ገበሬዎች የምጥ ወቅት መሆኑን የሚያውቅ ሰው ከዚህ ዜና በመነሳት ብዙ ነገር ሊገምት ይችላል።

ሰሊጥ የሰው ልጅ ከዱር ተክልነት አውጥቶ ካላመዳቸው የመጀመሪያወቹ ተክሎች አንዱ ነው። የሰው ልጅ ሰሊጥን የግብርና ተክል ካደረገ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ መቆጠራቸውን መዛግብት ያሳያሉ። ሰሊጥ በልዩ ጣዕሙ፣ በዘርፈ ብዙ አገልግሎቱና በከፍተኛ የዘይት ይዘቱ ተመራጭ የዘይት ተክል ለመሆን የበቃ ነው። እያንዳንዷ የሰሊጥ ፍሬ ከ55-60 በመቶ የዘይት እና 24 በመቶ የፕሮቶቲን ይዘት አላት። እነዚህ የሰሊጥ ባሕሪትና ይዘቶች ሰሊጥን በዓለም ደረጃ በጣም ተፈላጊ ተክል አድርገውታል። አገራችን ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው የግብርና ምርቶች አንዱ ሰሊጥ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። አገራችን በአብዛኛው የሰሊጥ ምርት የምታገኘው በቆላማ የምዕራብ ጠረፋማ አካባቢዎች ሲሆን በመተማ፣ በሑመራና በወለጋ ዙሪያ የሚገኙ ሰፋፊ እርሻዎች ዋነኞቹ የሰሊጥ ምርት የሚገኝባቸው ቦታዎች ናቸው።

ማንኛውም አዝመራ ጊዜውን ጠብቆ መዘራቱ፣ በጊዜው መታረሙና በወቅቱ መታጨዱ ለምርታማነቱ ወሳኝ መሆኑ ቢታወቅም፣ የእነዚህ የእርሻ ሥራዎች መስተጓጎል ብቻ ሳይሆን በጥቂቱ መዛነፍ የሰሊጥን ያህል በከፍተኛ ደረጃ ለምርት ማሽቆልቆል የሚዳረግ ሰብል የለም ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ የሰሊጥ ሰብል የአጨዳ ጊዜ መስተጓጎል ባዶ እጅን የሚያስቀር ችግር ማስከተሉ ተፈጥሯዊ ሃቅ ነው። የሰሊጥ ሰብል ለአጨዳ የመድረስ አዝማሚያ ሲያሳይ ከ4 እስከ 10 ባልበለጡ ቀናት ውስጥ መታጨድ ይገባዋል። ከ50 ሳንቲ ሜትር እስከ 1 ነጥብ 5 ሜትር ቁመት ያለውን አገዳውን በጣም ዝቅ ብሎ ማጨድ፣ የታጨዱትን የሰሊጥ ተክሎች እንደ ችቦ በማሰር ችቦዎቹን እርስ በርሳው እንዲደጋገፉ በማድረግ ማቆም የሰሊጥ ምርቱን በተገቢው መጠን ለመሰብሰብ የሚረዱ ሥራዎች ናቸው። የሰሊጥ ተክል ፍሬውን የአተርን በመሰሉና እስከ 4 ሳንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት ባላቸው ከረጢቶች አጭቆ የሚይዝ ሲሆን፣ የሰሊጥ አጨዳው መካሔድ ያለበት እነዚህ ከረጢቶች መከፈት (መፈንዳት) ሳይጀምሩ ነው። የሰሊጥ ከረጢቶች ባልታጨደ የሰሊጥ ተክል ላይ ከቆዩ የፍንዳታ ድምጽ እያሰሙ በኀይል ተከፍተው በውስጣቸው የያዙትን ሰሊጥ የበትኑታል። ይህ ተፈጥሯዊ ክስተት ሰሊጥ ራሱን የሚያራባበት ሒደት ነው። ሰሊጥ ጊዜውን ጠብቆ ታጨደ የሚባለው ቅጠሎቹ መርገፍ ጀምረው ከረጢቶቹ ቀለማቸው መወየብ ሲጀምር ነው። በጊዜው የታጨዱ የሰሊጥ ተክል ከረጢቶች በቁማቸው (ቀና ብለው) በተቀመጡ ችቦዎች ላይ እንዳሉ ቀስ በቀስ መከፈት ይጀምራሉ፤ ሁሉም ከረጢቶች የሚከፈቱበትን ጊዜ ጠብቆ በሰፊው በተዘረጋ የአቡጀዴ ጨርቅ ወይም በደንብ ተለስኖ በተዘጋጀ ሰፊ ውድማ ላይ ላይ ችቦዎቹን ቁልቅል ዘቅዝቆ በመወዘወዝ (በመንገፍ) የሰሊጥ ፍሬዎች ከየከረጢቱ ተራግፈው እንዲወጡ ማድረግና ተራግፎ የተከመውን ሰሊጥ ወደ ጆንያ እየጨመሩ ምርቱን መከመር ወሳኙ ሥራ ነው።

