የደብሊን ተረኮች – ከውስኪ ሙዚየም እስከ አራቱ ወንጌላት

Views: 279

ለዕረፍት ኹለት ሳምንታትን በአየርላንድ ያሳለፉት ቤተልሔም ነጋሽ፥ የአገሪቱ መስህብ ከሆኑት መካከል በተለይ ስለውስኪ ሙዚየም እና ስለታዋቂው ቡክ ኦፍ ኬልስ ኤግዚቢሽና ቤተመጻሕፍት በመጻፍ ተደራሲያንን የጉብኝታቸው ተቋዳሽ አድርገዋል።

 

 

ስትገዙት ሀብታም የሚያደርጋችሁ ብቸኛ ነገር ጉዞ ነው። “TRAVEL IS THE ONLY THING YOU BUY THAT MAKES YOU RICHER.” ይላል ምንጭ ያልተጠቀሰበት አንድ አባባል። ማድረግ ከሚያስደስቱኝ ነገሮች መካከል እንድጠቅስ ስጠየቅ ምናልባት ከማንበብ ቀጥሎ የሚመጣው መጓዝ አዲስ አገር ማየት፣ አዲስ ባሕል መተዋወቅ አዳዲስ የአኗኗር ዘይቤ መመልከት ነው እላለሁ። በመጨረሻ ደሃ ባልሆን ኖሮ ብዙ እጓዝ ነበር ብዬ እጨምርበታለሁ። ይህን ስል የተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራትን ከማየቴ ጎን ለጎን፣ ሥራ ምስጋና ይግባውና የማላውቀው የአገሬ ክፍል አለመኖሩን በኩራት በመጥቀስም ጭምር ነው። ለዛሬ ለኹለት ሳምንታት ዕረፍት የቆየሁባትን አየርላንድን ሳስቃኛችሁ፣ ይህ ጽሑፍ በምንም መልኩ ውቧንና ባለብዙ ታሪኳን አየርላንድንና ከትንሽዋ ደሴት ተነስተው ዓለም ላይ ተጽዕኖ ያሳረፉትን አይሪሾችን ታሪክ እገልፀዋለሁ ብዬ በማሰብ አይደለም። ይልቁን በቆይታዬ ያየሁትን ጥቂት ግን አስገራሚና አስደሳች ገጠመኝ ለማጋራት ያህል እንጂ።

የአገር ጉብኝትና ስለዚህ አገር ሊኖራችሁ የሚችለው ምልከታ በአገራችሁ ካለው ኤምባሲ ካለፋችሁበት ልምድ ይጀምራል የሚል አባባል የሰማሁ መስሎኛል። ከሌለም ግዴለም ታገሱኝ።

የአየርላንድ ነገር አዲስ አበባ ካለው ኤምባሲ ይጀምራል። የአየርላንድ የቪዛ ሒደት እስከዛሬ ከጎበኘኋቸው በዐሥርት ከሚቆጠሩ አገራት እጅግ ቀላሉ ነው ለማለት ይቻላል። የአንዳንዶቹ እጅግ አሰልቺ ከመሆኑ የተነሳ፣ በድረ ገጽ በቀጥታ ከዚያ በወረቀት ሰነድ ማስገባት፣ ከዛ ኤምባሲዎቹ ትላለቅ ግቢዎች በአዲስ አበባ ቢኖራቸውም እንኳን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሒደቱ የሚሠራ በመሆኑ በስልክ እየተደወለ መረጃ ስትጠየቁ፣ አንዳንዴ በቃ ተውት አልሔድም በሉ ያሰኛችኋል። የሚጠይቋቸውን በርካታ ነገሮች ለሚያሟላ እና ደህና የጉዞ ሪከርድ ላለው ለእነደኔ ዓይነቱ ሳይቀር (“ቀላል ሰው እንዳልመስላችሁ!” ዓይነት ጉራም አለበት) ቪዛ ፕሮሰስ ማድረግ አድካሚ ነገር አለው። በኢትዮጵያ ፓስፖርት የመጓዝን አታካች ጉዳይ ራሱን የቻለ ገጠመኝና ብሶት ስላለው ለሌላ ወግ ይቆየን።

