ቱሪዝም፡ “በእጅ ያለ ወርቅ…”

Views: 418

አዲስ ዓመት በመስከረም ወር እነሆኝ ብሎ ብቅ ከማለቱ እንደወትሮው ሁሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላት በአጀብ ተቀብለውታል። ዛሬ፣ መስከረም 17 በመላው ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል በዓል በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ይገኛል።

በተለይ ትላንትና በዋዜማው አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የደመራ በዓል ሥነ ስርዓት ተካሒዷል። በተለይ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ዕለቱ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የተከበረ ሲሆን፣ ችቦ በመለኮሱ ሥነ ስርዓት ላይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አባቶች፣ የከተማዋ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ ዲፕሎማቶች እና የተጋበዙ እንግዶች እንዲሁም የእምነቱ ተከታዮችና ጎብኚዎችን እንደተለመደው መመልከት ተችሏል።

በሚቀጥለው ሳምንት መስከረም 24/2012 ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ/ደብረ ዘይት በኦሮሞ ሕዝብ ባሕል የምሥጋና ቀን በመባል የሚታወቀው የኢሬቻ በዓል በድምቀት ይከበራል ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህ በዓላት ብዙ የውጪ አገር ቱሪስቶችን በመሳብ ይታወቃሉ።

በተጨማሪም ዮ መስቀላ፣ ጊፋታ፣ ጨምበላላ እና ሌሎችም በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚከበሩ የዘመን መለወጫ በዓላት በቀጣይም ወሩን አድምቀውት፣ የጎብኚንም ቀልብ ይዘው ይቆያሉ። በሰሜን ኢትዮጵያ አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶለን የተባሉ የልጃገረዶች ክብረ በዓላት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ለቀናት በድምቀት መከበራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

እነዚህ ለወራት ድምቀት ለሰው ልጅም ተፈጥሮንና ዙሪያውን እንዲያደንቅበት ምክንያት የሆኑ በዓላት፤ ሀብቴ ብሎ ለያዘው ኢትዮጵያዊ ኩራት ብቻ ሳይሆን ለቱሪዝምም ምንም እንኳን ያለውን እምቅ ሀብት በተገቢው ጥቅማ ላይ ባይውልም የገቢ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያውያን ብዙ ሀብት አለን ብለን የምንኮራ ሕዝቦች ሆነን ሳለ ዓለም በሚግባባበት ደረጃ ግን አገራችን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሕዝቦች የሞሉባት ናት፤ ይህም ደሃ ከሚባሉ አገራት ተርታ ያስመድባታል። ለኩራት የሚያበቁ ሆነው የተገኙ ሀብቶቿም በአንድ በኩል በተፈጥሮ የታደለቻቸው በሌላ በኩል ገናና በነበረችበት ዘመን ነገሥታቱ፣ ሊቃውንቱና ቅዱሳን የተባሉ የሃይማኖት ሰዎች ያቆዩላት ቅርስ ነው።

አሁን ከዘመናት በኋላ ታድያ እነዚህ ቁሳዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ሀብቶች በተለያዩ ምክንያቶች ተቆልፎባቸዋል። ብዙዎችም የኢኮኖሚ መፍትሔዎቻችን ቁልፍ ይህ ቱሪዝም ሊሆን እንደሚችል እምነታቸውን ይገልጻሉ። ይህም የሚባለው አንዳንድ አገራት ሀብታቸው ነዳጅ ሆኖ በነዳጅ እንደሚከብሩ ሁሉ፤ ኢትዮጵያም ያላት ሀብት ለቱሪዝም ምቹ የሚያደርጋት በመሆኑ ነው። ባሉት ችግሮች ምክንያት ግን በቱሪዝም ሊገኝ ብቻ ሳይሆን ሊታፈስ የሚችለውን ገንዘብ ማግኘት አልቻለችም። ዘርፉም ትርፍ ማግኘት ቀርቶ ራሱን ማደስ እንዳይችል ሆኖ ጥገኝነት ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሳምንት በፊት በመስከረም 2012 ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ ታስቦ የተጀመረውን የቤተ መንግሥቱን የግንባታ እንቅስቃሴ አስጎብኝተው ነበር። “ብዙ ኢትዮጵያዊ አገሩ ውስጥ ያለውን አያውቅም” ሲሉ የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ያለውን ሀብት አስተካክሎ መጠቀም የገቢ ጥቅም ብቻ አይደለም ሲሉ፤ “በቤተ መንግሥት ጊቢ ውስጥ ያለው ሀብት ተስተካክሎ ለዜጎችም ሆነ ለጎብኚዎች ቢገለጥ፤ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የማንነትን ልክ ያሳያል፤ አዳዲስ ነገር ለመፍጠርም ያነሳሳል” ብለው ነበር።