ሰሊጥ የአጨዳ ጊዜው ደርሶ ሳይታጨድ ከቀረ፣ ከረጢቶቹ በኀይል እየፈነዱ ሰሊጣቸውን ስለሚበትኑት ገበሬው ባዶ እጁን ይቀራል። ይህ የከረጢቶች መፈንዳትና የምርት መባከን የግብርና ተመራማሪወች በዓለም ዙሪያ መፍትሔ ሊያገኙለት ደፋ ቀና የሚሉበት አሳሳቢ ችግር ነው። በከረጢቶች መፈንዳት የሰሊጥ ምርት የመባከኑ ጉዳይ አሜሪካን የመሳሰሉ የበለጸጉ አገራትን ጭምር በማሳሰብ ላይ ያለ ምርት አባካኝ ችግር ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት ቪኦኤ ላይ የተሰማው በመተማ-ጭልጋ አካባቢ ሰሊጥ አምራች ገበሬዎች በቂ የጉልበት ሠራተኞች ማግኘት አልቻሉም የሚለው አቤቱታ፣ ሰበር ዜና ለመሆን የበቃው የአካባቢው ሰሊጥ አምራች ገበሬዎች ጭንቀት አድሮባቸው ለዜና ምንጩ እንዲደርስ ስላደረጉ ሊሆን ይችላል። ከ50 እና ከ60 ዓመታት በፊት ጀምሮ፣ በመተማና በሁመራ አካባቢዎች ሰፋፊ የሰሊጥ እርሻ ሥራዎች ከተጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ከጎንደር፣ ከጎጃም፣ ከወሎ፣ ከትግራይና ከኤርትራ እንዲሁም ከሱዳን ከዐሥር ሺሕዎች እስከ መቶ ሺሕ ገበሬወችና የቀን ሠራኞች ይህን የሰሊጥ አጨዳ ወቅት ጠብቀው ለ10 እና 20 ቀናት ወደ ቦታው የሚሔዱ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ወቅት ገበሬዎቹና የቀን ሠራተኞቹ በሰሊጥ አጨዳ ሥራ ላይ ተሰማርተው ገንዘብ ይዘው ወደ መኖሪያ አካባቢወቻቸው እንደሚመለሱ ጊዜ መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው።

በዚህ የሰሊጥ አጨዳ ወቅት ሰፋፊ እርሻ ያላቸው ሚሊዮነር ገበሬዎች ሳይቀሩ በዚያው በእርሻው ቦታ በተቀለሰ ጎጆ ወይም በተተከለ ጊዜያዊ ድንኳን ውስጥ ሆነው ቀንና ለሊት ሥራውን የሚከታተሉበት ወቅት ነው። የአጨዳው ሥራ በወቅቱና በአግባቡ አልተከናወነም ማለት በእርሻ ሥራው ላይ የፈሰሰው ገንዘብ በሙሉ ከስሮ ቀረ ማለት ነውና ይህን ወቅት ከባድ ምጥ ላይ ያለች እናትና ባለቤቷ ከሚገቡበት ሁኔታ ጋር ማነጻጸር ይቻል ይሆናል። በዚህ የምጥ ወቅት ተገቢው ሥራ ካልተሠራ የእናትንና የሕጻን ልጇን ሕይወት ሊያሳጣ የሚችል ስህተት እንደሚከሰተው ሁሉ በሰሊጥ አጨዳ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችም ሀብትን አሳጥተው ድካምን ሁሉ መና ሊያስቀሩ ይችላሉ።

የቪኦኤውን ዜና ተከትሎ ብዙ አስደንጋጭ ወሬዎች በተከታታይ ተደምጠዋል። የመተማ-ሱዳን መንገድ መዘጋቱ፣ በአካባቢው ግጭት መኖሩ፣ ወደ አካበቢው ሕዝብ ጭነው የሚጓዙ ተሸከርከሪወች ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑና ታጣቂዎች መኪኖችን አስቁመው መንገደኞች በመታወቂያቸው እየለዩ የገደሉበት አጋጣሚ መኖሩ ጭምር ተወራ። ለረዥም ጊዜ ዝምታን መርጠው የነበሩ የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኀን በመተማና በአካባቢው (በጭልጋ) ለቀናት ጦርነት አከል ግጭት መኖሩን፣ የመተማ ሱዳን መንገድን ጨምሮ ብዙ መንገዶች መዘጋጋታቸውን አመኑ። ቀስ በቀስ ዜናው የቅማንት ታጣቂዎችን ተጠያቂ ከማድረግ ጅምሮ እነዚህ ታጣቂዎች አልሞ ተኳሽ መሳሪያ፣ መትረየስና አካባቢውን የሚጠብቀው የክልሉ ታጣቂ ኀይል ካነገበው የተሻሉ ሌሎች የጦር መሳሪያወችን ታጥቀው መሰማራታቸውን የሚገልጽ ሆነ። ቪኦኤ የመጀመሪያውን ዜና ካሰማ በሳምንቱ፣ ማለትም መስከርም 19/2012 ማታ አንድ የአማራ ክልል የደኅንነት ባለ ሥልጣንን አቅርቦ ታጣቂዎቹ በሕወሐት (ትሕነግ) ሰልጥነው የተላኩ መሆናቸውን አሰምቶናል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የሆኑት አበረ አዳሙም ኢሳት ላይ ቀርበው ተመሳሳዩን ነገር ተናገረዋል። ሕወሓት አሰልጥኖና አስታጥቆ የላካቸው ኀይሎች አካባቢውን ወደ ጦርነት ቀጠና ቀይረውታል ብለዋል። የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኀላፊ የሆኑት አገኘሁ እንግዳም ማዕከላዊ ጎንደርን በተይም ጭልጋ ወረዳን የጦርነት ዓውድማ ለማድረግ የሚሠሩ ጸረ ለውጥ ኀይሎች መኖራቸውን ግልጸው እነዚህ ጸረ ለውጥ ኀይሎች ለቅማንት ጽንፈኞችን በማሰልጠን፣ ገንዘብና የጦር መሳሪያም በማቀበል ችግሩን እንዲፈጠር እያደረጉ መሆኑን አሳውቀዋል።