ከአዲስ አበባ ወደ አይርላንድ-ደብሊን ለመድረስ ዘጠኝ ሰዓታት የአየር ላይ በረራ ኹለት ሰዓት መካከል ላይ ማድሪድ ስፔን መቆየትን ጨምሮ ዐሥራ አንድ ሰዓት ይጠይቃል። የመጀመሪያው ጉዞ ሰባት ሰዓት ገደማ ሲፈጅ ማድሪድ ለኹለት ሰዓታት ረፍት አድርጎ ኹለት ሰዓትና ጥቂት ደቂቃዎችን በርሮ ደብሊን ይደርሳል።
ማድሪድ እስክንደርስ የነበረው በረራ ፊልም በማየት፣ በማንበብ ለመተኛት በመሞከር እንደምንም አልፎ፣ ማድሪድ ላይ ሲያርፍ እዛው እግር ለማፍታታት ዞር ዞር ብለን፣ አውሮፕላኑ ተጨማሪ መንገደኞችን አሳፍሮ ካሁን አሁን ተነሳን ስንል ያልተጠበቀ ነገር!

“የማናግራችሁ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ነኝ፣ ኬኔት እባላለሁ። ወደ ደብሊን ለምናደርገው በረራ ለመነሳት ዝግጁ ነበርን፤ ሆኖም በፈረንሳይ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ባለ ክርክር ምክንያት የበረራ መዘግየት ይኖራል። እዚህ የምንቆየው ለአራት ሰዓት እንደሆነ የተገመተ ሲሆን አሁን አንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ ዝቅ እንዳለ ተነግሮናል። በጉዳዩ ላይ እየሠራን ስንሆን በየሰዓቱ የደረስንበትን እናሳውቃችኋለን” ተባልን።

በረራው ሰባት ሰዓት ከማድሪድ ወደ ደብሊን ሊነሳ ዝግጅቱን አጠናቆ እያለ ምናልባት በመዘግየቱ “ምንድነው የሆነ ነገር አለንዴ?” ልንል ስንል ነው ማሳሰቢያውን የሰማነው።

ለነገሩ ከአዲስ አበባ ማድሪድ የነበረው የበረራው የመጀመሪያው ክፍልም ከምሽቱ አምስት ሰዓት መነሳት ሲገባው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ከዐሥር ላይ ነበር የተነሳው።

አንድ ሰዓት
ከዚያ በፊት ብዙ መድረሻዎችን ያሳፍር በነበረውና በሚቁነጠነጡ የደከማቸው ወደ መሔጃቸው ለመድረስ ክፉኛ የፈለጉ በሚመስሉ በርካታ መንገደኞች የተጨናነቀው ማሳፈሪያ በር ቁጥር C 11 ላይም ተሰብስበን እየጠበቀን በፌደራል ፖሊስ ጣልቃ ገብነት የበረደ የአንዳንድ መንገደኞች ድንፋታ፣ ጫጫታና ፉጨት ውጥረትም ጭምር አይተን ነበር። ጉዞው ከመነሻውም ጣጣ ወይም አዲስ ነገር አላጣም ልላችሁ ነው።
ጥቂት ቆይቶ መብራቶች ሁሉ ጠፍተው የፊልም ማሳያ ስክሪን በእያንዳችን ፊት ለፊት የታየው ብቻ ቀረ

ከ 30 ደቂቃ በኋላ
ካፒቴናችሁ ነኝ። እንዳለመታደል ሆኖ የፈረንሳይ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ነገር ትንሽ ብሷል። ስለዚህ ሞተራችንን መልሰን የምናስነሳው ከኹለት ሰዓት በኋላ ይሆናል በማድሪድ የሚገኙ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚቻላቸውን እየጣሩ ነው። ሰላሳ አውሮፕላኖች ነን ለመነሳት በመጠባበቅ ላይ ያለነው። በተፈጠረው ነገር ብናዝንም መሻሻሎች በመኖራቸው እንጽናናለን።

