የጤፍ ቢራ በአሜሪካ ተመረተ ሰኞ ለገበያ ይቀርባል

Views: 781

በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለቤትነት በአሜሪካን አገር የተቋቋመው ንጉስ ቢራ ኩባንያ በአሜሪካ ከተመረተ ጤፍ የተዘጋጀ ቢራ ለገበያ አቀረበ። ሰኞ መስከረም 19 ለሚጀምረው ስርጭት 19 ሺህ 200 ጠርሙስ የጤፍ ቢራ የተዘጋጀ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከቢራ ጠማቂው ኩባንያው ቺፍ ፋይናስ ኦፊሰር (CFO) መኩሪያ ንጉሴ ሰማች። ኩባንያው ቢራ በሚጠምቅበት ቦታ ለተጠቃሚ ምርቱ በትኩሱ ለተጠቃሚ የሚቀርብበት የመዝናኛ ማዕከል (brew pub)ና የሙዚቃ ኮንሰርት አዳራሽ ከፋብሪካው ጀርባ የመገንባት እቅድ እንዳለውም ገልፀዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት የተመሰረተው ንጉስ ቢራ ኩባንያ ካሁን በፊት ንጉስ ፕሬሚየም ክራፍት ላጋር የተባለ በአነስተኛ ፋብሪካ የተጠመቀ ቢራ (craft beer) በቨርጂኒያ ግዛት ማናሳስ ከተማ በማምረት በዋሺንግተን ዲሲ፣ ቨርጂንያ፣ ኒው ዮርክ፣ ኖርዝ ካሮላይናና ሌሎችም ኢትዮጵያውያንና ጥቁር አሜሪካውያን በስፋት በሚኖሩባቸው የአሜሪካን ግዛቶች ምርቱን ለገበያ ሲያቀርብ እንደነበር ኩባንያው አስታውቋል። አሁን ደግሞ ‘አዲስ ጤፍ አምበር ኤል’ በሚል መጠሪያ የተሠየመ በአሜሪካ ከሚመረት ጤፍ የተዘጋጀ ልዩ ቢራ ካሁን በፊት ምርቱን ከሚያሰራጭባቸው ግዛቶች በተጨማሪ ጥቁር አሜሪካውያንና የካሪቢያን ተወላጆች በስፋት በሚኖሩባቸው በጆርጂያና ሚኖሶታ ለገበያ እንደሚያቀርብ የቢራ ጠማቂው ድርጅት በስልክ ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።

በ2016 (እ.ኤ.አ.) የተቋቋመው ንጉሥ ቢራ ኩባንያ የገበያ አድማሱንም በማሳቹሴት፣ ጆርጂያ፣ ሚኖሶታና ካናዳ የማስፋት ዕቅድ እንዳለው የፋይናስ ኦፊሰሩ አብራርተዋል። ኩባንያ ከጤፍ ቢራ ማምረት የቻለው ከዓመታት የምርምርና ሙከራ በኋላ መሆኑን ጠቅሷል።

ለምርት ዋነኛ ግብዓት የሆነውን ጤፍ ከኢትዮጵያ ማስገባል ያልፈለኩት በኢትዮጵያ የምርቱ እጥረት እንዳይፈጠር ነው ያለው ኩባንያው፤ ከጤፍ ቢራ ምርቱ ከማገኘው ገቢ በኢትዮጵያ የጤፍ እጥረትን በዘላቂነት ማስወገድ እንዲቻልና የምርቱን መጠን ከፍ ለማድረግ በአገራችን በጤፍ ላይ የሚሰሩ የእርሻ ምርምሮችን በገንዘብ እደጉማለሁ ብሏል። የጤፍ ቢራ ምርት ስርጭትን ከማስፋፋት አልፎ የንጉሥ ቢራ ኩባንያ ጠላ፣ ጠጅ፣ እንደዚሁም ከአልኮል ነፃ ቢራ አና ሌሎችም የኢትዮጵያ ባሕላዊ መጠጦችን በዘመናዊ ፋብሪካ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ የምርምርና የሙከራ ሥራውን ያጠናቀቀ መሆንኑ አክሏል።