አገኘሁ ጥቃቱ እየደረሰ ያለው በፀጥታ ኀይሉና ትራንስፖርት እየተጠቀሙ ባሉ ንጹኃን ዜጎች ላይ መሆኑን ገልጸው ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ጥረት እያረገ እንደሆነ፣ ችግር እያደረሱ ያሉትን አካላት ከማኅበረሰቡ በመነጠል የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ፣ የፌደራሉ መንግሥትም በጉዳዩ እጁን እያስገባና የክልሉ ልዩ ኀይል አካባቢውን ለማረጋጋት መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ በአካባቢው እንዲቆይ መወሰኑን አሳውቀዋል።

በ2010 የመተማና የአካባቢው ሰሊጥ አምራች ገበሬዎች በምርት ሒደቱ ላይ ምንም ዓይነት ችግር ያልገጠማቸው ቢሆንም ምርቱ ለገበያ ይቀርብ ዘንድ ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዝ ግን በመንገድ ላይ ብዙ አስደንጋጭ ፈተናዎች ያጋጥሙ እንደነበረ የአካባቢው ሕዝብ እና ባለሥልጣናት የማይረሱት ጉዳይ ነው። ሰሊጥ የጫኑ ከባድ መኪኖች እየታገቱና ወደ ጫካ ገብተው እንዲሰወሩ እየተደረገ፣ የሰሊጡና የመኪኖቹ ባለቤቶች ከ300 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ ብር የሚደርስ ማስለቀቂያ ካልከፈሉ መኪኖቹ ከነጭነታቸው (ከነሰሊጡ) በእሳት እንደሚወድም የስልክ ማስጠንቀቂያ ይደርሳው እንደነበረ ይታወሳል። በድርድር እስከ 120 ሺሕ እና 200 ሺሕ ብር ከፍለው ንብረታውን ከእገታ ነጻ ያደረጉ ባለሀብቶችም ነበሩ።

በዚህ ዓመት ደግሞ ችግሩ የሰሊጥ አጨዳውን ጊዜ ጠብቆ ተከስቷል። ችግሩ ተከሰተው የሱዳንን መንገድ ለመዝጋት ነው፣ የቅማንት የማንነት ጥያቄ አራማጅ የሆኑ አክራሪዎች ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት የቀሰቀሱት ኹከት ነው፣ ፋኖዎች በአማራ ክልል ልዩ ኀይል ታግዘው በቅማንት ሕዝብ ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው የሚሉ ወገኖች በራቸውን በከፈቱላቸው ሚዲያዎች ላይ ሁሉ እየተወዛገቡ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የአማራና የትግራይ ባለሥልጣናት እየተፋጠጡበት፣ የአማራና የትግራይ አክቲቪስቶች እየተነታረኩበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው።

ያም ሆነ ይህ ይህን ደም አፋሳሽና ንብረት አውዳሚ ትርምስ ያስከተለው እውነተኛው ምክንያት ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የፌደራል መንግሥት በጉዳዩ ውስጥ መግባት ይኖርበታል። የሱዳን ኢትዮጵያን መንገድ ለመዝጋት ወይስ ለቅማንት የማንነት ጥያቄ መልስ ለመፈለግ ወይስ የሰሊጥ ምርቱ ባክኖ እንዲቀር አጭሩን የአጨዳ ወቅት ያለ ሥራ እንዲያልፍ ለማድረግ? ችግሩ የተፈጠረው ሰሊጡ ባክኖ እንዲቀር ታስቦበት ከሆነ፤ አክሳሪው መቀመቅ የሚቆፈረው ለማን እና በማን ነው? አክሳሪው ሴራ የተነጣጠረው በማን ላይ ነው? በአማራ ክልል ሰሊጥ አምራች ገበሬዎች ላይ ወይስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር በሚያገላታት በኢትዮጵያችን ላይ?
ግዛቸው አበበ መምህር ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com