እዚሁ ሆነን የሚቀጥለውን እርምጃ እንጠባበቃለን አመሰግናለሁ።”
ቆይቶ ከሦስት ሰዓታት ጥበቃ በኋላ ነዳጅ ለመቅዳትና ለመንቀሳቀስ ተፈቅዶልን ተነሳን ከማድሪድ ደብሊን ኹለት ሰዓት ከ22 ደቂቃ እንደሚፈጅና ደብሊን ከቀኑ ስድስት ሰዓት ከሰላሳ አምስት እንደምንደርስ ሲነገረን ይህንንስ ማን፡አየ ብዬ ነበር እንዳንዳንድ ጊዜ አመጽ 24 ሰዓት ቢቆይስ?
ከአውሮፕላኑ ለመውረድ የሚያስችል ፈቃፍ የሌለን ብዙ ነበርን። እንዳሁን አራት ሰዓት መቀመጥ ራሱ መከራ ነው
አውሮፕላኑ ደብሊን ሲያርፍ ሰዓቱ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ከሩብ ነበር። በኋላ እኛን ጨምሮ ከማድሪድ-ባራጋስ አዶልፎ ሱዋሬዝ አውሮፕላን ማረፊያ በተመሳሳይ ሰዓት ለመነሳት ሲጠባበቁ የነበሩ ዐሥራ አምስት አውሮፕላኖቹን ጉዞ ያስተጓጎለው ክስተት የሠራተኞች ሥራ ማቆም ክርክር ሳይሆን የኮምፒውተር ሲስተም ችግር እንደሆነ ከዜና አውታሮች ማወቅ ችያለሁ። በመላው አውሮፓ ያሉ የፈረንሳይን የአየር ክልል የሚያልፉ በረራዎች ሁሉ በዚህ ክስተት ተስተጓጉለዋል።

አጠቃላይ መረጃ ስለ አየርላንድ
አየርላንድ በሰሜን አትላንቲክ የምትገኝ፣ የምዕራብ አውሮፓ አካል የሆነች ደሴት ስትሆን ትልቁና ዋና ከተማዋ ደብሊን ነው። አይርላንድ ከሚሰኘው ደሴት 32 አውራጃዎች መካከል የአይርላንድ ሪፐብሊክ 26ቱንና የደሴቲቱን 5/6ኛ ስትይዝ ቀሪዎቹ 6 አውራጃዎች በሪፈረንደምና በፈቃዳቸው በአስተዳደር በዩናይትድ ኪንግደም ሥር የሚገኙት የሰሜን አየርላንዳውያን ናቸው። የሥራ ቋንቋቸው እንግሊዝኛና አይሪሽ ሲሆን ከምልክትነት ባለፈ አይሪሽ ቋንቋ በተናጋሪ አንጻር እምብዛም እንዳልሆነ ይነገራል። በማንነት አኳያ ስናየው አየርላንድ 82 በመቶ ሕዝቧ ነጭ አይሪሽ ሲሆን 9.5 በመቶው ሌሎች ነጮች ተብለው የተመዘገቡ ናቸው 2.1 እስያ- አይሪሽ ሲሆኑ 1.2 ጥቁር አይሪሽ ናቸው። ሌላው ክፍልፋይ ሌሎች ዘሮች፣ የማይታውቁ ተብለው የተዘረዘሩ ናቸው። የመንግሥት አስተዳደሯ ፓርላሜንታዊ ሪፐብሊክ ነው። ወቅቱ ፕሬዚዳንቷ ሚካኤል ሂግንስ ይባላሉ። ለረጅም ዓመታት በብሪታኒያ ቅኝ ሥር የቆየች ሲሆን ነፃነቷን ያገኘችው በአንግሎ አይሪሽ ስምምነት መፈረም በ1921 ነው። ጥር 1973 (እ.ኤ.አ.) የአውሮፓ ኅብረት አባል ሆናለች ።

ከእንግሊዝ ቀጥሎ በዓለማችን ብዙ ሕዝብ የያዘች ደሴት ስትሆን በ2019 ግምት 4.9 ሚሊዮን ናቸው። አየርላንድ በዓለም ላይ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ካላቸው አገራት መካከል ስትጠቀስ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 79 ሺሕ 925 የአሜሪካ ዶላር ነው ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትም (ጂዲፒዋ) በ2018 ግምት 385 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ሂውማን ዲቨሎፕመንት ኢንዴክስ በዓለም አራተኛ ደረጃ ላይ ሆና ከሃብታም አገራት ተርታ ከፍተኛ ደረጃ ይዛለች።
ባለዝና ከሆነችው አየርላንድ – ደብሊን ገብቼ መውጫ መግቢያዬን አይቼ የከተማዋን ዋና ዋና ቦታዎች ማየት ከቻልኩ በኋላ ቀጣዩ ዝነኛ የሆኑ መታየት አለባቸው ከሚባሉ ቦታዎች መካከል የቱን ልይ የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነበር። እንደምርጫዬ እንደነበረኝ ጊዜና እንደጓደኞቼ ምክር ያየኋቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከአየርላንድ መረጃዎቸ ጋር ከዚህ እንደሚከተለው ላካፍላችሁ እሞክራለሁ።