አያይዘው ካነሷቸው ነጥቦች በተጓዳኝ፤ ያለውን ሀብት የቱሪዝም ጥቅም እንዲያስገኝ ማመቻቸት ወሳኝ ሥራ መሆኑ አንዱ ነው። አሁን ላይ እንደቁምጣ ያጠረን የውጪ ምንዛሬ ገቢን ከፍ ለማድረግም ትልቁና ሰፊው ምንጭ ይኸው ቱሪዝም መሆኑ ሳይታለም የሚፈታ ነው። ያም ብቻ አይደለም የሰው ኀይል በማሠማራት ረገድ ጥቂት የማይባል ሥራ ሊፈጥር የሚችል መስክ ነው። ታድያ ይህ በኢኮኖሚ አቅምን ለማጎልበት ቀዳሚ ተጠሪ ሊሆን የሚችል ዘርፍ ለምን እና እንዴት ተቆለፈበት?

የተቆለፈበት ቁልፍ
አገራት ኢኮኖሚያቸውን የተሻለ ሊደግፍ ይችላል ያሉትን ዘርፍ ቅድሚያ ለመስጠት ይመርጣሉ። በዚህ መሠረት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ቱሪዝምን ለኢኮኖሚ ቀዳሚ የገቢ ምንጫቸው አድርገውና ከኢኮኖሚ ጋር አስተሳስረው የያዙ አገራት አሉ። እነዚህ አገራት ለቱሪዝም ቅድሚያ በመስጠት ለዘርፉ አስፈላጊውን ሁሉ ያሟላሉ፤ ለመሠረተ ልማት፣ ግንባታዎች፣ የሰው ኀይል ሥልጠና፣ ማስታወቂያና መሰል ተግባራትም በጀት መድበው ይንቀሳቀሳሉ።

ይህን በመጥቀስ ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያካፈሉት በጋዜጠኝነት ሙያ በቱሪዝም ላይ ከዘጠኝ ዓመት በላይ ያገለገሉት የሀገረ ሰብ ሬድዮ ፕሮግራም አዘጋጅ አስናቀ ብርሃኑ፤ ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ትርፍ ተጠቃሚ ያልሆነችበት ምክንያት ለዘርፉ ቅድሚያ አለመስጠቷ እንደሆነ ይናገራሉ። አሁን ባለበትና ትኩረት አግኝቷል በሚባልበት ደረጃ እንኳን በበጀት ለውጥ አምጥቷል ማለት እንደማይቻል ነው የሚገልጹት።

በቱሪዝም የእሴት ትስስር ከፍተኛ ዋጋ ይሰጠዋል። ይህም አንድ ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣና ቆይታው ሲራዘም ወጪው በዛው ልክ የሚጨምር በመሆኑ ነው። በዚህም ከታች ጫማ ከሚያጸዳው ሊስትሮ አንስቶ እስከ መንግሥት ድረስ በመካከል ያለውም ሁሉ ተጠቃሚ ይሆናል። ለዚህ ግን በተግባር ያለው መዋቅር ደካማ መሆኑ ኢትዮጵያ በዘርፉ እጇ እንዳይፈታ አድርጎ የቆለፈባት አንዱ ምክንያት ነው። በጠቅላላው ዘርፉ ገቢ ያመጣል ብሎ ማመን ላይ ችግር እንዳለ አስናቀ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቅሰዋል።