“ብዙ ትልልቅ ኩባንያዎች ከግሉትን ነፃ የሆነ ፓስታ፣ ዳቦ፣ ኬክና የመሳሰሉትን ምርቶች ከጤፍ በማዘጋጀት ከፍተኛ ገቢ እያገኙበት ሲሆን እኛ ኢትዮጵያውያን ግን የጤፍን አጠቃቀም ለማስፋፋት አሁንም ድረስ ጥረት ስናደርግ አይታይም። በመሆኑም የንጉሥ ቢራ ኩባንያ ጤፍን ለቢራ ጠመቃ በጥሬ ዕቃነት በመጠቀም እና ሌሎች የጤፍ አጠቃቀሞችን በማስፋት ዓለም ዓቀፍ እውቅና አንዲኖረው ለማድረግ በመሥራት ላይ ይገኛል”። ሲል ኩባንያው በቀጣይ ሊሠራ ያሰበውን እቅድ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስቀምጧል። ለዚህም የኩባያውን አቅም ለማሳደግ በአገር ቤትና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአክሲዮን ድርሻ በመሸጥ ዐሥር ሚሊዮን ዶላር ካፒታል የማሰባሰብ ፍላጎች እንዳለው አስታውቋል። በዚህም በአነስተኛ መዋዕለ-ንዋይ የሚቋቋሙ የቢራ ፋብሪካዎችን ኢትዮጵያውያን፣ ጥቁር አሜሪካውያንና የካሪቢያን ተወላጆች በስፋት በሚኖሩባቸው የሰሜን አሜሪካ ከተሞች በመክፈት የገበያ አድማሱን የማስፋት እቅድ እንዳለው ገልፀዋል። በተጨማሪም ከአምስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ምርቱን በኢትዮጵያ የማምረት ፍላጎት እንዳለውም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ንጉስ ቢራ የሚባል በሐበሻ ቢራ የሚመረት ከአልኮል ነፃ የሆነ ቢራ በመኖሩ ከሥም ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችልን ውዝግብ በተመለከተ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ የኛ ንጉስ ቢራ ቀድሞ ወደ ገበያ የገባ በመሆኑ ከሐበሻ ቢራ በኩል ችግር ይገጥመናል ብለን አናስብም ብለዋል። በጉዳዩ ላይ አዲስ አበባ የሚገኘውን ሐበሻ ቢራ ኩባንያቸው እንዳነጋገራቸውና አጥጋቢ መልስ እንዳላገኙም ገልፀዋል። አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በተመለከተ ሐበሻ ቢራን ለማናገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

በኢትዮጵያ በዋነኛነት በእንጀራ መልክ ለምግብነት የሚውለው ጤፍ የተለያዩ የጨጓራ፣ የአንጀት፣ የቆዳና የነርቭ ስርዓት መቃወስና ሌሎችም በሽታዎችን አምጪ የሆነው ግሉትን የተባለው የፕሮቲን ንጥረ ነገር በውስጡ ባለመኖሩ ምክንያት ተፈላጊነቱ በመላው ዓለም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል። በውስጡም የተለያዩ የምግብ ንጥረ ነገሮች ያሉትና ለተለያዩ የምግብ አዘገጃጀቶች ምቹ በመሆኑ በዓለም ላይ ከፍተኛ ታዋቂነትን እያተረፈ ከመሆኑም በላይ የወደፊቱ የዓለም ዓይነተኛ ምግብ (The next super food) የሚል ዕውቅና ተችሮታል።

ይሁን እንጂ ይህ በዋናነት በኢትዮጵያ የሚገኝ ምርት በቂ ክትትልና ጥበቃ ሳይደረግለት በመቅረቱ ምርቱ ተገቢ የዘረመል ባለቤትነት ጥበቃና ከለላ ሳይደረግለት ወደተለያዩ አገሮች መውጣት ችሏል። በዚህም ኤይንሸንት ግሬይን (Ancientgrain) የተባለ የደች ኩባንያ በምርቱ ላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ በአውሮፓ በመውሰድ ኢትዮጵያ በምርቱ ላይ ያላትን የባለቤትነት መብት ሲገዳደር መቆየቱ ይታወሳል። ምንም እንኳን ዘ ሔግ በሚገኝ ፍርድ ቤት ኩባያው ያቀረበው የባለቤትነት መብት ከስድስት ወር በፊት ውድቅ የተደረገ ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ ከምርቱ ጋር በተያያዝ የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለው ደካማ አያያዝ አገሪቱን ለሌሎችም ችግሮች እንደሚዳርጋት የሚሰጉ የዘርፉ ባለሙያዎች አሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com