የውስኪ ሙዚየም
“አይሪሾች ዓለምን እንዳይገዙ ለመከልከል አምላክ ውስኪን ፈጠረ” ኢድ ማክማሆን
የአይሪሾችን የመጠጥ ፍቅርና ዝንባሌ (እነሱም በኩራት ያምኑታል፣ በየአጋጣሚው ደጋግመው ይነግሯችኋል) ለመረዳት ይህ ጥቅስ ጥሩ አመላካች ነው።
ከደብሊን ሳትወጡ ማየት ከምትችሏቸው የቱሪስት መስህብና አይሪሾች የታሪካችን አካል ብለው በ2014 (እ.ኤ.አ.) ሙዚየም ካቆሙለት ጉዳይ አንዱ የውስኪ ታሪክ ነው። በሥነ ስርዓት ከሚያስተዋውቋቸው መስህቦች አንዱ ነው። መቼም በእንግሊዛውኛን ጨዋታ አዋቂነት (ሳቅ አፍላቂነት) የተገረምኩትን ያህል ጎረቤታቸው አየርላንድም በዚህ እንደማትታማ የገባኝ የመጀመሪያውን በአስጎብኚ የተካሔደ ገለጻ በውስኪ ሙዚየም ሳገኝ ነው። ሙዝየሙ (ያው ልትጠረጥሩ እንደምትችሉት) በከተማው አንደኛ ማወቅ ከምፈልገው የገበያ ሥፍራ ግራፍተን ጎዳና በተባለው የከተማዋ ማዕከላዊ ሥፍራ ይገኛል። ከመንግሥትም ሆነ ከቱሪዝም ድርጅት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ያልሆነ የግል ተቋም ነው ሙዝየሙ። በጉብኝታችን መጀመሪያም የሚያስቀምሷችሁ ውስኪዎች አምራቾች ሳይቀሩ ስፖንሰር እንዳላደረጓቸውና በግል እንደሚንቀሳቀሱ ይነግሯችኋል።