ከዚህ በሻገር በመንግሥት በኩል ለቱሪዝም ዘርፉ ፖሊሲ ለማውጣት እጅግ ተዘግይቷል። በዚህም ላይ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ምክንያት የተፈጠረበት ጫናም ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አዳክሟል። ከዚህ በተጨማሪ ተዘዋውሮ በዓለም ዐቀፍ መድረክ ማስታወቂያ አለማስነገርም ሌላው መፍትሔውን የቆለፈበት ችግር ነው።

በብዙና ሰፊ ፕሮዳክሽን የሚሠሩ ማስታወቂያዎች በማይኖሩ ጊዜ፤ አንዴ መጥቶ የጎበኘ የውጪ አገር ዜጋ ወደ መኖሪያ ቦታው ሲመለስ አምባሳደር ሆኖ ሊያገለግል ይችል ነበር፤ በማስተዋወቅ። ነገር ግን የመስተንግዶውም ነገር ደካማ በመሆኑ፣ ሆቴሎችም በቂ ባለመሆናቸው ጎብኚዎች ይዘው የሚሔዱት መልዕክት ጥሩ የመሆን እድሉ ጠባብ ነው። “አያድርገውና አሁን አንድ ሚሊዮን ቱሪስት ቢመጣ ለማስተናድ እንቸገራለን።” ያሉት አስናቀ፤ “የዋጋ ውድነትም አለ፤ ይህም መዳረሻዎች ላይ ሳይሆን አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የሚታይ ነው” ብለዋል።

ከዋጋ ውድነቱ ጋር በተያያዘ፤ አንድ ጎብኚ ወደ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቢያቀና ለመጎብኘት 3 ዶላር ነው የሚከፍለው። ይህም ምናልባት በዓለም ደረጃ ዝቅተኛ ሊባል የሚችል ዋጋ እንደሆነ አስናቀ ይጠቁማሉ። ይሁንና በሚያርፍበት ሆቴል ግን አብዛኞቹ ጎብኚዎች ቅሬታ እስኪያቀርቡ ድረስ ከፍተኛ ክፍያ ይጠየቃል።
ከዚሁ ላይ በቂ መስተንግዶ አለመደረጉ አለ፤ አስናቀ ነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክን በማሳያነት አንስተው መግቢያው ለጉብኝት የሚማርክ እንዳይደለ ያመላክታሉ። አንድ ጎብኚ ወደ አፋር ኤርታሌን ለማየት ቢሔድ፤ በስፍራው ውሃ የሚያቀርብ እንኳን አያገኝም። ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ በተሽከርካሪ መሔድን የመረጠ ጎብኚ መጸዳዳት ቢፈልግ መንገድ ላይ አንድም ቦታ አያገኝም። እናም የጎብኚዎችን ፍላጎትና ሥነ ልቦና ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ‘ደንበኛ ንጉሥ ነው’ የሚል መሠረተ ልማት የለም ማለት ነው። ይህም የጎብኚውን ቆይታ አሳጥሮ ገቢውንም በዛው መጠን ይቀንሰዋል።

አስናቀም “መሠረተ ልማት እና መዳረሻዎችን ምቹ ማድረግ ላይ ከተሠራ ኢትዮጵያ ያላት ሀብት በሚሊዮን የሚቆጠር ቱሪስት፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብም ያስገኛታል” ሲሉ ገልጸዋል። በድምሩ ግን የግንዛቤ ማነስ፣ የአቅም ማጣትና ትኩረት መንፈግ የተባሉና ሌሎች ምክንያቶች ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር መፍትሔ የሚከፍተውን ቁልፍ ቆልፈውበት ይገኛሉ።

ሌላው ማሳያ ደግሞ አክሱም ነው። ለቱሪስት መስህብና ለኢትዮጵውያንም ኩራት ከሆኑ ቅርሶች፤ ብሎም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት የተመዘገበው የአክሱም ከተማ እና ትክል ድንጋይ፤ ከጎብኚ መዳረሻ ቦታዎች መካከል አንዱ ነው። በአክሱም ከተማ ዳሰሳ ያደረገችው አዲስ ማለዳ ጥንታዊቷ አክሱምን ያላየና በዝና የሚያውቃት በሚሰማው ልክ የማያገኛት መሆኗን መታዘብ ችላለች።

በከተማዋ ለተገኘ ሰው የአክሱም ትክል ድንጋዮች ወዴት እንደሆኑ በመጠየቅ ካልሆነ በማየት የሚደረስበትም አይመስልም። ይሁንና የአክሱም ነዋሪ ኢትዮጵያውያን መንገድ ለመጠቆምና አቅጣጫ ለማሳየት የማይሰንፉና ቀናዎች በመሆናቸው ወደ አክሱም ትክል ድንጋዮችና የአክሱማውያን ግዛት መታወሻ የሆነውን ቅጥር ማቅናቱ አስቸጋሪ ቢሆን እንኳ ፈታኝ እንዳይሆን አድርጎታል።

በዚሁ መሠረት አክሱምን መጎብኘት ብዙ የሚያስከፍልና ውድ የሚባል አይደለም። የአገር ውስጥ ጎብኚ 200 እና 300 ብር እንዲከፍል ሲጠበቅ፤ የውጪ ጎብኚዎች ደግሞ 1 ሺሕ 200 ድረስ ይጠየቃሉ። ይህም ገቢ ሆኖ ከዚሁ ላይ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ በተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና ሰላም ማጣቶች ምክንያት የጎብኚ ቁጥር ሲቀንስ ገቢውም ካለው ወርዷል።

በአክሱም የየሐ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አምዶም ተክሌ ለአዲስ ማለዳ ይህንኑ ሲያስረዱ፤ የሆቴል ሥራዎች መቀዛቀዛቸውን ጠቅሰዋል። ይህም የሆነው ካሉት አገራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በተጓዳኝ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በሚመለከታቸው በኩል እነዚህን ቅርሶች የማስተዋወቅ ጥረት ዝቅተኛ በመሆኑ ብሎም አስጎብኚዎች የበቁ ባለመሆናቸው ነው ብለዋል። አስጎብኚዎችም በበኩላቸው ይህን ሐሳብ ይጋራሉ፤ አክለውም በቀን ቀርቶ በሳምንት ጎብኚ ዝር ሳይል እነርሱም ሥራ ፈትው እንደሚቆዩ በመጥቀስ።

ይህም ሆኖ የከተማዋን ኢኮኖሚ የቱሪዝም ዘርፉ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል። እንደምን ቢባል በከተማዋ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሀብቶች በመበራከታቸውና በርካታ የሚባሉ ሆቴሎች በመከፈታቸው ነው። ይህና መሰል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ታድያ ወደ 15 ሺሕ የሚጠጋ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉም ተብሎ ይጠበቃል። ይህ እንዲሆን ግን የተቋማት ትኩረትና የአመራር ውሳኔ ሰጪነት ከምንም በላይ ደግሞ የአገር ሰላም አስፈላጊ ነው።

አክሱምን እንደማሳያ አነሳን እንጂ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎችም መስህቦችና መዳረሻዎች፤ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶች በአገራችን አራቱም ማዕዘን ይገኛሉ። የተባሉት ሥራዎችን መቀባበል፣ ኀላፊነትን አለመውሰድ፣ እርምጃዎችን በፍጥነት አለማድረግ ወዘተ ችግሮችም በሁሉም የሚታዩ ናቸው። በእኔነት ስሜት ተቆጣጥሮ የሚሠራ የቱሪዝም ባለሙያ ስለመኖሩም ያጠራጥራል።

ኢትዮጵያ ካላት የቱሪዝም ሀብት አንጻር ተጠቃሚ አለመሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናግረው ነበር። በቅርቡ “ቱሪዝም፤ ብሩህ ተስፋ ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሐሳብ ተካሒዶ በነበረው በአንደኛው አገር ዐቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም ኮንፈረንስ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከቱሪዝም ዘርፉ ለመጠቀም በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶች መፈታት አለባቸው ሲሉ፤ ለዚህም መፍትሔው በጋራ መሥራት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