ትኬቱን ከመሃል ከተማ ካለው የቱሪስት ቢሮ ቆርጬ በተባልኩት ሰዓት ስደርስ እንደኔው ጉብኝቱን ለመቀላቀል ከተሰበሰቡ የሌሎች አገር ጎብኚዎች ጋር ተቀላቀልኩ። ጉብኝቱ ከታች ከሙዝየሙ ባር ሲጀመር አጠቃላይ መረጃዎች አንደኛ ፎቅ ከሚገኘው ባር ሰብሰብ ብለን ሰማን። ከላይ እንዳልኩት አስጎብኛችን ማርክ አየርላንዳዊ መሆኑንና በየ50 ሜትሩ ባር ካለበት ከተማ ማደጉ ኩራት እንደሚሰማው ገልፆ “የሚገርማችሁ ካናዳ አንዱ ከተማ ነበርኩ እዚህ ከመምጣቴ በፊት፤ ለሥራ ሔጄ፣ ባር ለማግኘት 15 ኪሎ ሜትር መንዳት ነበረብኝ፣ 15 ኪሎ ሜትር! ያው ልትጠረጥሩ እንደምትችሉት አልቻልኩም፣ ደብሊን ተመለስኩ!” አለን። ቀጠለናም “ስኮትላንድ ብትሔዱ ልክ እንደኛው ሙዝየም አላቸው፤ ውስኪን እኛ ፈጠርን ይሏችኋል። እዚህም እኛ እንደዛው እንላለን። ቁልፉ ግን ለእናንተ ሁለታችንንም አለመስማት ነው” አለ። ሳቃችን ሲበቃ ወደሚቀጥለው ወለል ተወስደን ስለ ውስኪ ታሪካዊ አመጣጥ በቪዲዮና በስላይድ የታገዘ ገለፃ ቀረበ፤ የአያቴን የአረቄ ማውጫ ባሕላዊ እንስራ አብሮት ተያይዞ ያለው የቅል ስባሪ አናት ያለበት ቱቦና ማጥለያ ተመለከትን። ውስኪ ለነገስታት እጅ መንሻ ይውል እንደነበር የአየርላንድ የቆየች ንግስት ታሪክ ተያይዞ ተነገረን፣ አደረሰ ከሚባለው ጉዳትና ከመጠን ያለፈ አጠቃቀምን ጨምሮ ከታክስ ለማምለጥ ይደረግ ስለነበረ ሸፍጥና በውጤቱ የተለያየ ዓይነት አመራረት (በብቅል አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የቀረጥ ሒደት ነበር) ሒደቶችና ስያሜዎች ተነገረን፤ ውስኪ የተለያዩ ቀለሞች እንዲያመጣ ስለሚያደርገው ሒደት ጭምር። የመጨረሻው ወለል ደርሰን የምትጠጡ ወደ ፊት ኑ ተብሎ አራት የተለያየ የአመራረት ሒደት የተከተሉ (ነጠላ ብቅል፣ ደብል ብቅል፣ ሦስት ጊዜ የተጣራ፣ ቅልቅል/ብሌንድድ) ሲጠጡ በሰውነታችን ላይ የተለያየ ስሜት ከሚፈጥሩ ውስኪዎች ጋር ተዋወቅን። ተዋወቅን ያልኩት ራሴን በመወከል ሲሆን ከዚያ በፊት ውስኪ ጠጪ አልነበርኩም፤ የአይሪሽ ውስኪ የሚባል ብራንድ ስለመኖሩም አላውቅም፤ ውስኪ የሚተረክ ታሪክ እንዳለውም እንዲሁ። ከጉዞ የመጣ አንድ እውቀት አትሉም?
በጉብኝቴ ካየኋቸው ቦታዎች አንድ ተጨማሪ ነገር ላስቃኛችሁና በአይሪሾች ምርቃት ለሳምንት ቀጠሮ ይዘን እንለያይ
የ“ቡክ ኦፍ ኬልስ” ኤግዚቢሽንና ቤተመጻሕፍት – ደብሊን ትሪኒቲ ኮሌጅ
ቡክ ኦፍ ኬልስ በደብሊን ትሪኒቲ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኝ ቋሚ ኤግዚቢሽንና በዕድሜ ትልቅ የሚባለው ሎንግ ሩም የሚሉት መንፈሳዊ መጻሕፍትን የያዘ ከመሬት እስከ ጣራ በረጃጅም በመሰላል በሚወጣባቸው የመጻሕፍት መደሪደሪያዎች የተሞላ የጥንት ላይብረሪ ያለበት የጉብኝት ሥፍራ ነው። ወደ ቋሚ ኤግዚቢሽኑ ለመግባት ያለውን ሰልፍ ስታዩ ትገረማላችሁ። ለእኔ ካየሁት ሁሉ የገረመኝ በብራና የተጻፈ፣ ባለ ቀለም ስዕል የሞላው ውዳሴ ማርያም በቡክ ኦፍ ኬልስ ወይም የኬልስ መጻሕፍት ከሚባሉት ተርታ ከተቀመጡ ሌሎች ታሪካዊ መጻሕፍት ጋር አብሮ ተቀምጦ ማየቴ። በመስታውት ውስጥ ከመጻሐፉ ጋር ያየሁት ገለጻ ግን አልተመቸኝም “ከሰሜን አፍሪካ፣ ከኢትዮጵያ የመጣ፣ የተጻፈበት ጊዜ የማይታወቅ” ይላል። እውነት? ኢትዮጵያ የምትገኘው በሰሜን አፍሪካ ነው?

በቡክ ኦፍ ኬልስ ወይም የኬልስ መጻሕፍት የሚባሉት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ384 ዓመተ ዓለም በላቲን ቋንቋ፣ ቩልጌት በተባሉት ፊደላት የተጻፉትና በዚሁ ወቅት ቅዱስ ዤሮም አጠናቀቃቸው የተባሉት የአራቱ የክርስቶስ ወንጌላት በትላልቅ ብራና ላይ በውብ ቀለምና የፊደል አጣጣል የቀረበባቸው ጽሑፎች ስብስብ ነው። 340 በተለያየ ቅርጽና መጠን የቀረቡ የወንጌላቱ በአጫጭሩ የቀረቡ ማጠቃለያ መሰል ዝርዝሮችና ስዕላዊ መግለጫዎችን የያዙ ሲሆን የተጻፉት በጥጃ ቆዳ በተዘጋጀ ብራና ላይ መሆኑ ተመልክቷል። አሳሳልና የሚያምር አቀራረባቸው፣ የክርስቶስን የምድር መመላለስ ያሳዩበት ሁናቴና የቆዩበት ዘመን ልዩ ያደርጋቸዋል እንደመረጃዎቹ።
የቀሩትን የደብሊን ታሪኮች ሳምንት፤ በአይሪሽ ምርቃት ስንለያይ፤

“ሁሉም ቀን ከጅምሩ አስደሳች ይሁንላችሁ፤ መልካም ዕድልና መዝሙር በልባችሁ ይኑር!”
”A wish that every day for you will be happy from the start and may you always have good luck and a song within your heart.”
Irish Blessing

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com