እርሳቸው በዋናነት ያነሱት መስተንግዶውን ሲሆን ከዘመነው ፍላጎት ጋር አብሮ የሚሔድ ተቋማዊ አገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖሩን ነው። “በዘርፉ የእሴት ሰንሰለት በርካታ ተዋንያን አሉ፤ በእያንዳንዱ ያለው ክፍተት ሁሉን የሚመለከት ችግር ስለሚሆን በጋራ መረባረብ ያስፈልጋል”ም ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በነሐሴ 25/2011 43ኛ ሳምንት እትሟ በትንታኔ ገጽ ላይ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት እና የኦሞ ብሔራዊ ፓርክን ውዝግብ አንስታ ነበር። ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በኦሞ ወንዝ ላይ ተመሥርቶ የተቋቋመ ፓርክ ሲሆን በድምሩ 4 ሺሕ 68 ካሬ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ውግዝቡ የተነሳው ኦሞ ኩራዝ ፋብሪካ የፓርኩን 30 ከመቶ ይዞታ በመውሰዱ ምክንያት በፓርኩ የሚገኙ እንስሳትና በጠቅላላም ሥነ ምህዳር እየታወከ በመገኘቱ ነው።

ምንም እንኳ ችግሩን ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ የተሔደና አሁንም በሒደት ላይ ያለ ጉዳይ ቢሆነም፤ ፕሮጀክቱ ግን “የተሻለ ጥቅም የማስገኘውም ሆነ አካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ የማደርገው እኔ ነኝ” በሚል የፓርኩን ጉዳት ጉዳዬ አላለውም። ፓርኩ በቱሪዝም ዘርፉ የተሠራበት በቂ ነገር ባለመኖሩ ምክንያት ፍትሕን በሚያስተናግድ ፍርድ ቤት ሚዛን ላይ ኹለቱ ቢቀመጡ በእርግጥም ፋብሪካው ሊያሸንፍም ይችላል። ለምን ቢባል የኦሞ ፓርክን ጠብቆና አልምቶ ሊያስገኝ የሚችለውን በመጠቀም ረገድ በቂ ሥራ ባለመሠራቱ ነው።

በአውሮፓውያኑና በሰለጠኑ አገራት በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ታሪካዊነታቸው የገዘፈና ዋጋቸው የማይተመን ቅርሶች ሩብ የማይሞላ ታሪካቸውን ከሽነው ያቀርባሉ። በተፈጥሮ ያገኙት ካለ እርሱን ከማቆየታቸው ባሻገር፤ ሙዝየሞችንና ሰው ሠራሽ ፓርኮችን በመከለልና በማዘጋጀት የቱሪስት መስህብ ለመሆን ዋጋ ሲከፍሉ ይታያል። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ያለውን መጠበቅ ላይ ሳይቀር ጥረቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት በወጣው መረጃ መሠረት ከአገር አገር የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1997 ከነበረው 613 ሚሊዮን በ2020 ወደ 1.6 ቢሊዮን እንደሚደርስ ተጠቅሷል። ዕድገቱም ሊቀንስ የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም ተብሏል። ያም ብቻ አይደለም ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች፣ የንግድ ተቋማት እና መዝናኛ ቦታዎች በዚያው መጠን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚሁ ዘገባ ላይ ዓለም ዐቀፍ ቱሪዝም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በአንደኛ ደረጃ የሚመደብ ነው ይላል። ያም ብቻ ሳይሆን ቱሪዝም ከየትኛውም ዘመናዊ የሚባል ኢንዱስትሪ በላይ በፍጥነት እያደገ ያለ እንደሆነም ተያይዞ የተጠቀሰ ነው። ይህ በኢትዮጵያም እንዲሆን ታድያ ቁልፉ ላይ የቆለፉበትን ጉዳዮች መፍታት አስፈላጊ ነው።

መፍትሔው ምን ይሁን?
አስናቀ እንደሚሉት የመጀመሪያው መፍትሔ ቅድሚያ ለቱሪዝም ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነሳሽነትና ንግግር ጠንካራና አበረታች መሆኑን አያይዘው በማንሳት፤ ነገር ግን በተቋም ደረጃ በተግባር የታየ ለውጥ አለመኖሩን አስታውሰዋል። እናም የስርዓት ለውጥ ያስፈልጋል፤ ለዚህም አንደኛውና ትልቁ በጀት ነው፤ በጀቱ መቅረብ አለበት፤ እንደ አስናቀ ገለጻ።

በተመሳሳይ ቱሪዝም ዘርፉ ላይ የሚመደቡ ባለሙያዎች ዘርፉን የማያውቁ መሆናቸው መቀየር አለበት። “ውጪ አገር መሔድ ብርቅ የሆነባቸው ሰዎች ናቸው ቱሪዝም ላይ የሚሠሩት። ውጪ ሲላኩ ለራሳቸው እንጂ ሠርተው የሚመጡት ለአገር አይደለም። እናም ባለሙያ መመደብ አለበት” ሲሉ አስረድተዋል።

ሌላውም የመዳረሻ ቦታዎች ተጠቃሚነትን በመጨመርና የእሴት ትስስሩን በማስቀጠልም መሥራት ያስፈልጋል። ይህም ሲሆን የመዳረሻ አካባቢዎች እንዲሻሻሉ ያስችላልና ነው። ማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ የማገልገል ስሜትና ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋልም ሲሉ ሐሳባቸውን ያስተላልፋሉ።

በተመሳሳይ ለዘርፉ ዕድገት ሐሳብና አስተያየት የሚሰጡ ሰዎችና ባለሙያዎችም ይህንኑ በተደጋጋሚ ያነሳሉ። ይልቁንም ቅድሚያ በዘርፉ ያለውን የሰው ኀይል በዘመናዊ መልክ ማደራጀት ያስፈልጋል የሚለው ሐሳብ ይጠቀሳል። ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያዩ አገራት ማስታወቂያዎችን ማሰራጨትንም ይመክራሉ። ይህም በአቀራረብ፣ በመረጃ ትክክለኛነት፣ በዲዛይን ውበት ደረጃውን የጠበቀ ሥራ መሥራት የሚለው ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ “መንግሥት የሚፈለግበትን ለመወጣት ቁርጠኝነት አለው፤ በተናጠል የሚደረግ ጥረት ውጤቱ ዝቅተኛ ስለሆነ ከባሀለብቱ ጋር ለመሥራት በጣም ዝግጁ ነው፤ ዘርፉንም ቁልፍ የዕድገት ምንጭና መንገድ አድርጎ ወስዶታል” ሲሉ ተናግረዋል። በመንግሥት በኩል ምቹ የሥራ ሁኔታ መፍጠር፣ ለተወዳዳሪነት አቅምን መገንባትና ድግፋን አጠናክሮ መቀጠል ላይም ይበረታል ሲሉ የመንግሥትን አቋም አንስተዋል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሒሩት ከሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው በተለይም በአንደኛው አገር ዐቀፍ የሆቴልና ቱሪዝም ኮንፈረንስ ላይ ቱሪዝምን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፤ በመተሳሳይ የሠለጠነ የሰው ሀብት አለመደራጀቱ፣ ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት አለመቻምና የመስህ ቦታዎች ለምተው በተገቢው መንገድ ተወዳዳሪ ሆነው አለመገኘታቸው ችግር መሆናቸውን ጠቅሰዋል። አክለውም ጥቅሙን በመመልከት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን አቃሎ የሚገኘውን ጥቅም ለመጨመር እየመከረና ተጨባጭ ሥራ ለማከናወን እየተሠራ ነው በማለት በቀጣይ ውጤት ጠብቁ ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 47 መስከረም 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com